የጌታ ጾም መታሰቢያ የመጨረሻው ሳምንት ስያሜ ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡
በዚህ ሳምንት ከምን ጊዜውም በላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ “ወገኖቹ” የደረሰበት ጸዋተወ መከራ ከወንጌላት፣
ከግብረ ሕማማትና ከሌሎችም መጻሕፍት እየተውጣጡ ይነበባሉ፤ ሕማማቱንም ማዕከል ያደረጉ ሥርዓተ አምልኮዎች በጸሎት፣ በዝማሬ፣ በንባብና
በቅዳሴ ይቀርባሉ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የጌታን ሕማም የጌታ እራት በቀረበበት ጊዜ መናገርና መመስከር
እንዳለብን “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና፤”
(1ቆሮ.11፥26) በማለት ይናገራል፡፡ ጌታ ኢየሱስም ከሙታን መካከል ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “እርሱም፦ ከእናንተ ጋር
ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው፡፡
በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን
ከሙታን ይነሣል፥” (ሉቃ.24፥46) አላቸው፡፡
ጌታ ኢየሱስ መከራ እንደሚደርስበት በነቢያት ትንቢት እንደተነገረለት
እንዲሁ(ኢሳ.52፥13-53፥12)፤ ከመሰቀሉ በፊት ራሱም በአንደበቱ ደጋግሞ ተናግሯል፤ (ማቴ.8፥20 ፤ 16፥21 ፤ ማር.8፥31
፤ 9፥1 ፤ 9 ፤ 10፥33 ፤ 14፥21)፡፡ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ያስተዋሉትና “መከራ ሊቀበል ይገባዋል” ብለው ያመኑት፣
ከሙታን ትንሣኤ በኋላ እርሱ ራሱ “መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን በከፈተላቸው” ጊዜ ነው፡፡ አስተውሉ! የክርስቶስ መከራውንና
ሕማሙን፣ ስለዚህም የሚመሰክሩትን የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት በትክክል ለማስተዋል አእምሮችንንና ውስጣዊ ዓይናችን በመንፈስ ቅዱስ
አቅም መከፈትና ማየት ሲችል ብቻ ነው፡፡
ቅዱስ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታ በተሰቀለ ጊዜ፣ ፊት ለፊት ቆመው ካዩ
ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፤ (ዮሐ.19፥26)፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነገረው ከዚያች ቀን ጀምሮ ቅዱስ ዮሐንስ የጌታን
ሕማምና መከራ በትክክል በዘመኑ ሁሉ በማሰብ፣ ፊቱ ሳይፈታ፤ ከአለም ሳቅና ተርታ ነገር ፈጽሞ በመራቅ ኖሯል፡፡ እውነት ነው! ብዙ
ቅዱሳንና ሰማዕታት በዚህ ዓለምና ኃጢአት ላይ እንዲጨክኑና ፊታቸውን ፈጽመው በማጥቆር እንዲሸሹ፤ ብሎም እንዲጋደሉ ያደረጋቸው የክርስቶስ
የመከራው ጉልበትና የኢየሱስ የሕማሙ አቅም ነው፡፡ ለእውነተኛ ክርስቲያን የክርስቶስ ሕማም ለማናቸውም መንፈሳዊ ሥራ አዲስ ጉልበትና
ልዩ አቅም ነው፡፡
የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የነገረ ድኅነት መሠረት ነው ማለት፣ ለአይሁድም
ለአሕዛብም ጥበብ አልባ ሞኝነት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ … እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ
ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥” (1ቆሮ.1፥23)፡፡ አይሁድ የጠበቁት መሲሕ በጦር ወይም በተአምራት “ለእስራኤል መንግሥትን እንዲመልስ”
(ሐዋ.1፥6) ሲሆን፣ አሕዛብ ደግሞ የተከበረና ታላቅ የሆነ ሰው ፈጽሞ ሊዋረድና ዝቅ ሊል አይገባውም በማለታቸው፣ መሲሑ በቀዳማይ
ምጽአቱ አገልጋይ ሆኖ በመምጣቱ ከእጅግ ጥቂቶች በቀር በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡
በዛሬውም ዓለም ዝቅታና አገልጋይነት ሥፍራ የሌላቸው ነገሮች ሆነዋል፤
መንፈሳውያን በሚባሉ ወገኖች ዘንድ ሳይቀር በትዕቢት ቀና ቀና ማለት፣ ስለራስ ብዙ በማውራት መድከም፣ በራስ መመካት፣ መብትንና
ጥቅምን ቀድሞ ማስላት፣ ለእኔ ቅድሚያ ሊሰጠኝ ይገባል፣ ለራስ የሚጠቅመንን ቀድመን ማየት … ዛሬ ላይ ጤናማና ትክክለኛ እይታ እንደሆነ
ታምኖበታል፡፡ ክርስቶስ ግን እንዲህ አላስተማረንም፤ እርሱ በዓለም
ፊት ሞኝ የተባለውን፣ ነገር ግን ያስተማረን በሰማያት ዓለም የሚያሸልመውን ጥልቅ ምስጢር ነው፡፡ “ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ
ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም
ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ፡፡ ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው
ፈቀቅ አትበል፤”(ማቴ.5፥39-42)፡፡ ይህን ቃል ዛሬ ዛሬ ድራማና ቀልዶች መካከል እንጂ በሕይወት ከማንተገብራቸው ከሆኑ ዓመታት
ተቆጥረዋል ያስደፍራል፡፡
ይህንን እውነት ለመረዳትና ለማስተዋል፣ ከብልጽግና ወንጌል በመራቅ ስቁሉን
ኢየሱስንና መከራ ተቀባዩን ክርስቶስ በትክክል ራስን ክዶ መከተል ይጠይቃል፡፡ ጌታ ኢየሱስን ስለበረከቱና ስለሰጠን ዘላለማዊ ሕይወት
ብቻ አንከተለውም፤ በመስቀል ላይ ደም ግባት አልባ ሆኖ (ኢሳ.53፥2-5)፣ በሰው ሁሉ ፊት እስኪናቅና እስኪሾፍበት (ሉቃ.23፥35-39)፣
እስኪተፋበት ድረስ(ማር.14፥65) ስላገኘው መከራው ሁሉ በፍቅርና በእውነት እንወደዋለን፤ እናፈቅረዋለን፤ እናመልከዋለን፤ እንሰግድለታለንም፡፡
ትልቅ ሞኝነት ቢሆንም፣ ይህንን ዓይተንና ሰምተን እንደተከተልነው ዓለም ሁሉ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡
ሕማማቱ በዘመናችን ሁሉ የማይዘነጋ ሕያው ትዝታችን እንጂ፣ በዓመት ውስጥ
ባለ አንድ ሳምንት ብቻ የምናስበውና የምናሰላስለው አይደለም፤ የጌታን
እራት በምንቆርስበትና በምንቀበልበት በማናቸውም ጊዜ “የጌታን ሞት መናገር አለብን”፡፡ አዎን! ጌታ ኢየሱስ እኛን ስለማዳን በገዛ
ወገኖቹ ጽኑዕ መከራን እንደተቀበለ፣ እንደተዋረደ፣ እንደሞተ በሦስተኛው ቀን ከሙታን መካከል እንደተነሣ፣ ይህንን ሳንፈራ ለዓለሙ
ሁሉ የምንመሰክረው ዘወትርና ሳናቋርጥ ነው፡፡ ጌታችን ዳግመኛ መጥቶ እስኪወርሰንና እስኪጠቀልለን ድረስ የጌታን እራት(ቅዱስ ቁርባኑን)
መካፈላችንና መቁረሳችን ግድ ነው፤ በምንቆርስበትም በማናቸውም ሰዓት መከራውንና ሕማሙን እናስባለን፤ እንዘክራለን፤ እናወራለን፤
እንመሰክራለን፡፡ በእርሱ ሞትና ሕማም፤ የትንሣኤውም ኃይል ከዘለዓለም ፍርድ፤ ከእግዚአብሔር ቁጣ ማምለጣችንን፣ የኃጢአትን ሥርየትም
እንደተደረገልን ሕያዋን ምስክሮች ነን እያልን ለዓለሙ ሁሉ እናውጃለን፡፡
አዎን! ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን፣ “እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ”
(ሉቃ.24፥48) እንዳላቸው “እኛም የዚህ ነገር ዋና ምስክሮች ነን”፡፡ የክርስቶስ ሕማምና ሞት በመንፈስ ቅዱስ ዓይንና ጆሮ፣
ችንካሮቹን አይተናል፣ ተጠማሁ ብሎ የሲቃ ድምጽ ሲያሰማ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ሰምተናል፡፡ እናም ክርስቶስ ስለእኛ እንደሞተና
እንደተነሣ የማናፍር፤ የማንፈራም ምስክሮች ነን፡፡ ይህንንም ምስክርነት የምንገልጠውና የምናጉተመትመው፣ በሕይወታችንም የምንገልጠው
በሕማማቱ ሰሞን ብቻ አይደለም፤ በዘመናችን ሁሉ እንጂ፡፡ ጌታችን እስኪመጣ ይህን ድንቅ ምስክርነት ከመናገር ቸል አንልም! ልክ
ጾሙ ሲፈታ ወይም ሲጨረስ፣ ለኃጢአት ራሳችንን ስድና ፈት አናደርግም፤ ጌታችን በደሙ የገዛን ዘመናችንን ሁሉ ነውና፡፡
ስለዚህ ሞቱንና ሕማሙን፤ ትንሣኤውንም ለመናገር ሁለት ታላላቅ ምክንያት
አለን፤
1.
ጌታ እስኪመጣ ድረስ እራቱን በቆረስን ጊዜ ሁሉ ሞቱንና ሕማሙን፤ ትንሣኤውንም
እናስባለን፡፡ በጥንት የእስራኤል ልማድ በየዓመቱ የፋሲካን በግ አርደው ሥርዓቱን ሲፈጽሙ ከቤተሰቡ አንዱ ልጅ ተነሥቶ “ይህ ምንድር
ነው?” ይላል፤ አባትም “ይህማ ሞት ተገስጾ እኛ የእግዚአብሔርን ምሕረትና እውነት ለመናገር የተረፍንበት መታሰቢያ መሥዋዕት ነው”
ይላል፡፡ እውነትም የፋሲካው በግ መታሰቢያ እንዲያ ነበር፡፡
2.
ሕማሙንና ሞቱን የምናስብበትና የምንዘክርበት፤ የምንመሰክርበት የጌታ እራት፣
ተስፋችን የሆነውን ዳግም ምጽአትንና (1ተሰ.4፥13 ፤ ቲቶ.2፥13) ከመጣም በኋላ ከእርሱ ጋር የምናሳልፈውን የዘለዓለም ደስታ
የምናስብበት ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ እርሱ ከመጣ በኋላ ግን እራቱን አንቆርስም፤ ነገር ግን በሰማያት ከራሱ ከጌታ ኢየሱስ ጋር የምንቆርሰውና
የምንመገበው “የበጉ ሠርግና ግብዣ” የተባለ ልዩና አስደናቂ ጉባኤ አለንና፤ (ማቴ.26፥29 ፤ ማር.14፥25)፡፡
“ … የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን
ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡ … እርሱም፦ ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም፦
ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ፤” (ራእ.19፥7 እና 9) አዎን! ከእግዚአብሔር ጋር ከበጉ ሕማምና መከራ፣ ከሙታን
መካከል በመነሣቱ ምክንያት እንዲህ ያለ ጥብቅ ግንኙነት አለን፡፡ ደስ ይበላችሁ! ሕማማቱ በደስታ የምናለቅስበት ብቻ ያይደለ፣ ታርዶ
የተሠዋው በግ ያዘጋጀውን ግብዣና ሠርግ ተስፋ የምናደርግበት ነው፡፡ ደስ ይበላችሁ! ሕማሙንና ሞቱን፣ ከሙታን መካከል መነሣቱንም
በልባችሁ እያጉተመተማችሁና እየመሰከራችሁ እራቱን በእውነትና በፍቅር፣ ከኃጢአት ሁሉ ነጽታችሁ በመስማማት የምትቆርሱና የምትፈትቱ፣
የምትቀበሉ ሆይ! በሰማያት ውብና አስደናቂ ልብን የሚመላና አእምሮን የሚያልፍ ሠርግና ግብዣ አላችሁና፡፡ አሜን፤ ስቁሉና አገልጋዩ
ኢየሱስ ሆይ! ችንካርህን እያሳየህ በግርማ መለኮትህ ናልን!
Yedengel Lege Geta Eyesus Krstose Elet Elet betebeb Slemiyasadegeh Zemeneh hulu Egeziyabhern Bewnet Bemagegel Yeleke!!! Wendeme.Enkwan Adersek.!!!30,60,100 frea Yafra.
ReplyDeleteደስ ይበላችሁ! ሕማማቱ በደስታ የምናለቅስበት ብቻ ያይደለ፣ ታርዶ የተሠዋው በግ ያዘጋጀውን ግብዣና ሠርግ ተስፋ የምናደርግበት ነው፡፡ ደስ ይበላችሁ! ሕማሙንና ሞቱን፣ ከሙታን መካከል መነሣቱንም በልባችሁ እያጉተመተማችሁና እየመሰከራችሁ እራቱን በእውነትና በፍቅር፣ ከኃጢአት ሁሉ ነጽታችሁ በመስማማት የምትቆርሱና የምትፈትቱ፣ የምትቀበሉ ሆይ! በሰማያት ውብና አስደናቂ ልብን የሚመላና አእምሮን የሚያልፍ ሠርግና ግብዣ አላችሁና፡፡ amen amen amen
ReplyDelete