Tuesday 28 March 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ሰባት)

                                                         Please read in PDF

7.   አገልጋይ ለጌታው በፍጹም ፈቃዱና በፍጹም ሃሳቡ መታዘዝ ይገባዋል፦ ከሕጉ ትዕዛዛት አንዱ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” (ዘጸ.20፥3) የሚል ነው፤ ይህ ቃል የምሥራቅ ዓለሙን ሁሉ አምላኪነት የሚቃወም ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤል እግዚአብሔርን በመፍራትና በማክበር ልታመልከው እንደሚገባ ፍጹም አመልካች ሕግ ነው፡፡ ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ሌሎችንም ሃሳቦች በውስጡ ይዟል፡፡ ይኸውም (1) አማኞች ቅዱስ ለሆነው እግዚአብሔር ከአማልክትና ከርኩሳን አጋንንት ራሳቸውን በመለየት መቀደስ አለባቸው፡፡ ከከንቱ አማልክትም መራቅ ይገባቸዋል፡፡ ይህ የቆሙትንና የሚሰገድላቸውን አማልክት ብቻ ይይደለ፣ ከእግዚአብሔር ያስበለጥነውን ወይም ያስተካከልነውን ማናቸውንም ነገራችንን ይመለከታል፡፡ (2) አማኞች እግዚአብሔር በጎውን ነገር ብቻ እንደሚሰጣቸው  በማመን በፍጹም ኃይላቸውና ፈቃዳቸው፤ ሃሳባቸውም ሊያምኑትና ሊታዘዙለት ይገባል፤ (ዘዳግ.6፥5 ፤ ፊልጵ.3፥8)፡፡

    የዚህን ቅዱስ ሕግ መርሕ ይዘን ስንነሳና፣ “ምስክሩን የሚፈልጉ፣ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፤ ዓመፅንም አያደርጉም፣ በመንገዶቹም ይሄዳሉ” (መዝ.119፥20 የሚለው ቃል አጽንዖት ሰጥተን ሁለት ምሳሌዎችን ብናነሳ፣ አገልጋይ(አማኝ) ከምንም በላይ ለእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ በፍጹም ፈቃዱና ሃሳቡ መታዘዝ እንዳለበት እናስተውላለን፡፡
    በእርግጥ አንዳንዴ የታዘዝነው ነገር “የማይጥምና የማይመስል” ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም እንኳ ለታዘዝነው የእግዚአብሔር ሥራ ግድ የለሽነት በበዛበት ችኮላና ማስተዋል በጎደለው ቸለኝነት ልናደርገው አይገባንም፡፡ ልክ እንደተባልነው ልናደርገው ይገባናል፡፡ ቃሉም፣ “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደግ ርጉም ይሁን” (ኤር.48፥10) ሲል፣ የእግዚአብሔርን ሥራ በተሸነፈ ማንነት ማድረግ እንደሌለብን የሚያሳይ ሃሳብ ነው፡፡
     በአንድ ወቅት ንጉሥ ሳዖል “ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፣ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው፤” (1ሳሙ.15፥18) ተብሎ ታዞ ነበር፤ ነገር ግን “ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፤ ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት፤ … ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል፤ የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን” (1ሳሙ.15፥9 ፤ 15)፤ በማለት ያልታዘዘውን ለእግዚአብሔር የቀና በሚመስል ሞኝነት ትእዛዙን ከመፈጸም ቸል አለ፡፡ እግዚአብሔር ከከለከለው ነገር ውስጥ በረከት ይገኛል ብሎ እንደመፈለግ ያለ ከንቱነትና መታለል የለም፡፡
   ንጉሥ ሳዖል በፍጹም ሃሳቡ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ መሥዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ወደደ፡፡ እጅግ ብዙና የሰቡ መሥዋዕቶችን ከማቅረብ ይልቅ የእግዚአብሔርን ፍጹም ፈቃድ ማስተዋል መጀመር እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ምድርና መላዋ የእግዚአብሔር ከሆነች፣ እኛ ከምንሰጠውና ከምናቀርበው ነገር ይልቅ የሚታዘዝ ልብን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል፡፡
    ቅዱስ ነቢይ ሙሴ ፍጹም እግዚአብሔርን በደለ፤ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአርባ ዓመታት በኋላ፣ ከአርባ ዓመታት በፊት በራፊዲም(ዘጸ.17፥1-3) በማመጽ በበደሉት በደል አሁንም በደሉ፡፡ በዚያ ውኃ ስላልነበረ ሕዝቡ በማጉረምረም በሙሴ ላይ ተነሣሣ፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሴና አሮን ወደእግዚአብሔር ፊት ቀርበው ማለዱ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ሙሴን “በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤” (ዘኊል.20፥6) በማለት ተናገራቸው፡፡
    መመሪያው እጅግ በታም ግልጽ ነበር፤ “ድንጋዩን ተናገሩት” የሚል፡፡ ነገር ግን ሙሴ እንደታዘዘው ያይደለ በሕዝቡና በዓለቱ ላይ ተቆጥቶ “እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው”፡፡ ይህን በማድረጉም የተነገረውን ትእዛዝ በግልጥ ተላለፈ፡፡ እግዚአብሔርም እጅግ አዘነበት፤  ለምን ግን እንዲህ አዘነበት?፣ ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶችን ማንሳት እንችላለን፤
1.      ሙሴ የታዘዘው ሕዝቡ ሁሉ ባሉበት ዓለቱ ውኃ እንዲሰጥ እንዲናገረው ነበር፡፡ ነገር ግን ሙሴ ዓለቱን ሁለት ጊዜ በመምታት ለእግዚአብሔር በትክክል አለመታዘዙን አሳየ፡፡ ይህንንም ያደረገው በመቆጣትና በችኮላ ነበር፤ በተለይም ንግግሩ “በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን?” የሚለው ቃሉ በግልጥ “መሰልቸትንና መታከትን” የሚያንጸባርቅ ነበር፡፡
    በሌላ መልኩ የሙሴን ሃሳብ ስንመለከተው ዓለቱን መናገሩ ብቻ በቂ አልመስልህ ያለው ይመስላል፤ በዚህም እግዚአብሔር እንደተናገረው፣ “በእስራኤል ልጆች ፊት አልቀደሰውም ወይም አላከበረውም ወይም ልክ እንደባርያ ፈቃዱን አልታዘዘውም“፤ ስለዚህም መዝሙረኛው እንደተናገረው፣ “በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ” (መዝ.106፥33)፡፡
2.     በእግዚአብሔር ጥበቃና መግቦት ላይ የነበረው እምነትም ፍጹም የተረሳው ይመስላል፡፡ ይህም በሁለት ነገር ይታወቃል፤ ልክ ጥያቄ ከሕዝቡ ሲቀርብለት፣ በእግዚአብሔር ታምኖ መልስን አልመለሰም፤  ውኃው ከፈለቀ በኋላ ደግሞ  በእግዚአብሔር ላይ መታመኑን በግልጥ ተወ፡፡ በዚህም ምክንያት “በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም” (ዘኊል.20፥12) የሚል ከባድ ወቀሳ አገኛቸው፡፡ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን አሳዘኑ፡፡ ከኪዳኗም ርስት በገዛ አለመታዘዛቸው ራሳቸውን ለዩ፡፡ በዚህ ሥፍራ ላይ እግዚአብሔር ቅጣቱን ያስተላለፈው በወንድሙ በአሮንም ላይ ነው፤ ምክንያቱም በሁሉም ነገር ሲተባበረው ነበርና፡፡
    እግዚአብሔር በአብዛኛው ከሕዝቡ ይልቅ በታመኑ አገልጋዮቹ ላይ በጥፋታቸው ፍርድን ያስተላልፋል፡፡ ስለዚህም በተስፋይቱ ምድር ማዶ እንዲቀሩና እንዳይገቡባት ከለከላቸው፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ጠንካራ ፍርድ በባርያዎቹ የሚያስተላልፈው ጨካኝ ሆኖ አይደለም፤ አገልጋዮች የሚሠሩት ስህተት የሚያስተው ብዙውን ነው፤ ስለዚህም እነርሱን በግልጥ በመቅጣት ኃጢአትን ፈጽሞ ይቃወማል፡፡
     አገልጋይነት በዛሬ ዘመን ከጌትነት መደብ ተመድቧል፡፡ ልጅነት አንሶ አገልጋይነት ወደመግነን ሄዷል፡፡ አገልጋዮች ከልጆች በላይ ራሳቸውን አግነው፣ ልጅነትን ወግድ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ጌታቸውን የማያከብሩና የራሳቸውን ስምና ቤት የሚያስከብሩና የሚያደራጁ፣ ለጌታ ፈቃድና ሃሳብ በፍጹም ፈቃድና ሃሳባቸው የማይታዘዙ አገልጋዮች ከመቼውም ጊዜ በዘመናችን ፈልተዋል፡፡ ስለዚህም አገልጋይነት ከልጅነት በልጦብናል፡፡ በልጅነት መንፈስ ለአባታችን ከመታዘዝ በላይ በአገልጋይነት ዘመናችን ከምንም በላይ የላከንን ጌታና አምላክ ልንሰማውና እንደተናገረን ቃሉም ልንታዘዘው ይገባናል፡፡
ጌታ አምላክ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …



4 comments:

  1. ጌታ ሆይ! የታመኑ አገልጋዮችን አስነሳልን … ወንድሜ ጌታ ይባርክህ

    ReplyDelete
  2. KALEHIEWET YASAMALEN!

    ReplyDelete
  3. "ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።"
    (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2:13፤)

    ReplyDelete
  4. selam lante yihun wendeme betam xru meleke yalachi tsufochun new mitsifew ina kegize gare mihedw new ina bezi kexil geta yiderah ina semonu post mitaregachew pdf mawerd imbi iyale new echi bitasitekakilew ina geta yageligilot zemih yibarekew

    ReplyDelete