3. ወታደር፦ ከሰይጣንና ከክፋት ኃይላት ጋር የምናደርገው ትግል ወታደር በጦርነት ሥፍራ
ከሚያደርገው መጋደል ጋር ተመሳስሏል፡፡ እንዲያውም የተነገረን፣ “በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ” (ኤፌ.6፥10)
በሚል ትእዛዛዊ ቃል ነው፡፡ መጋደላችንም ደምን እስከማፍሰስ ድረስ መቃወም ሊኖርበት ይችላል፤ (ዕብ.12፥4)፤ እንደበጎ ወታደርም
የክርስቶስ ኢየሱስን መከራ መካፈል እንደሚገባም ጭምር፤ (2ጢሞ.2፥3)፡፡
የብዙዎቻችን የክርስትና ሕይወት ሲታይ በክርስቶስ
ለክርስቶስ መኖርን አያመልክትም፡፡ በሌላ ንግግር ትኩረታችን ጌታ ኢየሱስ ብቻ አይደለም፡፡ ከእርሱ[ከጌታ ኢየሱስ] የሚያንሱ ነገሮችንም
ከእርሱ ጋር አስተካክለን ይዘን መጓዝ እንፈልጋለን፡፡ እንደሯጭ የሩጫውን ሥርዐት ወይም መማችንን[መስመራችንን] ብቻ፤ እንደባርያ ደግሞ ለገዛን
ጌታ ፈቃድ ብቻ መኖርን አልተለማመድንም፤ አላሳደግነውምም፡፡ መንገዳችንን ለማቅናትና ትኩረታችንን ሁሉ በጸጋውና በ“ጸጋው ተቀባዮች”
ላይ ከማድረግ ይልቅ፣ በእርሱ ላይ ብቻ እንድናደርግ፤ የወታደርን ጠባያት ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጣጥተን እንማማርበታለን፤ ጌታ እግዚአብሔር
መንፈስ ቅዱስ ይርዳን፤ አሜን፡፡
ወታደር፦
1. “የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት
ንግድ ራሱን አያጠላልፍም” (2ጢሞ.2፥4)፦ “በዚህ ምድር ያሉ” ብዙ ነገሮች በራሳቸው ክፉ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር
ግን ወታደር መልካም ነገሮችን ሁሉ በመሰብሰብና በመሸከም ራሱን አያደክምም፤ እንዲያውም ወታደራዊ ባልሆነ ሕይወትና ልምምድ ውስጥ
ራሱን አያባክንም፡፡ ቁጥብ ኑሮ፣ አጭር ትጥቅ፣ ትኩረቱንም ሁሉ ወደአንድ አቅጣጫ ወደአዛዡ ማድረግ [እርሱን ለማስደሰት] ብቻ ነው፡፡
የአማኝም፤ የአገልጋይም ትልቁ ግቡና ዓላማው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በዘመኑ
ሁሉ ደስ ማሰኘት ነው፡፡ በማናቸውም አገልግሎታችንም ሆነ የሕይወት ዘይቤዐችን ውስጥ ክርስቶስን ማስደሰት ካልቻልን በሁሉ ነገር
ምስኪን ነን፡፡ እውነተኛ ወታደር የግል ዕቅዱንና ኑሮውን ሳይቀር፣ ለወታደራዊ ሕይወቱ ራሱን ኣሳልፎ ይሰጣል፡፡ እኛም እንኖርለታለን
ላልነው ጌታ ከወታደርነት ሕይወት ያነሰ ኑሮ ልንኖር አልተጠራንም፡፡
ሸክም መቀነስ፣ ጥቂቱንና እጅግ አስፈላጊውን ብቻ መያዝ፣ ሌላውን መናቅና
መተው የወታደር ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡ ዳዊት “ጎልያድን” ለመዋጋት ወደጦሩ ሥፍራ ሲሄድ ንጉሡ ሳዖል የራሱን
ካባ አልብሶት ነበር፤ “ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰ፡፡ ዳዊትም
ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ፡፡ ዳዊትም ሳኦልን፦ አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም
አለው፡፡ ዳዊትም አወለቀ፤” (1ሳሙ.17፥38-39)ይለናል፡፡ አስተውሉ! ሰውየው ብቻ የሚፈተን አይደለም፤ የሚታጠቀው ትጥቁም ከወታደሩ
ጋር አብሮ የተፈተነ መሆን አለበት፡፡
የሳዖል ካባው ውድና እጅግ የከበረ ሊሆን ይችላል፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር
ስምና ሕዝብ ላይ ከሚሳለቅ ሰው ጋር ውጊያ ለመግጠም ፈጽሞ አይመችም፡፡ ስለዚህ ያልተፈተነውን መሣርያና ትጥቅ አውልቆ ጣለው፤ እናም
አብሮ የተፈተነው “በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ”
ይዞ ወደውጊያው በመግባት ውጊያውን በድል አጠናቀቀ፡፡ ካልተፈተነ የቦና ጭሬ ይልቅ የተፈተነ ጠጠር እጅግ መልካምና ለድል የሚያበቃ
መሣርያ ነው፡፡
2. የምንዋጋው የትና ከማን ጋር እንደሆነ ማስተዋል፦ በምድራዊው
ውጊያ ወታደር ምንጊዜም ስለባላጋራው በቂና አስተማማኝ ማስረጃ አለው፡፡ ማጥቃትና መከላከል የሚያስችል መሣርያ ለመታጠቅ፣ ስለጠላታችን
ማንነትና ትክክለኛ መረጃ ሊኖረን አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም፡፡ የውጊያውም ሥፍራ ጠላት ባለበት በዚያው አድራሻ ነው፡፡
የምንዋጋው ወይም “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና
ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ፤” (ኤፌ.6፥12)፡፡
የሚቃወሙን ሰዎች ዋና ባላጋራዎቻችን ወይም ጠላቶቻችን አይደሉም፡፡ እነርሱንም እንደዋና ጠላቶቻችን በመቁጠር በቁጣና በጥላቻ ልንነሣሣባቸው
አይገባንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ማድረግ እንደሌለብን በማስጠንቀቂያ ይናገራል፡፡ ዋናና ልንዋጋቸው የሚገቡን ጠላቶቻችን “አለቆች”፣
“ሥልጣናት”፣ “የጨለማ ዓለም ገዦች” እና “በሰማያዊም ስፍራ ያሉ የክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት” ናቸው፡፡ እኒህ የአጋንንት ክፍለ
ግዛት አይነቶች አይደሉም፤ ረቂቅና ስውር ዓላማን ይዘው በእግዚአብሔርና በቅዱስ ሕዝቡ ላይ የተነሣሱ የክፋት ኃይላት ናቸው፡፡ የሐዋርያው
አጠቃቀስ ያላቸውን የክፋት ደረጃና እኩይ አላማቸውን ገላጭ ነው፡፡ ሰይጣን ሁል ጊዜ ዋና ዓላማው እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር
የሆነውን ሁሉ መዋጋት ነው፤ (ራእ.12፥17)፡፡
የሰይጣን
ኃይላት ተራና በሥጋና በደም ጉልበት ድል የምንነሣቸው ወይም የምንዋጋቸው አይደሉም፡፡ ቁሳዊውን ዓለም አይተን በሥጋና በደም በመዋጋት
ያሳለፍነውን ዘመናችንን በንስሐ ዘግተን፣ አሁን ጠላቶቻችን ባሉበት
በዚያ ውጊያችንንም ለማድረግ መነሣትና በእግዚአብሔር ዕቃ ጦር ትጥቃችንን “ማሰናዳት” ይገባናል፡፡ ብዙ ጊዜ ጉልበታችንና ጊዜያችንን የፈጀነው አላስፈላጊና አላግባብ በሆኑ የሰልፍ
ሜዳዎች ላይ ነው፡፡ ከሥጋና ከደም ጋር በመታገል፣ በመነታረክ፣ በመጠላላት፣ በመፋለም፣ እሰጣገባ ውስጥ በመግባት ዘመናችንን የፈጀን
ብዙ ነን፡፡
እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር ማንሳቱ አስፈላጊ ነው፤ ዘመናችንን ከሥጋና
ከደም ጋር የጨረስነውን ያህል፣ በተቃራኒው ደግሞ ሥጋና ደም የተሸከሙ አገልጋዮችን በመከተል ጌታ ኢየሱስ ዘንድ ሳንደርስ ያሳለፍነው
ዘመን እጅጉን ሊያንገበግበን፤ ሊያጸጽተንና በትልቅ እንባ ወደአዳኝና ቤዛችን እንድንመለስ አስተውሎት[ምክንያተ አስተውሎት] ሊሆነን
ይገባል፡፡
አዎን! የምንዋጋው የክፋት አለቆች፣ የሥልጣን ዓላማቸው ከፍ ካለ፣ በጨለማ
ሥልጣናቸው እግዚአብሔርንና ሕዝቡን በመቃወም ከተነሡ ርኩሳን ሰማያውያን መናፍስትና አጋንንት ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ውጊያችን ከመናፍስት
ጋር በሰማያዊ ሥፍራ ነው፡፡ ይህንን ማስተዋል ጉልበታችንን ከሥጋ ለባሽ ጋር እንዳናባክንና ለሥጋ ለባሹ ሰው በመራራት፤ ለክፉና
ለጨካኙ ባላጋራችን ያለአንዳች ርኅራኄ እንድንዋጋ ያስችለናል፡፡
አሁን ባለንበት
ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ “የሚያማምሩ ሕንጻዎች” ሲገነቡ እናያለን፤ በተለያየ ዓውደ ምሕረትም የሚያገለግሉ በቁጥር የበዙ አገልጋዮችን
እያየን ነው፤ ይህ ጥሩ ቢሆንም ፍጹም ግን በቂ አይደለም፡፡ ለሰይጣን አደገኛው ነገር እንደእሳት ትንታግ በቃልና በሕይወት የተመሰከረላቸው
ጥቂት አገልጋዮችንና አማኞችን ማየት ያሸብረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ችላ ብላለች፡፡ መገልገሉን እንጂ
የአገልግሎቱን ቅድስና፣ ሩጫውን እንጂ የሚሮጥበትን መንፈስ መጋደሉን እንጂ ከማን ጋር እንደምንጋደል መለየት የተፈለገ አይመስልም፡፡
ጌታ ኢየሱስ
ግን ይህን በግልጥ ለይቶ ተናገረ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ለጌታ ሞትና መከራ በተሻለ የቀና መስሎ፣ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤
ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ፤” ጌታ ኢየሱስ የመጣበት ዋናው ዓላማው፣ “ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና
ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ” ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ስለሰው
ልጅ መዳን ሁሉ ነበር፡፡ ይህንን ታላቅ ሰማያዊ ምስጢር እንዳይፈጸም የሚሻ ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ ጌታ ይህን በሚገባ ስለሚያውቅ፣
ሥጋ ለባሹንና የማያስተውለውን ጴጥሮስ ሳይሆን፣ እርሱን ተገን አድርጎ “ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋ”(ዮሐ.10፥10) የመጣውን ሰይጣንን፣
“ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው” (ማቴ.16፥22-23)፡፡
የእግዚአብሔርን ሃሳብ በዘመናችን ልንፈጽም ስንነሣ የሚዋጉንን ሰዎች ሳይሆን ከእነርሱ ጀርባ ያለውን ክፉ ሰይጣንን ፈጽሞ መዘንጋት
የለብንም፡፡ ከማን ጋር እንደምንዋጋ በትክክል እናስተውል፤ ከሥጋ ለባሽ ጋር በመታገል ዘመናችን አይባጅብን፡፡
አቤቱ ማስተዋልን አብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
Geta Eyesus Kiristos Abzto abzto ybarkih wendme
ReplyDeletetsega yibzalh!
ReplyDelete