Sunday 2 February 2020

ንቀት (ክፍል ፰)

Please read in PDF
1.    በአገራችን አስተዳደጋችን ምንታዌነት አለው
   በመጀመሪያቱ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ የነበሩት ባሪያዎች፣ አንዳንዶቹ በጌታ ኢየሱስ ያመኑ ነበሩ፤  ስለዚህም እኒህን ባሪያዎች እንደ ወንድሞቻቸው እንጂ እንደ ቤት አገልጋዮቻቸው እንኳ አይመለከቱአቸውም ነበር፤ ነገር ግን እኒህ ባሪያዎች በተቃራኒው ጌቶቻቸውን መናቅ ጀመሩ፤ የክርስትናው ነጻነት ይበልጥ ሊያከብሩአቸውና ሊሠሩላቸው እንዲገባ ማዘዙን ዘነጉት፣ እነርሱ ግን በተቃራኒው አደረጉ። አንድ አገልጋይ በግዴታ ያገለግል በነበረበት ወራት ይሠራ የነበረውን ሥራ ኹሉ፣ አኹን ግን በፍቅር መሥራት ተሳነው። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ፦
የሚያምኑም ጌቶች ያሉአቸው፥ ወንድሞች ስለሆኑ አይናቁአቸው፥ ነገር ግን በመልካም ሥራቸው የሚጠቅሙ የሚያምኑና የተወደዱ ስለሆኑ፥ ከፊት ይልቅ ያገልግሉ።” (1ጢሞ. 6፥2)

በማለት ቅዱስ ጢሞቴዎስ ለባሪዎች የተሰጠውን መመሪያና ትእዛዝ እንዲያስተምርና እንዲመክር የተነገረው። ክርስትናው የሰጠን ነጻነት ይበልጥ በፍቅር እንድንታዘዝ እንጂ ፈጽሞ እንድንናናቅ አይደለም። በአገራችን ሠራተኞችን መናቅ እጅግ የተለመደ ነው፤ ሠራተኞችም በዚያ ስቃይ ውስጥ እንደሚኖሩ እርግጥ ነው፤ ግና እንዲህ ያለውን መራራ ባህል አሽቀጥሮ መጣል፣ መንግሎ መንቀል ያሻል።
 በሌላ እይታ፣ በአገራችን ተጨባጭ ኹኔታ፣ ከክርስትናው ውጭ ባለን የባህልና እሴት አስተዳደግ፣ በክርስትናው ውስጥም ስንመጣ መከበርና የከበሬታ ቦታ ወይም ስፍራ ወይም ወንበር እንዲለቀቅልን እንፈልጋለን። በአጭር ቃል በብዙ የመከበር ፍላጎት በአገራት ባህላት ውስጥ ተንሰራፍቶ አለ፤ በክርስትናው ውስጥም ስንመላለስ እንዲያ እንዲያደርጉልን በብዙ እንጠብቃለን። ስለዚህም በስሙ አንዳች ነቀፋና መገፋት፣ ስድብና መገለል ሲያገኘን ፈጥነን ከመስመር የመውጣት፣ ከኢየሱስ የመለየት ዕጣ ይገጥመናል።
   በአንድ ወቅት እጅግ በተደጋጋሚ ያገለገልኩትና በአገልግሎት ዘመን በብዙ የምበልጠው አንድ ወንድሜ፣ ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር “እስኪያጥወለውለኝ በብዙ ንቀት” ተናገረኝ፤ እናም እጅግ በጣም ተናደድሁ፤ ተቈጣሁ፤ ነገር ግን ወደ ልቤ በተመለስሁ ጊዜ የመጣው የመንፈስ ቅዱስ የወቀሳ ቃል፣ “እኔን አገልግለህ አንተ ትከበር ዘንድ ይገባሃልን? እንኪያስ ለምን ፊትህ ጠቆረ?፣ ልብህስ ለምን በሃዘን ተመላ?” የሚል ነው። አዎን! የኖርንበት ባህል አንዱ ሌላውን እንዲያከብር በብዙ ያዝዛል፤ ይህ እጅግ መልካም ቢኾንም ነገር ግን የተሰቀለውን ኢየሱስ ስናገለግል መናቅን ፈጽሞ እንዳንዘንጋ!
   ኢዮብ ለእግዚአብሔር ሥራ ከመናቁ የተነሣ መዝፈኛ እስኪኾን መዋረዱን እንዘነጋለን፤ በ“ሰው” ዘንድ ጳውሎስ በንግግሩ የተናቀ ነበር፤ (2ቆሮ. 10፥10)፤ በእርግጥም ለእግዚአብሔር ወንጌል ብቻ ራሳችንን የተመሰገንን (ትክክለኞች) አድርገን እናመሰግናለን እንጂ በምንመሰክረው ወንጌል ለሚያገኘን የትኛውም ንቀትና መንጓጠጥ ልናፍርበት ወይም መልስ ማዘጋጀት የሚነግረን የኢየሱስ የሕይወትም የትምህርትም አብነት የለንም!
ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” (ማቴ. 5፥11-12)
2.   በአገራችን በአንዳንድ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች ዘንድ ግልጥ መናናቅ አለ፦ ስማቸውን ጠቅሰን መናገር በምንችላቸው ብሔረሰቦች መካከል ግልጥ መናናቅ አለ፤ በሥራና በአገልግሎት ምክንያት የተለያዩ ብሔረሰቦችን የማግኘት አጋጣሚው አለኝ፤ በእኔም በራሴ እንኳ በመኪና አደጋ ፊቴ ላይ ባለው ጠባሳና በቋንቋዬ ቃና ብዙዎች የተለያየ ግምታቸውን ሲነግሩኝ እደነቃለሁ፤ ቢያንስ ስለ ራሴ ከሦስት በላይ ብሔር ለበስ “ማንነት” እንዳለኝ ሲነግሩኝና ሳስብ፣ እንኳንም ኾንኩ እላለሁ፤[“ሰው፤ ሰው” ብቻ እንድሸት ይህ ሃብት ቢኾንና እፍል ቢኖረኝ እላለሁ፤ ነገር ግን ሰውነት የእግዚአብሔር መልክና አምሳል በቂው ነው።] በተለይም ደግሞ በአንዱ ብሔረሰብ ስም የተለያዩ የቋንቋ ዘዬዎችን በመናገሬ በማይወዱትና መስማት በማይፈልጉት መካከል ስናገር እንዴት ያለ ንቀት እንደሚደርስብኝ ሳስብ እደነቃለሁ።
    አንዳንድ የአገራችን ብሔረሰቦች የመናናቃቸው ምክንያት እጅግ ብዙ ነው፤ በአገር ደረጃ እንዲህ ያለ ነገር መኖሩ አንዳች አይደንቅም፤ መጽሐፍ፣ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።” ይላልና፣ ነገር ግን እንዲህ ያለ ነገር በአብያተ ክርስቲያናት መካከል እንዳለ ስንሰማ እጅግ ከመደነቅ ባለፈ እናዝናለን።
   በአባላት ቊጥር ብዛት ስለሚመኩ አብያተ ክርስቲያናት ስንቶቻችን እናውቅ ይኾን? በንቀትስ አንዳቸው ከሌላው አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናንና ምዕመናትን የሚሰራረቁ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉስ የምናውቅ ስንቶች እንኾን? “በጎቼን ሰረቀብኝ” የሚባባሉ የአገልጋዮችን የእርስ በርስ ክስና መነቃቀፍን ስንሰማ፣ ምን ያህል ልብ የሚሰብርና ኢ መንፈሳዊ ነገር በክርስትና ስም በመካከላችን እንደ ፋነነ፤ ክፉ ፍሬም አብቦ እንዳፈራ ማስተዋል አያዳግትም።
3.   ከኢየሱስ ጋር ሕይወታችን አልተጣበቀም፦ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ተናቁት ወገኖች የቀረበና ያጽናናቸው ቅዱስ አባት ነው፤ በተመሳሳይ ደግሞ በግብዝነት ሌሎችን የሚንቁትን ደግሞ ፊት ለፊት ገስጾአቸዋል፤ ነቅፎአቸው፤ (ሉቃ. 7፥39-43)። እርሱ ግብዝና አስመሳይ ያልኾኑትን ቀረጥ ሰብሳቢ፣ አመንዝሮች፣ ቀማኞች ተብለው ማኅበረ ሰቡ ያገለላቸውን ኀጢአተኞች ሳይንቅ፤ በልዩነትም ሳይመለከትም  ተቀብሎአቸዋል፤ እጅግ ወዳጃቸው እስኪባልም በአንድነት አብሮአቸው ተመግቦአል፤ (ሉቃ. 15፥1)።
   ዛሬ ላይ ግን ኀጢአተኞች ወይም በኾነ አንድ ነገር ከእኛ ጋር አንድ ያልኾኑ ሰዎችን መናቅ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ተጠምደንበታል። ጌታ ኢየሱስ ካደረገው ነገር ወይም ካስተማረው ትምህርት የቱም ልባችንን ሊገዛው የወደደ አይመስልም። መንፈስ ቅዱስ ምሕረት ያድርግልን፤ አሜን።
ይቀጥላል …


No comments:

Post a Comment