Friday 14 April 2017

ዳኞቹ

Please read in PDF    

    እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነው፤ (መዝ.7፥11)፡፡ በፍርዱም ጻድቅና የማይሳሳት፤ በቅንም ፈራጅ(ኤር.11፥20) ነው፡፡ ልብንና ኵላሊትን የሚመረምር አምላክ ነው፤ የሰውን ውስጣዊ ማንነት የሚፈትንና በፊቱም አንዳች የተሰወረ ነገር የሌለ አምላክ ነው፡፡ ደግሞም “ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ የሚሰጥ” አምላክ ነው፤ (ኤር.17፥10 ፤ ራእ.2፥23)፡፡ እግዚአብሔር የልብንና የውስጣችንን ነገር ሁሉ ስለሚያውቅና ስለሚመረምር በፊቱ የተሰወረ አንዳች ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ጻድቅ በእግዚአብሔር ጽድቅ በእምነት ይመካል፤ እንጂ አልበደልኩም እያለ አይሞግትም፡፡
    ዳኝነት እውነትን በማጽደቅ፤ ሐሰትን በመጸየፍ የተከበበ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህም ፈራጅ ከምንም በላይ በመልካምነቱ በተመሰከረለት “ትልቅ” ሥነ ምግባር የታነጸ ሊሆን ይገዋል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ለዚህ ነው፣ የእስራኤል ዳኞችን የሥነ ምግባር መመዘኛን ለቅዱስ ነቢይ ሙሴ፣ “አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በአገርህ ደጅ ሁሉ በየነገዶችህ ፈራጆችንና አለቆችን ሹም፤ ለሕዝቡም ቅን ፍርድ ይፍረዱ፡፡ ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል፡፡ በሕይወት ትኖር ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም የሚሰጥህን ምድር ትወርስ ዘንድ እውነተኛውን ፍርድ ተከተል፤” (ዘዳግ.16፥18-20) በማለት የተናገረው፡፡

     ፈራጅ እውነትንና ጽድቅን ከመከተል ቸል ካለ፣ በሕዝብ መካከል ከፍ ያለ የሥነ ምግባር ውድቀት ከመታየቱም ባሻገር፣  ፍትህ አልባነት በምድሪቱ ይነግሣል፡፡ ከዚህም የተነሣ ኃጥእ ጸድቆና ተወድሶ፤ ጻድቅና ለእውነት የሚያደላ ሁሉ ሊወቀስና ሊነቀፍ ይችላል፡፡ የሳሙኤል ልጆች እንዲህ ባለ ነውር ተይዘው ነበር፤ “ … ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር፤” (1ሳሙ.8፥2) እንዲል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ግፍና ኃጢአትን ፈጽሞ እንደሚቀጣ ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋትና ምልአት ይመሰክራሉ፡፡
    በጌታ የአገልግሎቱ ፍጻሜ ወራት አይሁድ ያቀረቡበትን ክሶች የዳኙና ጉዳዩን የመረመሩ የጊዜውን ዳኞች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ የሰው ክፋት ሲገን፣ ኃጢአት እንደውኃ ጭልጥ ተደርጐ ሲጠጣ፣ ርኩሰት የቤተ መቅደሱን ድንበር ጥሶ ሲገባና በዙፋኑ ሲቀመጥ፣ ረበናትና የሕጉ አገልጋዮች ለፈቃዳቸውና ለገዛ ክብራቸው ሉዐላዊውንና ቅዱሱን ሕግ ሲሽሩና እንደገዛ ፈቃዳቸው ሲተረጉሙ፣ የጌታን ፈቃድ ሲያጐድሉና ቅጥሩን ሲያፈርሱ የዚያኔ ዳኝነትና መንፈሳዊ፣ ሚዛናዊ፣ ለእግዚአብሔር ቅድስና ያደላ እይታና ብይን ግድ ያስፈልገናል፡፡
    በጌታ የሕማሙ ዘመን ካየናቸው ዳኞች አንዱ ጲላጦስ[1] ነው፡፡ ስለጲላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ብዙ ነገሮች አሉት፤ የበደለበትን ምክንቶች ብናነሳ፦
1.     ቋኝና ጨካኝ ገዢ ነበር፦ ሉቃስ ወንጌላዊው ለምን እንደተደረገ ምክንያቱን ባይነግረንም፣ የጲላጦስን ጭካኔ የሚያጎላ፣ ብዙ ሰዎች የተገደሉበትን አንድ ድርጊት ግን ይነግናል፤ “በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ለኢየሱስ አወሩለት” (ሉቃ.13፥1) ይለናል፡፡
    ጲላጦስ የገደላቸው ሰዎች ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር መደባለቁ፣ እጅግ አረመኔያዊ ድርጊቱን ያሳያል፡፡[2] ምናልባትም ጲላጦስ እኒህ ሰዎች የሮማን ሕግ በመጣሳቸው ወይም የገዛ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ያስገዳላቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያም ሆነ ይሀ ግን የሰው ነፍስ አንሶ ሥልጣንና የራስ ማንነት ገዝፎ ታይቷል፡፡
    እንዲህ ያለ ነገር ለአገራችንና ለአፍሪካ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለሥልጣንና ዙፋንን ለማስጠበቅ የገዛ እናትንና ወንድምን መግደል፣ በአምባዎች ወኅኒ ቤቶች ማጎርና ማሰር፤ ያለፈው ዘመን ንስሐ ያልገባንበት የአደባባይ ነውራችን ነው፡፡ ምናልባት ያ የክፋት መንገድ ዛሬም ሲደገም እንጂ ሲታፈርበት አይታይም፡፡ ለሥልጣን ድልድል ነፍስ ማጥፋት፣ ለዙፋን ደህንነት ሰውን መግደል፣ ለፖለቲካቸው ማማር ሕጻናትንና አዛውንትን በቦንብ ጢስ በጥይት አረር ማደባየት “የሥልጡኑም፤ የድሆቹም” አገራት መሪዎች መገለጫ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ 
    ጲላጦስ ከጭካኔውና ከአይሁድ ጠልነቱ አንጻር፣ ኢየሱስን ለማዳን ብዙ ከአይሁድ ጋር “መታገሉና መለማመጡ” የብዙ አስኳላ ትምህርት ተማራማሪዎችንና ፈላስፎችን ልብ ያሸፈተና “ለምን” ብለው በምርምር እንዲሞግቱ ያደረገ ሁኔታ ነው፡፡ ጲላጦስ ጥረቱ ሁሉ መና የሆነውና በፍጻሜው በሚጠላው የአይሁድ ወግና ሥርዓት መሠረት እጁን በመታጠብና “ … በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? … ሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?” (ማቴ.27፥17 ፤ 21) በማለት እንደሕጋቸው እስረኞችን ያማረጠበትን መንገድ[3] መምረጡ ብዙ ግር የሚያሰኝና በእርግጥም ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነገር ነው፡፡
     ጸረ አይሁድ የሆነው ጲላጦስ ድንገት በኢየሱስ ጉዳይ ለዘብተኛ ሆኖ መቅረቡና እነርሱን “መለማመጡ” የሚደንቅ ጠባዩ ነው፡፡[ምናልባት ለራሱ በብዙ መድከሙ ወይስ ኢየሱስንም ኤይሁድንም ላለማጣት አስቦ ይሆን?] ጲላጦስ ንጹሑን ሰው ወደፍርድ ማምጣቱ ከባድ ሕሊናዊ ሙግት ውስጥ ከትቶታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሑ ጌታ ስለንጹሕነቱ በምንም ዓይነት ሁኔታ ራሱን ሲከላከል አልታየም፡፡ እንዲያውም ጲላጦስ በእርሱ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው፣ “አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” ብሎ ሲናገረው፣ “ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው” (ዮሐ.19፥10-11) የሚለው የጌታ ጽኑዕ ምላሽ፣ የእርሱ ሞት ቀድሞ የተወሰነ መሆኑን፤ ይህም በጲላጦስ እጅ አለመሆኑን በአጽንዖት ይናገራል፡፡
    ይህ ቢሆንም እንኳ ጲላጦስ በእግዚአብሔር ዓይን ፈጽሞ ንጹሕ ሰው አይደለም፡፡ በብዙ መንገድ ያረጋገጠውን እውነት ከመቀበል ይልቅ፣ ጻድቁን ሰው አሳልፎ በመስጠት የአይሁድ የክፋት ተባባሪ ሆኗል፡፡ ኃላፊነቱን በአይሁድ አላክኮ ለራሱ ንጹሕ ሊሆን ወደደ፡፡ ነገር ግን በሌሎች ኃጢአት መስማማት ሁሉ፣ ዋና የኃጢአት ተባባሪነትን በግልጥ ያሳያል፡፡ ሳውል በእስጢፋኖስ ላይ ምንም ድንጋይ ባያነሳም፣ ነገር ግን የገዳዮችን ልብስ በመጠበቁ በሞቱ ሙሉ ለሙሉ መስማማቱን ያሳያል፡፡ ኃጢአት ሁል ጊዜ ድርጊት ብቻ አያመለክትም፤ ለድርጊቱ መነሻ የሆነውን ተስማሚ ክፉ ሃሳብ ጭምርን እንጂ፡፡ በጲላጦስ የሆነው እንዲሁ ነው፡፡
2.    የሱስን በመግረፍ ብቻ ሊያድነው ሞከረ፤ ጲላጦስ አይሁድ በቅንአት እንደጠሉትና ሊገድሉት እንዳሰቡ አውቋል፤ ሚስቱም፣ “ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ መልእክት ልካበታለች” (ማቴ.27፥19)፤ ደግሞ ራሱም ጌታ ኢየሱስን ሲመረምረው ምንም በደል እንዳላገኘበት፣ “በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም”፣ “ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም”፣ “ሦስተኛም፦ ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም” (ሉቃ.23፥4 ፤15 ፤ 22) በማለት በተደጋጋሚ በእርግጠኝነት ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ምስክር ባሻገር በነጻ ከመልቀቅ ይልቅ ገርፎ “ሊለቅቀው” ወደደ፡፡
    ጲላጦስ ሁለት ነገሮችን በማድረግ ፍጹም ስቷል፤ ንጹሕ መሆኑን እያወቀ ገረፈው፤ ገርፎ ሳያበቃ ለሁለተኛ “ቅጣት” ለክፉ ሃሳባቸው አሳልፎ ሰጠው፡፡ ይባስ ብሎ እጁን በመታጠብና ከኃላፊነት በመሸሽ ንጹሕ ለመሆን ሻተ፡፡ በተለያየ መንገድ ብዙ ማስጠንቀቂያ ደርሶት፣ ሁሉንም ችላ ብሎ ያለፈ ወይም ለሥልጣኑ ያደላ ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር ግን በደልን እንዳያደርግ፣ ጻድቁም ላይ እጁን እንዳያነሳ በብዙ ትእግስቱና ምሕረቱ ጎብኝቶት፣ ዕድልም ሰጥቶት ነበር፤ ግን አልተጠመቀበትም፡፡ ከእግዚአብሔር ሃሳብ ይልቅ ለሰው ሃሳብ ተሸነፈ፡፡ እግዚአብሔርን ከማስደሰት ሰውን ወደማስደሰት አደላ፡፡ ከእጅግ በጣም ትልቁ፣ እጅግ መናኛውንና ኃላፊውን ክብር መረጠ፡፡
     እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዳናደርግ በብዙ መንገድ ያስጠነቅቀናል፤ ዕድልም ይሰጠናል፡፡ ከዚህም ሲልፍ ከሠራን በኋላ እንኳ ብዙ የመመለሻ መንገድን ያበጅልናል፤ ግን መስማትና ተቀብሎ መመለስ የሰው ድርሻ ነው፡፡ “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና” (ኢሳ.1፥19-20) እንዲል፡፡ በተለይም እንደአገራችን እንደሕዝባችን ብዙ የንስሐ ዕድል የተሰጠውና የበዛለት ያለ አይመስልም፡፡ ነገር ግን ዛሬም ልባችንን አደንድነናል፡፡ ከመመለስ ይልቅም ምክንያታችን የሚያድነን መስሎናል፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቆየን፡፡





     [1] ከ26-36 ዓ.ም የነበረ የይሁዳ ገዥ ሲሆን (ሉቃ.3፥1)፤ የጴንጤን አገር ሰው ወይም ጴንጤን የተባለ ቤተሰብ ወገን ነው፡፡ የሮምን ወታደሮች ሰንደቅ ዓላማዎች ወደኢየሩሳሌም በማምጣቱ አይሁድን አስቀየመ፡፡ ጸረ አይሁድ ወይም ጸረ ዘረ ሴም በመሆኑ ምክንያት አይሁድን ለማበሳጨትና ሃይማኖታቸውን ለማንቋሸሽ ብዙ ነገሮችን አድርጓል፡፡ የቤተ መቅደሱን ገቢ ሁሉ በመውሰድ ለውኃ ፕሮጀክት ግልጋሎት እንዲውል ማድረጉ፣ በአንድ ወቅት በኢየሩሳሌም ከተማ የቄሣርን ምስል ማቆሙ … በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በፍጻሜውም ብዙ ሳምራውያንን በማስገደሉ በ36 ዓ.ም ተከሶ ከሥልጣኑ ተሻረ፡፡ አንዳንዶች በራሱ ራሱን እንዳጠፋ ሲናገሩ፣ አንዳንድ ትውፊቶች ግን አምኖ ክርስትናን እንደተቀበለና በሰማዕትነትም እንዳረፈ ይናገራሉ፡፡
    [2] ከዚህ ባለፈ በአንድ የአይሁድ ተቃውሞ ላይ ወታደሮችን አስታጥቆ ሲቪል ልብስ በማልበስና በሕዝቡ መካከል በመልቀቅ ብዙ አይሁድን አስገድሏል፡፡
[3]  በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁበዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው”፤ (ዮሐ.18፥39 ፤ ማቴ.27፥15) እንዲል፣ አይሁድ በፋሲካ በዓል ለእስረኛ ምሕረት የማድረግ ልማድ ነበራቸው፡፡ ጲላጦስ ይህንንም የእነርሱ ሥርዓት ማክበሩን እናያለን፡፡

2 comments:

  1. እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዳናደርግ በብዙ መንገድ ያስጠነቅቀናል፤ ዕድልም ይሰጠናል፡፡ ከዚህም ሲልፍ ከሠራን በኋላ እንኳ ብዙ የመመለሻ መንገድን ያበጅልናል፤ ግን መስማትና ተቀብሎ መመለስ የሰው ድርሻ ነው፡፡
    GEta tsega yabzalihi

    ReplyDelete
  2. tsega yibzalh

    ReplyDelete