መግቢያ
በአንድ ሰሞን “ኦርቶክሳዊ ተብሎ ባለመጠራቱና የሌላ ቤተ እምነት ተከታይ
ሆኗል ተብሎ መጠርጠሩ ያናደደውን ዘፋኝ” ተመልክቼ፣ “ዘፋኝ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ምኗ ነው?” ብዬ ሃሳቤን ማፍሰሴ የሚዘነጋችሁ
አይደለም፤ በዚያን ሰሞንና ከዚያም በኋላ ዘፋኙን “በመገሰጼ” የበዙ ተቃውሞዎች ገጥመውኝ ነበር፤ ተቃውሞዎቹ ሁለት መልክ አላቸው፤
አንዳንዶች የሌላውን[የዘፋኝን] ኃጢአት የምታወራው አንተ ማን ነህ? የሚሉ ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ዘፈን ያልተከለከለ መሆኑን፣ ሥራ(ሙያ)
መሆኑን፣ “እግዚአብሔር የሚባርከው” መሆኑን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የተጠቀሰ መሆኑንና ዳዊት መዝፈኑን፣ “እግዚአብሔርን በዘፈን
አመስግኑት” መባሉን፣ ብሎም መኃልይ መኃልይ ዘሰሎሞን ስለ“ተቃራኒ ጾታ” ግንኙነት ካወራ፣ እኛስ ምናለ እንዲያ ብናደርግ የሚል
“ሙግት” መልክ ሊያቀርቡልኝ ብዙ ጥረዋል፡፡ በአብዛኛው ግን ስድብ መልክ ስለነበረው አያንጽም፣ ሰውንም አያስተምርም ያልኩትን ሁሉ
ለራሴ ከማንበብ፣ ሰዎችም እንዳይመለከቱት በማድረግ ወደቅርጫት እንዲጣል አድርጌዋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ስለዘፈን አስፍቼ ለመጻፍ
ከብዙ ጊዜ በፊት አስብ፤ አሰላስል ነበር፡፡
ለዚህ ጽሁፍ ሌላው መነሻ ምክንያት የሆነኝ፣ በጄ ቲቪ የቴሌቪዥን ጣቢያ
ሰኞ በ16/8/09 እና 23/8/09[2]
ምሽት አራት ሰዓት ገደማ በሚተላለፈው የ“ብራና” ፕሮግራም ላይ፣ ሰርጸ ፍሬ ስብሐት የተባለ ሰው ሙዚቃን(ዘፈንን) በተመለከተ አንድ
“ጥናታዊ ጽሁፍ”፣ በአንድ ሌላ ቦታ ላይ አቅርቦ የነበረውን ሲያስተላልፍ ያሳያል፤ ለሰርጸ “ጥናታዊ ጽሁፍ” መነሾ ምክንያቱ ደግሞ፣
ዮናስ ጎርፌ የተባለ ሌላ ሰው “ቤት ያጣው ቤተኛ-
ሙዚቃ፣ ሙዚቀኛነትና ኢትዮጵያዊቷ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ዘፈንን[ሙዚቃን] ባስመለከተ በጻፈው መጽሐፍ ላይ የቀረበ ነው፡፡ ዮናስ ጎርፌ ለተባለው ሰው
በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዓቃቤ እምነት ላይ የሚሠሩ ብዙዎች መልስን ስለሰጡት እርሱን ማንሳት አልፈልግም፡፡ ሰርጸ ግን፣
“ቤት ያጣ ቤተኛ” መጽሐፍን፣ “ከዚያኛው ቤት ሲሰደድ”[በእርግጥ ተሰዷል ብዬ ለማመን ብቸገርም] አዲስ ጎጆ ሊሠራለት ዳድቶ፣ ወደሚድያ
እንዲመጣ የመፈለጉ አንድምታ፣ አደገኛነቱ የቱም መንፈሳዊና ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ቅድስና የሚቀና አገልጋይ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፡፡
ለሰርጸ ፍሬ ስብሐት፣ ዮናስ ጎርፌ የጻፈውን መጽሐፍ “መደገፉና”፣
በዚያ ላይ “ጥናታዊ ጽሁፍ” ማቅረቡ አንድ ነገር ነው፡፡ የሁለቱም ሃሳብ አንድ መሆንና መደጋገፋቸው ብዙም አልደነቀኝም፡፡ ምክንያቱም
የሁለቱም ስልተ ምት “ዘፈን” ወደትውልዱ እንዴት ማስረጽ እንዳለባቸው “የተጉ” ወይም የሚተጉ ናቸውና፡፡ አሳዛኙ ክፍል፣ ሰርጸ
መጽሐፍ ቅዱስን አንስቶ ስለዘፈን የተሟገተበት አካሄድ እጅግ አሳፋሪና ኢ ሥነ ምግባራዊ ነው፡፡ በተቻለ መጠን መጽሐፍ ቅዱስ ዘፈንን
እንደማይከለክል እንጂ፣ ይከለክላል ለማለት አልደፈረም፡፡ ፈጥኜ ብእሬን እንዳነሣ ያደረገው ሌላኛውና ዋና ምክንያቴም ይኸው ነው፡፡[3]
ትርጉም
ወደትርጉም
ከመሄዳችን በፊት ማስተዋል ያለብን ሦስት መሠረታውያን ነገሮችን እጅግ በጣም በጥንቃቄ ማስተዋል አለብን፤ እኒህም፦
1.
እግዚአብሔር ሉዐላዊ አምላክ መሆኑንና የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣንን ማመን
ይገባናል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ስንል የራሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን ማለታችን ነው፡፡ ቃሉን ስናከብር ተናጋሪውን ፍጹም ማክበራችንን
ያሳያል፡፡ ስለመጽሐፍ ለማውራት ከመነሳታችን በፊት የተናጋሪውን ልዕልና አለመዘንጋት ከሥጋና ደም ያይደለ ብርቱ ማስተዋል ነው፡፡
2.
ቅዱሳት መጻሕፍት ሲተረጎሙ፣ ዋናውንና ትልቁን ግብ ክርስቶስን ማዕከል
ባደረገ፣ የሥነ አፈታትን መርሖ በተከተለ መንገድ መሆን መቻል አለበት፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉበት ዋናው ግብ፣ “ኢየሱስ እርሱ
ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል” (ዮሐ.20፥21)
ለሚለው ቅዱስ እውነት ፍጻሜ ነው፡፡ ስለዚህ ስንተረጉም ይህንን መሠረታዊ ዓላማ ባለመሳትና ባለመዘንጋት ሊሆን ይገባል፡፡
3.
እግዚአብሔርን በሚያስከብር ሕይወትና ቅድስና እንድንኖር በሚጋብዝና ከዚህም
የተነሣ ሰው እጅግ ሊጠቀምበት በሚችል መንፈሳዊ እውነት ላይ በመቆም ሊሆን ይገባዋል፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት ለሰው እንጂ በሰው ወይም ከሰው በሆነ ጥበብ አልመጡም፡፡
መጽሐፍ፣ “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ”
(2ጴጥ.1፥21) እንዲል፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን አነቃቅቶ ላጻፈው እግዚአብሔር ክብርና ፈቃድ አስማምተን መተርጎም ይገባናል እንጂ፣
እንደገዛ መንገዳችን ልንተረጉም አይገባንም፡፡ ስንተረጉምም ደግሜ እላለሁ፤ መሠረታዊውን የሥነ አፈታት መርሖ በመከተል፤ የዓውድን
“ሥልጣን” ባለመጣስ ቢሆን እጅግ መልካም ነው፡፡ ሰዎች ይህን ካላስተዋሉ እልኸኞች ሆነው፣ “እውነትን በዓመፃ ይከለክላሉ” (ሮሜ.1፥18)
ወይም በክፋታቸው እውነትን ያፍናሉ፤ እግዚአብሔርንም እንደአምላክነቱ አያከብሩትም፤ አያመሰግኑትምም፤ (ሮሜ.1፥20)፡፡ እግዚአብሔርንም
ማወቅ ጠቃሚ ላይመስላቸው ይችላል፤ (ሮሜ.1፥28)፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ራሱን እንድናውቀው በገለጠልን ልክ ልናመልከውና ልናመሰግነው
ይገባናል፡፡ አልያ ለማይረባ አእምሮ ተላልፈን ልንሰጥ እንችላለን፡፡
በእርግጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን የመተርጎም ሃሳብ እንዲህ እንደምናስበው
ቀላልና ወዲያው “ጥንቅቅ” የሚል ሥራ አይደለም፡፡ መተርጎም “ጥረትና
ከፍ ያለ ትጋትን” የሚጠይቅ የትጉሃን ሥራ ነው፤ ከዚህም ባሻገር ግን የመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ዋናና ማሠርያው ነው፡፡ በተለይም
ከእናት ቋንቋ ወደተቀባዩ ቋንቋ[ወደሚተረጎምበት ቋንቋ] ሲተረጎም፣ አቻዊ የቃል ፍቺን ማግኘት እጅግ አድካሚ ከመሆኑም በላይ፣ ብርቱ
ጥንቃቄን የሚሻ ሥራ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ቅሩብ እንጂ ፍጹም አቻዊ የትርጉም ፍቺ ላይገኝ የሚችልበት ጊዜም ሊኖር ይችላል፡፡
[4]
ይህን እውነት በትሁትና ልበ ሰፊ በሆነ መንፈስ በመቀበል፣ “ዘፈን” የሚለውን
ትርጉም በተለይም “ዘፈን” የሚለው ቃል ያለባቸው የአዲስ ኪዳን ምንባባትን ተከትለን[5]
ብንሄድ፣ “ኮሞስ” የሚለውን የግሪክ ቃል በዋናነት እናገኛለን፤ (ሮሜ.13፥13 ፤ ገላ.5፥21 ፤ 1ጴጥ.4፥3)፡፡ ይኸንኑ “ኮሞስ”
የሚለውን ቃል፣ የግሪኩ ኮይኔ መዝገበ ቃላት በሦስት ዓይነት መንገድ ተርጉሞት እናገኘዋለን፤ አያይዘንም “ዘፈን” የሚለውን ቃል
የተለያዩ መዝገበ ቃላት የተረጎሙትን ትርጉም አብረን እንናቀርባለን፡፡
1.
በጥንት ግሪክ ለወይን አምላክ በሚደረግ ታላቅ ግብር ላይ ተሰልፎ መዞር፣
መፈንደቅ፣ መጨፈር፣ መጯጯኽ፣ መፈንጠዝ፣ ኢ ሥነ ምግባራዊና ገደብ የለሽ በኾነ የአልኮል መጠጥና ገደብ የለሽ በኾነ የአልኮል መጠጥና
በምግባረ ብልሹነት እርካታ ለማግኘት የሚደረግ ወሲባዊ ጭፈራ( ... Drinking parties involving
unrestrained indulgence in alcoholic beverages and accompanying immoral
behaviour, - ‘orgy, revelling, carousing.)
2.
በአማልክት (በጣዖታት) ፊት በቡድንና በግል የሚደረግ ፈንጠዝያ፣ ዝሙትና መጠጥ ባካተተ መልኩ የሚደረግ ጭፈራ፣
3.
በቡድን በተደራጀ መልኩ በተለያየ ሁኔታ የሚደረግን አደባባያዊ ትርኢት
መልክ ያለው የመንደር ክብር በዓል፣ ጭፈራ፣ ዘፈን፣ ግጥም፣ ዜማ፣ መሽከርከርን ... የሚያመለክት ትርጉም ያለው ነው፡፡
በ1886 ዓ.ም የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ “ማሶልሶል” ሲለው፣ በ1954
ዓ.ም የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ዘፈን፣ ዘፋኝነት ብሎ አስቀምጧል፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተረጎመችውና
በስሟ ያዘጋጀችው መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በገላ.5፥21 እና በ1ጴጥ.4፥3 ላይ ያሉትን ዘፋኝነትን ጨርሳ አውጥታቸዋለች፡፡ ይህ ያደረጉበት ምክንያታቸው ግልጥ አይደለም፤ ነገር
ግን ጨርሶ ቃሉ “ቢወጣ” በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትነቱን ፈጽሞ ሊተው አይችልም፡፡ ቃሉ ከጥንት ያው ነውና፡፡ [6]
የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳተመው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ “ዘፈን”ን
ሲተረጉም፦ “በቅኔና በግጥም ከልዩ ልዩ መሣሪያ ጋር እየተቀነባበረ የሚቀርብ የደስታ ምልክት፡፡ ዘፈን፦ 1. በልደት ቀን (ኢዮብ 21፥11-12 ፤ ማቴ. 14፥6) 2. በሰርግ ቀን (ኤር 31፥4 ፤ ማቴ.11፥17) 3. በድል በዓል ቀን (ዘጸ.15፥21 ፤ 21 ፤ መሳ.11፥34 ፤ 1ሳሙ.18፥6) 4. በመንፈሳዊ በዓል ቀን (2ሳሙ.6፥14)
ይደረጋል፡፡ ከዚህም ሌላ በልዩ ልዩ የደስታ ቀን ይዘፈናል፤ (ሉቃ.15፥25)፡፡ በእስራኤል የአምልኮት ሥርዓት ዘፈን (ማኀሌት) ትልቅ ቦታ ይይዝ ነበር፤ (መዝ.149፥3 ፤ 150፥4)፡፡ ነገር ግን ባዕድ አምልኮትንና ዝሙትን የሚያስከትል ዘፈን አልተፈቀደም (ዘጸ.32፥6፤
19 ፤ ማር.6፥21-22)፡፡ ሐዋርያት ዘፈን የማይገባ መሆኑን ተናግረዋል፤ ሮሜ.13፥13 ፤ ገላ.5፥21፡፡)” [7]
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም[8] “ዘፊን፤
ኖት፤ (ዘፈን ይዘፍን ይዝፍን፡፡ ዐረብ)፤ መዝፈን መወዛወዝ፤ ማሸብሸብ ማጋፈት መዝለል መፈንጨት፡፡ … ዘፋኒ፤ (ኒት፤ ንያን፤
ያት)፤ የሚዘፍን ዘፋኝ፤ ተወዛዋዥ፡፡ ዘፈን፤(ናት)፤ በቁሙ ዝላይ እስክታ፡፡”[9]
የደስታ ተክለ
ወልድ መዝገበ ቃላትም “ዘፈን”[10] የሚለውን፣
“ዘፈን፤ (ዘፊን ዘፈነ)፤ ቀነቀነ አወረደ ግጥም ገጠመ፣ አዜመ፣ አንጐራጐረ፣ ዘለለ፣ ተውረገረገ፡፡” አሁንም ዘፈነ፤ ተንቀጠቀጠ ተንዘፈዘፈ፡፡ ዘፋኝ(ኞች)፤ የዘፈነ የሚዘፍን፤ አውራጅ አንጐራጓሪ
ዘፈን ወዳድ(መዝ.፹፯፥፯)” በማለት ሲያስቀምጡት፣ ገላ.5፥21 ላይ የተቀመጠውን ዘፋኝነት የሚለውን ሃሳብ ደግሞ፣ “መጽሐፍ ግን መሶልሶል[11][ሶለሶለ - አንሶለሶለ፣ አዞር፣ አንቀዠቀዠ፣ አንቀለቀለ መንሶልሶል፣ መዞር፣ መንቀዥቀዥ] ይላል” በማለት ጥቅሱን ጠቅሰው አስቀምጠውታል፡፡
የኦሮሚኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም፣
“Sirba(Dance) - Walaloo, Weedduu, faarfannaa fi meshaalee faarfannaa adda addaa
waliin qindeessudhaan gammachuu ibsuudhaaf sochii qaama gochuu, shuubbisuu
yookiin quruphisuu[12]
dha. Macaafa Qulqulluu keessatti namoonni yommuu ayyaana guyyaa dhalata isaanii
kabajan (Iyo.21:11, 12; Mat.14:6), guyyaa cidhaa (Er.31:4; Mat.11:17), guyyaa
injifannoo (Ba’u.15:20, 21; Abo.11:34; 1Sam.18:6), guyyaa ayyaanni hafuuraa
kabajamu (2Sam.6:14-16), guyyaa gammachuu garaa garaa (Luqa.15:25), ni sirbu
turan. Sabni Israa’el sirba waaqeeffannaa ormaa fi xuraa’ummaa foonitti geessu
akka hin sirbinne dhowwameera (Bau.32:6, 19; Mar.6:21, 22); sirbi akkanaa kunis
cubbuu dha, (Rom.13:13; Gal.5:21).[13]
ትርጉም፦ “ዘፈን፤ ግጥም፣ እንጉርጉሮ፣ መዝሙርና ከተለያዩ
የዜማ መሣሪያዎች ጋር በማቀናጀት ደስታን ለመግለጥ ሰውነትን ማንቀሳቀስ፣ መወዛወዝ፣ መዝለል መፈንጨት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
ሰዎች የልደት በዓላቸውን ለማክበር፣ (ኢዮ.21፥11 ፤12 ፤ ማቴ.14፥6)፣ በሰርግ ቀናቸው (ኤር.31፥4 ፤ ማቴ.11፥17)፤
በድል ቀን (ዘጸ.15፥20፣ 21 ፤ መሳ.11፥34 ፤ 1ሳሙ.18፥6)፣ በመንፈሳዊ በዓል ቀን (2ሳሙ.6፥14-16)፣
በተለያዩ የደስታ ቀናት (ሉቃ.15፥25) ይዘፍኑ ነበር፡፡ በእስራኤል ሕዝብ ባዕድ አምልኮትንና የሥጋ ፍትወትን የሚያስከትል ዘፈን እንዳይዘፍኑ ተከልክለዋል፤ (ዘጸ.32፥6፤
19 ፤ ማር.6፥21፤ 22)፡፡ እንዲህ ያለውም ዘፈን ኀጢአት ነው፤ (ሮሜ.13፥13 ፤ ገላ.5፥21)፡፡”
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
[2] በሁለቱም ቀን የቀረበው ተመሳሳይ ነገር ነበር፡፡ “ምናልባት ደጋግሞ በማቅረብ፣ ሃሳቡን በሕዝብ ልቡና
ለማስረጽ ታስቦ ይሆን?!”[ማን ያውቃል? … እግዚአብሔር ግን ልብና ኩላሊትን ይፈትናልና የሰውን መንገድ ሁሉ ያውቃል፤ (መዝ.11፥20
፤ 17፥10 ፤ 20፥12 ፤ ራእ.2፥23)፡፡
[3] ይህን ጽሑፍ ሌሎች
ወንድሞች እንዲያዩትና አስተያየት እንዲሰጡበት[በተለይ ሁለቱ ሙሌዎች] ካደረግሁ በኋላ፣ አንድ ሌላ አስነዋሪ ነገር ጆሮዬን ጭው
አድርጎት ነበር፤ “ቴዎድሮስ ካሳሁን” የሚባል ዘፋኝ ስለሚያወጣው ዘፈን፣ ያሬድ አደመና ዘመድኩን በቀለ የተባሉ ሌሎች “ቤተ ክርስቲያንን
እናገለግላለን” የሚሉ ሰዎች ደግሞ፣ ከአገልጋይነት ወርደው፤ ከመንፈሳዊነት ተዘልለው ወዲያ ወጥተው፣ ዘፋኙን በቀጥታ “ሲደግፉ”
አስተውያለሁ፡፡ እንግዲህ መጽሐፍ፣ “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው
ያስተውል፥” (ማቴ.24፥15) እንደሚል፣[በእርግጥ ግን በትክክል የክርስቶስ ፍቅር ቢገባቸው ዘመናቸውን ለክስ፣ ለስድብ፣ ለምድራዊ
ብልጥግና፣ እንዲህ ላለ ነውርም አሳልፈው ባልሰጡ] በአንድ ወቅት “ከእኛ በላይ አገልጋይ ላሳር” የሚሉትም ከአለሙ ክፋት ተደምረዋልና
በአገባቡ ማስተዋል ይገባናል፡፡
[7]
የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 6ኛ እትም፤ 1992 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ባናዊ ማተሚያ ቤት፡፡
ገጽ.215
[8] የእርሱን ሃሳብ ያልደገፉለትን
“ሊቃውንት” አባቶች ሥራን አቀራረቡና አጠቃቀሱ ሌላው የሰርጸ ኢ ሥነ ምግባራዊና አሳዛኝ ገጽታ ነው፤ ለምሳሌ አለቃ ኪዳነ ወልድ
ክፍሌን በመዝገበ ቃላቸው ላይ ያሉትን በአግባቡ ካለመጥቀሱም ባሻገር፣ በንግግር ቅላጼው ጭምር ሳይቀር “ንቀት” ባዘለ ንግግር
“ምናምን” የሚል ጸያፍ ቃል ተጠቅሟል፡፡
[13] Kabbadaa Bakaree, Galmee jechoota Macaafa Qulqulluu Afaan
Oromoo; 2016; Addis Ababa, Rehobot Printers, fuula 230
Tebarek
ReplyDeleteGooftaan umrii siif yaa dheressu. jabaadhu boo ...
ReplyDeleteመተርጎም “ጥረትና ከፍ ያለ ትጋትን” የሚጠይቅ የትጉሃን ሥራ ነው፤ ከዚህም ባሻገር ግን የመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ዋናና ማሠርያው ነው፡፡ ewnet new!
ReplyDelete