Sunday, 2 April 2017

ኒቆዲሞስ - ለሕጉ እውነት የሚሟገት ጻድቅ! (ዮሐ.7፥51)

Please read in PDF

“ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?”
    ነቢያት ለሕጉ ቀናተኞችና ሕጉ እንዲተገበር የሚተጉ ከእግዚአብሔር ለሕዝቡ የተላኩ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተነገራቸውንና በተለያየ መንገድ የተቀበሉትን (ዕብ.1፥1)፤ በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚታዘዙትን (ኤር.1፥7) የትንቢት ቃል ሸክም ከእግዚአብሔር በተላኩ ጊዜ (ኤር.1፥4 ፤ ሉቃ.3፥2) ሳይሸራርፉ፤ ሳይቀንሱና ሳይጨምሩ እንዲናገሩ ይገደዳሉ፡፡ በዋናነት ነቢያት ራሳውና ሕዝቡ እንደሕጉ እንዲኖሩ ትልቅ ሥራን ይሠራሉ፡፡ ደጋግመውም የሕጉን መጽሐፍ ያውጃሉ፡፡ ከዚህ የበለጠ ትልቅና ዋና ሥራም የላቸውም፡፡

  ከዚህም ባሻገር፣ ጌታ እግዚአብሔርም ሕግ ሲላላ ሕዝብ ወደተላላነት እንደሚያደላ አስቀድሞ ስለሚያውቅ መሪዎችና አስተዳዳሪዎችን እንደወደደው ይሾማል፡፡ የአይሁድ መምህራንም የተጠሩበት ዋና ዓላማም ይህ ነበር፤ የሕዝቡ መሪና የሕግ መምህራን እንደመሆናቸው መጠን ሕጉን በመጠበቅ ለሕዝቡ ትልቅ ምሳሌ በመሆን፣ ሕዝቡን ያስተምራሉ፤ እንዲጠብቁም ያደርጋሉ፡፡ ዳሩ፣ በአንድ ወቅት በሕዝቡ መሪዎችና በሕጉ መምህራን መካከል ጌታ ኢየሱስን በተመለከተ ትልቅ ክርክር ሆነ፡፡ ለሕዝቡ ጥቂቱን እንጀራና ዓሳ ለብዙ ሺሆች በመመገቡ ምክንያት፣ ከመከበርና ከመደነቅ ይልቅ ለመገደል በቂ ምክንያት ሆነ፡፡

      የሰው ጠባይ ለኃጢአትና ለራሱ ኅሊና ተላልፎ ሲሰጥ(ሮሜ.1፥20 ፤26) መልካሙ ነገር ርኩስ፤ ርኩሱ ደግሞ ተወዳጅና ተፈላጊ፤ ትክክልም ይሆናል፡፡ ዛሬ በዘመናችን መልካሙ ነገር ረክሶ ርካሹ ለምን የተፈለገና የተወደደ ይመስላችኋል? ለገዛ መንገዳችንና ፈቃዳችን ተላልፈን ተሰጥተን ይሆን? ውሸት፣ ሽንገላ፣ ድንበሩን የሳተ መዝናናት፣ ዘፋኝነት፣ ስካር፣ መዳራት፣ አመንዝራነት፣ ሴሰኝነት፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ጉበኝነት፣ ዘረኝነት … ተወዶና ተደግፎ ለምን ይሆን እውነተኛነት፣ ሐቀኛነት፣ በልክ መኖር፣ መልካም ትዳር፣ ጨዋነት የተነቀፈውና የተተቸው?
    ጌታ ኢየሱስ በመቅደስም እያስተማረ ሳለ፣ “የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ” (ዮሐ.7፥32)፤ ነገር ግን የተላኩት ሎሌዎች ከመሪዎቹ ተሽለው ስለኢየሱስ፣ “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው” መሰከሩ፡፡ እብሪት እንጂ መልካም ነገር የማይወጣቸው የአይሁድ መሪዎች፣ “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው …” በማለት የወታደሮቹን ምስክርነት እጅግ አጣጣሉት፡፡
ከዚህ ከአይሁድ መሪዎች ንግግር ሦስት ነገሮችን እስናስተውላለን፤
1.      ሕዝብ ያላቸውን ንቀት፦ እውነት ነው፤ ሕዝቡ ሕጉን መጠበቅ ባለመቻሉና ሕጉን ራሱን ባለማወቁ እጅግ በጣም ኃጢአተኛ ነበር፤ ለሕጉ ቅርብና ሕጉን አዋቂዎቹ መሪዎቹ ነበሩ፤ ግን ለሕዝቡ ከማስተማር ይልቅ በሕጉ አመካኝተው ሕዝቡን ይበዘብዙና ያራቁቱት ነበር፤ (ማቴ.23፥4 ፤ 14)፡፡ ከአስራቱና በኩራቱ ጥቂቷ እንኳ ሳትቀር በዝብዘው ሲያስወጡና ሲያስከፍሉ፣ ነገር ግን እንኳን ዋናውን ጥቂቱን ለሕዝቡ ሲስተምሩ አይታዩም ነበር፡፡
    ለንቀታቸው ማጽኛ ደግሞ፣ “የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን” (ዘዳግ.27፥26) የሚለውን ጥቅስ በመጥቀስ የሕዝቡን አላዋቂነት በማጋነን በአላዋቂ ሕሊናቸው ኰነኑ፡፡ እጅግ በተቃራኒው ከአይሁድ መሪዎች ይልቅ ሕዝቡ ለሙሴ ሕግ በመታዘዝ የተሻለ የሚበልጥም ነበር፡፡ ሎሌዎቹ እንኳ ያዩትንና የሰሙትን እውነቱን በመናገር ከእነርሱ እጅግ የተሻሉ ነበሩ፡፡
2.     ውቀቱ ቢኖራቸውም ከማስተዋል ጐድለዋል፤ ነቢይም ሆነ ክርስቶስ ከገሊላ እንደማይነሳ ደጋግመው ተናግረዋል፤ (ዮሐ.1፥47 ፤ ዮሐ.7፥53)፡፡ እንደገናም ከሸንጐው መካከል ያመነ ሰው እንደሌለ በድፍረት ተናግረዋል፡፡ አወይ አለማስተዋል! መጻሕፍትን በእውነትና በልበ ሰፊነት ቢመረምሩ ዮናስ የተነሣው (2ነገ.14፥25) ከገሊላ ነበር! እንዲያው ማንም ባይነሳ እንኳ፣ ጌታ እግዚአብሔር ከወደደበት ቦታ ነቢያትን ማስነሳት ይችላል፡፡ እርሱ በሥራው ከልካይ የለበትምና፡፡
    ይህ ስህተታቸው እግዚአብሔርን የእነርሱ ሃሳብ ተስማሚ ለማድረግ መሻታቸውን ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔርን ውብና ድንቅ ሃሳብ ከሰው ድኩምና ሰባራ ሃሳብ ጋር ለማስማማት እንደመሞከር ስንፍና የለም፡፡ አዎን! እነርሱ ከናቋት ገሊላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ተገኝተዋል፡፡ 
     እጅግ የሚገርመው፣ ከሸንጐው መካከል ኒቆዲሞስ በእርሱ ያመነ ነበር፤ ያም ብቻ ሳይሆን፣ “ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤” (ዮሐ.12፥42) እንዲል ሌሎችም ለማመን የደፈሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የአይሁድ መሪዎች ይህን ሁሉ ሊያዩ ባለመመውደዳቸው፣ “መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም” (ኢሳ.6፥9 ፤ ማቴ.13፥14 ፤ ሐዋ.26፥28) የሚለው ተግሳጽና ወቀሳ ወደቀባቸው፡፡
3.     ግ ተላላፊዎች ነበሩ፦ የሕዝቡ መሪዎች ሕዝቡ ሕጉን አያውቅም ብለው ኮንነዋል፡፡ ኒቆዲሞስ ደግሞ ስለጌታ ኢየሱስ፣ “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” ብሎ በመናገሩ፣ መሪዎቹ ሕዝቡን የሙሴን ሕግ አልጠበቃችሁም ብለው ከኰነኑበት ኩነኔ በባሰው መያዛቸውን መሰከረባቸው፡፡ ባላስተማሩት ሕዝብ አላዋቂነት ሲሳለቁ እነርሱ ባወቁት ፍርድ ስተው ተገኙ፡፡ እነርሱ ሕዝቡ በሕጉ እንዲመላለስ ያስጨንቁትና ይገፋፉት ነበር እንጂ፣ ለራሳቸው መጠበቅን አይፈልጉም፤ መጠበቅም ተስኗቸው ነበር፡፡ ዛሬስ ያለው እውነት ከዚህ የተለየ ይሆን? ቤተ መንግሥቱ አሥር እና አምሳ ብር ሰርቆ ፍርድ ቤት ቀርቦ ያመነውን “ወንጀለኛ አገኘሁ” ብሎ አምኖ ዋና የዜና ርዕስና የመወያያ አጀንዳ ሲያደርግ፣ እጁን በደም የታጠበውን፣ አገር አሳልፎ የሸጠውን ግን ሲሾምና ሲሸልም አይደል ወይ የሚገኘው? ቤተ ክህነቱ የታወቁ ሴሰኞችና ጉበኞች፣ ዘረኞችና ፍርደ ገምድሎች በጉያው የተሰገሰጉ አይደለም ወይ?
    ኒቆዲሞስ ይህን ነው አጽንቶ የተናገረው፤ ሕዝብ ከመራገምና ከማራኮት መጀመርያ ለራስ ሕጉን መጠበቅ ይገባል በማለት፡፡ የማንጠብቀውን ሕግ እንዴት እንዳኝበታለን? እኛ ሕግ ተላላፊዎች ሆነን ሌሎችን እንዴት ሕግን ተላለፋችሁ ብለን መውቀስና መቆጣት ይቻለናል? ያውም እኛ በባሰ ስህተት ሆነን፣ አላዋቂውንና የምንመራውን ሕዝብ እንዴት እንመጻደቅበታለን? ጉቦ ተቀብለን እየፈረድን፣ ጉቦ ሰጪውን በምን ሕሊና ነው የምንቀጣው?
    ኒቆዲሞስ እውነት በመናገሩ እኩያ መሪዎቹ አሽሟጠጡበት፤ “ተከታዩ ነህን?” በሚል ንግግር፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ” አሉት፤ ይህ ግን መባል የነበረበት ለእነርሱ እንጂ ለኒቆዲሞስ አልነበረም፡፡ ዳሩ በማሽሟጠጥ ቢሆንም የተናገሩት እውነት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ የጌታ ኢየሱስ ተከታይ ነበርና፡፡ እውነተኞች የጌታ አገልጋዮች ዛሬም ከመተረብ፣ ከመናቅ፣ ወደዳር ከመገፋት፣ ካለመደመጥ፣ ከመሽሟጠጥ፣ ከመተቸት፣ ከመገለል … አላመለጡም፡፡ በእርግጥ ኢየሱስን በመከተል የሚደርሰን፣ የላላው ሕግ እንዲጠብቅ መቅናታችን፣ ድኃ አደጉ እንዳይበደልና እንዳይጠቃ መሟገታችን፣ … ዛሬም ዋጋው ሽልማት፣ ጽዋው ምርቃት አይደለም፡፡
  አዎን! ከምን ጊዜውም ይልቅ ኢየሱስን በትክክል መከተልና ማወጅ ዛሬም የክስ ዋና ምክንያት ነው! ይህ እየሆነ ያለው ወንጌል በጨበጡና የወንጌሉን እውነት ለራሳቸው በሚተረጉሙ አሳቾችና የበግ ለምድ ለባሾች ተኩላ ነው፡፡ አዎን! ምንም እንኳ የሚቀበለን ባናገኝና ብንገለልም፣ ዘወትር ለጌታ ኢየሱስ በመታመን ልንኖር ይገባናል፤ እርሱ በሚነቅፉትና በሚሰድቡት መካከል ስሙን የሚመሰክሩለትና የሚያውጁለት እንጂ በእርሱ የሚያፍሩበት ልጆች የሉትምና፡፡

    ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ የአብ ልጅ የክርስቶስን ፍቅር በልባችን ይሳል፤ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡ 

1 comment:

  1. አዎን! ከምን ጊዜውም ይልቅ ኢየሱስን በትክክል መከተልና ማወጅ ዛሬም የክስ ዋና ምክንያት ነው! lik bilehal!

    ReplyDelete