Please read in PDF
አይሁድ በይሁዳ ምድር በቢታንያ መንደር ለግድያና ለወገራ ጌታ ኢየሱስን ይፈልጉ በነበረበት ወቅት፣ አልዓዛር በጠና መታመሙን ሰማ፡፡ ወዳጁ አልዓዛርን ስለእግዚአብሔር ክብር ሊያስነሣው ደቀ መዛሙርቱን “ወደይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው፤ (ዮሐ.11፥8) ይህንን ሲል ሁሉም ፈርተው ነበር፤ ቶማስ ግን “ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት፦ ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” በማለት ደፋርና የማይፈራ ሰው መሆኑን አስመሰከረ፡፡
አይሁድ በይሁዳ ምድር በቢታንያ መንደር ለግድያና ለወገራ ጌታ ኢየሱስን ይፈልጉ በነበረበት ወቅት፣ አልዓዛር በጠና መታመሙን ሰማ፡፡ ወዳጁ አልዓዛርን ስለእግዚአብሔር ክብር ሊያስነሣው ደቀ መዛሙርቱን “ወደይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው፤ (ዮሐ.11፥8) ይህንን ሲል ሁሉም ፈርተው ነበር፤ ቶማስ ግን “ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት፦ ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” በማለት ደፋርና የማይፈራ ሰው መሆኑን አስመሰከረ፡፡
በቤተ ክርስቲያን ቀኖና የዛሬው እሁድ ዳግማይ ትንሣኤ ወይም ዳግም ትንሣኤ
ተብሎ ይጠራል፡፡ ከስምንት ቀን በፊት ለደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ውስጥ ሳሉ ተገለጠላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ልክ ጌታ ኢየሱስ
ከሙታን መካከል እንደተነሣ አንድ ክስ በአይሁድ ሽማግሌዎች ቀርቦባቸዋል፡፡ “… ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት” (ማቴ.28፥11)
የሚል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ክስ የተነሣ በጥብቅ ይፈለጉ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ እናም ይህን ክስና “አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹን
ዘግተው” (ዮሐ.20፥19) ተቀምጠው ነበር፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በሩ ዝግ ሳለ፣ ጌታ ኢየሱስ እንዴት እንደገባ
አይነግረንም፡፡ ነገር ግን በሩ ተዘግቶ ሳለ ጌታ ኢየሱስ በመካከላቸው በአስደናቂ ሁኔታ ተገኘ፡፡ ቃሉም “ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥
ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ” እንደአይሁድ ልማድ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ እንደተናገራቸው ይመሰክራል፡፡ በፍጹም ሰውነቱ
ሥጋ የለበሰ ጌታ ቢሆንም፣ እርሱ ከአብ የተካከለ ፍጹም አምላክም ነው፡፡
የጌታ ኢየሱስ ሰላም በቃል ሊገለጥ የማይችል ልዩና ድንቅ የልብና የነፍስ
እረፍት ነው፤ እርሱ ራሱም፣ “እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” (ዮሐ.14፥27) በማለት በማይታበል አምላካዊ ቃሉ አረጋግጦልናል፡፡
የእርሱ ሰላም ውጫዊና በቁሳዊ ነገር ላይ ያልተመሠረተ ሲሆን፣ በማናቸውም የመከራና የስደት ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ እንኳ በውስጣችን
የሚኖርና የማይጣፋ ዘላለማዊ ሰላም ነው፡፡ እንዲህ ያለውንም ሰላም ማግኘት የሚቻላቸው፣ “በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” እንዲል በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የጸደቁና በእርሱም የሚኖሩ ብቻ ናቸው፤ (ሮሜ.5፥1)፡፡
ለደቀ መዛሙርቱ
ለመጀመርያ ጊዜ እንዲህ ጌታ ኢየሱስ በተገለጠ ጊዜ ቶማስ አብሯቸው አልነበረም፡፡ ከስምንት ቀን በኋላ ሲገለጥ፣ ቶማስ ከደቀ መዛሙርቱ
በአንድነት ነበር፡፡ ቶማስ ምንም የማይፈራና ደፋር ቢሆንም፣ የጌታን ትንሣኤ በተመለከተ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ
ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም” (ዮሐ.20፥25)፣ ብሎ እስከመናገር የተጠራጠረ ሰው ነው፡፡
በእርግጥ ጌታ ኢየሱስ በሥጋ በሞተ ጊዜ እስከሚያዩት ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ተጠራጥረውና[አንዳንዶቹ አይተውትም እንኳ፤ ማቴ.28፥17]
ተስፋ ቆርጠው ነበር፤ (ማቴ.28፥17 ፤ ማር.16፥11 ፤ 14 ፤ ሉቃ.24፥10-11 ፤ 13 ፤ ዮሐ.21፥2)፡፡
ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ በከባድ ጥርጣሬና አለማመን ውስጥ ቢሆኑም እንኳ፣
ጌታ አልታዘባቸውም ወይ በከባድ ተግሳጽ አልተናገራቸውም፡፡ ይልቁን በበዛ ፍቅር ተገናኛቸው፡፡ ስለዚህም ከስምንት ቀን በፊት በተገለጠበት
መንገድ እንደገና በዚያው ቤትና በዚያው አገላለጥ ቶማስ ባለበት ጉባኤ በመካከላቸው ተገለጠ፡፡
ቶማስ፣ ጌታ ኢየሱስ ሲገለጥ በልቡ ምን አስቦ ይሆን? ምንስ ስሜት ተሰምቶት
ይሆን? ያ ደፋርና አይፈሬ ሰው ልቡ አልራደ፤ አላፈረ ይሆን? ጫፍ የነካው ጥርጣሬውስ ተኖ ጠፍቶ ይሆን ወይስ …? ብቻ ልብንና
ኩላሊትን ፈትኖ የሚያውቀውና የሰዎችን የልብ ሃሳብ የሚያውቀው ጌታ ኢየሱስ የቶማስን የልብ ጥርጣሬ አውቆ፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣና
እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው” (ዮሐ.20፥27)፡፡
ጌታ ኢየሱስ
አምላክ ነው፤ አምላክ ስለሆነም የእያንዳንዳችንን የልባችንን ሃሳብና መንገድ ያውቃል፤ (ማቴ.9፥4 ፤ 12፥25 ፤ ሉቃ.6፥8 ፤
9፥47፤ 11፥17 ፤ ዮሐ.2፥25 ፤ 6፥61 ፤ 64 ፤ 13፥11)፡፡ ደግሞ አዳኝና መድኃኒት ስለሆነም የበዛ እድልና የተትረፈረፈ
የንስሐ ዘመን ሳይሰጠንና መንገድ ሳያበጅልን በአምላክነቱ ብቻ አይፈርድብንም፡፡ ፍርድ እንግዳ ጠባዩ ነው፤ (ኢሳ.28፥21) ማዳንና
ሰዎች ወደንስሐ እንዲመለሱ ማድረግ ግን የመጣበትና ልዩው ገንዘቡ ነው፡፡
ቶማስ የጌታ
ኢየሱስ ጐኑን ስለመንካቱና ስለመዳሰሱ ወንጌሉን የጻፈልን ዮሐንስ አልገለጠልንም፤ ዳሩ ቶማስ ጌታን ፊት ለፊት ዓይቶታል፤ ድምጹንም
ሰምቷል፤ ይህ ለቶማስ በቂና ከበቂ በላይ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣም ጌታ ኢየሱስን “አምላኬና ጌታዬ” ብሎ ተጣራ፡፡ ከሐዋርያት መካከል
ጌታ ኢየሱስን “አምላኬ” ብሎ የጠራው የለም፡፡ ቶማስ ግን “አምላኬ” ብሎ ጠራው፡፡ ያውና የሰማው ነገር ከሰማቸውና ካያቸው ነገሮች
ሁሉ ትልቅና ወደር የሌለው ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ልዩና ድንቅ በሆነ መንገድ ስለተገለጠለት የተናገረው ታላቅ ምስክርነት ነው፡፡ በእርግጥም
ጌታ ኢየሱስን በትክክል ያየች ዓይንና የሰማች ጆሮ ከመደነቅና ከመገረም፤ እጅን በአፍ ከመጫን ባለፈ ልባዊና በማንም ፍጡራዊ ኃይል
ሊገደብ የማይችል ታላቅ ምስክነት አላት፡፡
ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከጌታ ኢየሱስ ጋር ቢቆይም፣ ብዙ ተአምራትና ድንቆችን
ቢመለከትም ቶማስ ለማመን እጅግ በጣም ዘግይቷል፡፡ ጌታ ግን በፍቅር ወቀሰው እንጂ በብዙ አልተቆጣውም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ልጁን
ወደምድር ሲልክ እጅግ የገለጠው ጥልቅ ፍቅሩንና የማዳን ክንዱን እንጂ ቁጣውን አይደለም፡፡ ቁጣውን ግን በፍጻሜው ዘመን ባላመኑትና
ልጁን ባለማመን ልባቸውን ባደነደኑት ላይ እንደሚያፈስ እጅግ የተገለጠና የማይቀር ነው፡፡
ቶማስ ልቡን በጥርጣሬ ማጽናት አልነበረበትም፡፡ ይልቁን ከእርሱ ዘመን በኋላ የሚመጡ እልፍ አዕላፍ አማኞች ጌታ ኢየሱስን በእምነት
እንጂ በአካል አያዩትም ወይም ቶማስ እንዳየውና እንደሰማው ላያዩትና ላይሰሙት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንደቶማስ ባያዩትና ባይሰሙትም
በእምነት በእርሱ የሚያምኑበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ለእኒህ አማኞች የሰሙትንና ያዩትን የሚመሰክሩላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ዋና ምስክሮቻቸው
ናቸው፤ “እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን”
(2ጴጥ.1፥18) እንዲል ከእርሱ[ከጌታ ኢየሱስ] የሰሙትን ቃል የሚናገሩንን እነርሱን ቃልና ምስክርነት የሚያምኑ ሁሉ ብሩካንና
ብጹአን ናቸው፡፡ ቢዘገይም በክርስቶስ እንደጸጋው ባለ ጠግነት መጠን ቶማስ ምርጡ ሐዋርያ ሆኗል፡፡ ወዳጆቼ! ዘመን የተጨመረልን
ለንስሐና እንድንመለስ ነው፤ ተመልሰንም ታማኝ የወንጌሉ ባላደራዎችና ምስክሮች እንድንሆን ጭምርም፡፡
ጌታ ኢየሱስን በዓይኖቻችን እንደቶማስ ባናየውና ባንሰማውም፣ ነገር ግን አረፋፍደን
መጥተን ክርስቶስን አምነን በተጠመቅን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ለልባችንና ለመንፈሳችን መስክሮልናል፤ (ሮሜ.8፥16)፡፡
እንኪያስ የጸጋውንና የትንሣኤውን ወንጌል በፍቅርና በቅንነት ለመመስከር ትጉ! ጸጋ ይብዛላችሁ አሜን፡፡
ጸጋውንና የትንሣኤውን ወንጌል በፍቅርና በቅንነት ለመመስከር ትጉ! ጸጋ ይብዛላችሁ አሜን፡፡ amen
ReplyDelete