ጌታችን ኢየሱስ ፍጹም ተንቆአል!
በአንድ ወቅት በክርስቶስ ኢየሱስ ጉዳይ በአይሁድ ሸንጐና ሕዝብ ክርክር መደረጉን፤
በመካከላቸው መለያየት በተደጋጋሚ መከሰቱንም የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ይነግረናል፤ (7፥43፤ 9፥16፤ 10፥19)።ለዚህ ምላሽ እንዲኾንም የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለማስያዝ
ያደረጓቸው ተግባራት ለኢየሱስ የነበራቸውን ንቀት ፍንትው አድርጐ ያሳያል። ዮሐንስ ይህን በሚገባ ይገልጠዋል፤ አስቀድሞ እነርሱ
ከሚያከብሩአቸው ሰዎች ታላላቅ ሰዎችን በመላክ ለኢየሱስ ያላቸውን አክብሮት ቢያሳዩም፣ በኋላ ላይ ግልጹ ዐሳባቸው ታውቆአል፤ ይኸውም
ለኢየሱስ ያላቸውን ንቀት ለማሳየት ጠባቂዎችንና ዝቅተኛ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ልከዋል፤ ነገር ግን ከፊተኞቹ የኒቆዲሞስ ማመን
ከኋለኞቹም ጠባቂዎች “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” የሚል ምስክርነት መገኘቱ እጅግ የሚደንቅ ነው፤ (ዮሐ. 7፥45-52)።
ንግግርና ዕይታ ብቻ ሳይኾን
አይሁድ እንዳደረጉት ለሰዎች ያለን ትኵረት መቀነስም፣ እዲሁ ከንቀት ሊያስቈጥር እንደሚችል ማስተዋል ይቻላል፤ ይህ ብቻ
ያይደለ ጌታ ኢየሱስን ለመስቀል በማሰብ ለይሁዳ ተተምኖ የተሰጠው የገንዘብ መጠንም ለኢየሱስ ያላቸውን ከፍተኛ ጥላቻና ንቀት
የሚያመለክት ነው፤
እንዲሁም ሳኦል ለኢየሱስና ለአማኞች የነበረው ንቀት እጅግ መራራ ነበር!አዎን
ቅዱሳት መጻሕፍት መሲሑ ኢየሱስ በምድር ካሉት ሰዎች ኹሉ እጅግ የተናቀ እንደ ኾነ ይነግረናል፤(ኢሳ. 53፥3፤ ሉቃ.23፥11፤
1ቆሮ.1፥28፤ መዝ.118፥22፤ ማቴ.21፥42፤ ማር.12፥10፤ ሉቃ.20፥17፤ 23፥18) ለኢየሱስ ከዚህ በተሻለ በምን
መንገድ ንቀታቸውን ይገልጡ ይኾን? ዓለምን የወደደው አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ፣ “ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን
እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤” እንዲል እኛም የተጠራንበት
ድንቅ ጥሪ ለመናቅና ከሰፈር ውጭ በመናቅ መከራን እንቀበል ዘንድ ነው!
አስቀድሞ እንደ ተናገርን፣
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመጣበት ወቅት በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ከፍተኛ የንቀት ስሜት ነበር! እርስ በእርስ ፈጽሞ
አይከባበሩም፤ አይቀባበሉምነበር፤ በምድሪቱ ሴቶች፣ ሳምራውያን፣ አሕዛብ፣ ቀራጮች፣ ዝቅተኛ ኑሮ ነዋሪዎች የተናቁና የተገለሉ ነበሩ!
በግልጥ ቃልና ምሳሌም በአዲስ ኪዳን ሳምራዊው ለወደቀው አይሁዳዊ ቸርነት እንዳደረገ ቢነገረንም፣ አይሁድ ግን ለሳምራውያን ያደረጉት
ቸርነት ፈጽሞ አልተጠቀሰም።
ስለኢየሱስ ጤናማውንና
የቀናውን ነገር የተናገረው ኒቆዲሞስም በአይሁድ ታላላቅ ባለሥልጣናት ፊት ከመናቅና ከመገፋት አላመለጠም፤ ኢየሱስን ከገሊላ አይመጣም
በማለት እንደ ናቁት፣ ኒቆዲሞስንም “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን?” በማለት ተናግረውታል፤ ቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱንም እንዴት እንደ ተናገሩት
ማስተዋል እንችላለን፤ “እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?” (ዮሐ. 7፥41፤ 52፤ ሐዋ. 2፥7)።
በእርግጥ እግዚአብሔር፣ “ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ” (መዝ. 15፥4) ነው፤ ኀጢአተኛ አካሄዱ ኹሉ እግዚአብሔርን የማያከብርና እንደ ፈቃዱም ሕይወቱን
የማይመራ ነውና፤ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር አንዳች ክብር የሌለው ኀጢአተኛን እግዚአብሔር ይንቀዋል ወይም ለገዛ ራሱ ይተወዋል፤
መዝሙረኛው ከተናገረው ከኀጢአተኛ ድርጊት አንዱ ገንዘቡን በአራጣ የሚያበድርና ጉቦ የሚቀበል ነው፤ እኒህ ሰዎች ደግሞ በራስ ስኬት ሰውን በሚያሳዝን መንገድ የሚደሰቱና በሰው ውድቀት ሃብትን የሚያጋብሱ
(gloating) ናቸውና እጅግ መራራ ናቸው፤ እንግዲህ ይህን ነው ጠቢቡ፣ “ኀጥእበመጣጊዜንቀትደግሞይመጣል፥ነውርምከስድብጋር።”
(ምሳ. 18፥3)።
ስለዚህ እውነተኛ
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከኾንን የዕብራውን መልእክት ጸሐፊ እንደ ጻፈልን መንገዱን መከተል ለእኛ ይገባናል፤ ሙሽራው በምድር ላይ
ንቀትና መስቀልን ከተቀበለ፣ እኛ ለሚንቁን አጸፋ በመመለስ ነፍሳችንን ከማዛል ይልቅ ክብርን ከሰማይ እየጠበቅን በትእግስት ሩጫችንን
መሮጥ ይገባናል። ለዚህም ደግሞ ለምናምን ለእኛ ደሙና መንፈስ ቅዱስ ፍጹም ኀይላችን ነው፤ አሜን።
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment