Sunday 5 February 2017

ጌታ ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
4.   ድቅን ሁሉ ለመፈጸም   ጽድቅ የሚለው ቃል፣ ቀጥታ ከዕብራይስጥ የተቀዳ ሲሆን ትርጉሙ፥ ፍጹም ትክክለኛነት፣ ቀጥተኛ፣ ፍትሓዊ፣ በጐ ምግባር ማለት ነው፡፡  ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት “በትክክለኛ ሁኔታ” ላይ ሆኖ መገኘት ማለትን በግልጥ ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ከመጀመርያው ለሰው ያለው ሃሳቡ እንዲህ ነበር፡፡ ፍጹም ጻድቅና መልካም እንዲሆን፥ ሰው ግን በእግዚአብሔር ፊት በመልኩና በአምሳሉ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ወደገዛ መንገዱም በማዘንበል በምሳሌው እንደ መልኩ ማንነቱን በመያዝ (ዘፍ.5፥3) በኃጢአት ተሰነካክሎ ወደቀ፤ ከትክክለኛነትም ተሰናከለና በዕድፈት ረከሰ፡፡
    መጥምቁ ዮሐንስ አስቀድሞ ጌታ ኢየሱስን ለማጥመቅ ፈቃደኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ምንም በደልና ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ጻድቅ መሆኑን አስተውሏልና፡፡ ስለዚህም አብረውት ስለኃጢአታቸው ሊጠመቁ ከቆሙት እንደአንዱ ሊቆጥረው አልደፈረም፤ ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ከሁሉ የተለየ ልዩ መሆኑን የአዋጅ ነጋሪው ሰው ተገነዘበ፡፡ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” በማለት፣ ራሱን ከኢየሱስ ጋር በማስተያየት፣ ዮሐንስ ራሱ መጠመቅ የሚያስፈልገው ፍጹም ኃጢአተኛ መሆኑን መሰከረ፡፡ በእርግጥም፣ ሰው ከሆነው ከኢየሱስ በቀር አንዳች ፍጹምና ጻድቅ ከምድር ስለጠፋ ክርስቶስ ጽድቃችን ሊሆን መጣ፡፡ እርሱ አንዳች በደልና ነውር ያልተገኘበት ነውና ጽድቅን  በመሥራት ለእግዚአብሔር አቀረበን፤ (ዕብ.4፥14 ፤ 1ጴጥ.2፥22-23)፡፡

     የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የሰውን ሁሉ ኃጢአት እንዲሸከምና ስለሰው ልጆችም ሁሉ በደልና ኃጢአት የተቀጣ እንዲሆን ፍጹም ፈቃዱ ነው፡፡ አዳም ምርጫውን ተከትሎ ኃጢአትን ሠርቷል፤ በአዳምም አይሁድና(ሮሜ.2፥1-3፥8) አሕዛብ(ሮሜ.1፥18-32) እንዲሁም ዓለሙ ሁሉ ኃጢአትን በመሥራት ከእግዚአብሔር ጽድቅ ወይም ትክክለኛነት ፈጽመው ጐድለዋል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ በባሕርይው ንጹሕ ነውና፣ የሰውን ልጅ ወደራሱ ለመሳብ ሰው በፈቃዱ የፈጸመውን ኃጢአት መቅጣትና የሰውን ልጅ መቤዠትና መታደግ አለበት፤ ይህን ባይሆን ግን የእግዚአብሔር ጽድቅ ፍጹም መሆን ይሳነዋል፡፡
     በዚህ በጥምቀቱ ቀን እጅግ ልዩና የሚያስደንቅ ነገር ሆኗል፤ ይኸውም ክርስቶስ መጥምቁ ዮሐንስን፥ “አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” በማለት፣ ከዘላለም የነበረውን የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሃሳብ ሊፈጽም የመጣ መሲሕ መሆኑን መስክሯል፡፡
   ጌታ ኢየሱስ በደል የለበትምና ለራሱ መጠመቅ አያስፈልገውም፡፡ ራሱን ከኃጢአተኞች ጋር “በመቁጠርና” እጅግ ዝቅ በማድረግ የተጠመቀው ለእኛ ሲል ነው፡፡ እርሱ በፈቃዱ ጽድቅን ባያደርግልን እኛ ጻድቃን መባል አይቻለንም ነበር፡፡
    እግዚአብሔር ትክክለኛነትን ወይም ፍጹምነትን ከሰው ወገን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ሰው ሁሉ ከፊተኛው ሰው የተነሳ በመርገምና በፍዳ ተይዞ ነበርና፡፡ ኃጢአት መበላሸትን በአንዱ ሰው አዳም ብቻ ያይደለ በመላው ዓለም ላይ ሙስናን(መፍረስና መበስበስን) አስከትሏል፡፡ ኋለኛው አዳም በፍጹም ሰውነቱ እግዚአብሔር አብ ነፍሱ ደስ የተሰኘችበት ጻድቅ ሆኖ ተገለጠ፤ (ኢሳ.42፥1 ፤ 53፥11)፡፡ እግዚአብሔር አብም በአንደበቱም “የምወደው ልጄ” ብሎ ከሰማያት መሰከረለት፡፡
     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅን አደረገ ስንል፣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ሊኖር የሚገባውን ትክክለኛና ተገቢውን ሕይወት ኖሮ በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት ተገለጠ፤ ታየም ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በምድር ፊት ከሚመላለሰው ሰው ሁሉ ፈልጎ ያጣውን ጽድቅ፣ ከፍጹም ሰው ከክርስቶስ ኢየሱስ አገኘ፤ ፍጹምም ረካ፡፡ ጌታችን፣ መጥምቁ ዮሐንስን  “እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” ማለቱ ለዚህ ነበር፡፡ “ምንም እንኳ ንጹሐ ባሕርይ አምላክና መሲሕ ብሆንም ስለሰው ተገብቼ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባኛል” ብሎ፣ ጌታችን ኢየሱስ ሲናገርም መጥምቁ ዮሐንስ ፈጽሞ ታዘዘ እንጂ አልተከራከረም፡፡
   ጌታ ኢየሱስ ለሚያምኑበት ሁሉ መታያና ፍጹም መዳኛ መሆን የተቻለው ለዚህ ነው! ጻድቅ ሆኖ ጽድቅን ስለፈጸመ በእርሱ የሚያምኑና በሕይወቱም የሚኖሩ ሁሉ ጻድቃንና የተመረጡ ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ የተገለጠ የወንጌል አዋጅና ምስክርነት ሆነ፡፡ ወንጌልን ማወጅ ወይም መመስከር ማለት፣ “በእግዚአብሔር ልጅ ጽድቅ ጽድቁ፤ በሥራችሁ ለመጽደቅ አትንከራተቱ፤ በጽድቁ ጸድቃችሁም በሕይወቱ ተመላለሱ” ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ጽድቅን ሁሉ ሊፈጽም መጥቶ ጽድቅን ሁሉ ፈጽሞታልና፡፡
5.   ምንከተለው ምሳሌ ይሆነን ዘንድ፦ ክርስቶስን በሚመስል ሕይወት መመላለስ እንዳለብን፣ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” (1ጴጥ.2፥21) ተብሎ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አንደበት ተገልጧል፤ በሌላ ሥፍራ እንዲሁ ደግሞ፣ “ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” (ሮሜ.6፥2-3) በማለት ጥምቀት ከክርስቶስ መከራ፣ ሥቃይና ሞት የመካፈል ምስጢር እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡
   ሁላችን የክርስቶስ ምዕመናንም ስለወንጌልና ስለምስክርነታችን መከራን እንቀበላለን፡፡ ራሱ ጌታችንም፣ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና” (ማቴ.5፥11-12) በማለት ክርስቲያኖች ሁሉ በስሙ መከራን በመቀበል ሐዋርያትንና ቅዱሳንን ሁሉ መምሰል እንደሚገባቸው አስተማረ፡፡ 
   መከራውንም የምንቀበለውና በሁሉ ነገራችን እርሱን መከተላችንና መምሰላችን የሚታወቀው፣ የመከራው ምንጭ በእግዚአብሔር ፈቃድ(1ጴጥ.3፥17 ፤ 4፥19)፣ ጌታችን እንደነገረን በቅዱስ ስሙ ምክንያት ከሆነ (ማቴ.5፥11 ፤ ሐዋ.9፥16)፣ ስለጌታ ወንጌልና (ማር.8፥38 ፤ ኤፌ.3፥1 ፤ 2ጢሞ.1፥8) ስለጽድቅ (1ጴጥ.3፥14 ፤ 4፥15) የተቀበልን ስንሆን ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ብዙ አማኞች በዚህ ባለንበት ዘመን መከራችን፣ መነቀፋችን፣ መተቸታችን፣ መሰደባችንና መዘለፋችን ብሎም ከሰው መካከል መገለላችን ምንጩና ምክንያቱ ምን ይሆን? እውነት ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ናቸውን? ካልሆነ ራሳችንን በንስሐ፣ በቅዱስ ቃሉ እውነትነት እንመርምር!
   እንግዲህ ክርስቶስ ለምን እንደተጠመቀ በትክክል ካልተረዳን “የመታሰቢያ በዓሉን መንፈሳዊነት” ከመዘንጋታችን አልፎ፣ ትክክለኛ የክርስትና አማኞች መሆናችንን ከጥርጣሬ ሊያስገባ የሚችል ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በበዓሉ ቀን የሚታዩ ቅጥ ያጡ ጭፈራዎችና፣ የዳንስ ምሽቶች፣ የአመንዝራነት ጠባዮች፣ ስካርና የሚፈጸሙት የቡድን ወንጀሎች ወዘተ. ምን መሆናችንን እየመሰከሩብን ነውና፡፡ ስለዚህም መንፈሳዊነታችንን በቃሉ እውነትና በወንጌሉ እውቀት ላይ እንገባ፡፡ ደግሞም በክርስቶስ የጽድቅ ሕይወት የተለወጠ ማንነትን በመያዝ ጽኑዓን ኾነን ልንቆም ይገባናል፡፡
    ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ሆይ! ስለቸርነትህ እናመሰግንሃለን፤ ስላደረክልንም የመስቀል ቤዛነትህ እናመልክሃለን፡፡ አሜን፡፡ ተፈጸመ፡፡


3 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር

    ReplyDelete
  2. egziabehere yibarkehe. teru sehuf new.

    ReplyDelete
  3. ራሱን ከኃጢአተኞች ጋር “በመቁጠርና” እጅግ ዝቅ በማድረግ የተጠመቀው ለእኛ ሲል ነው፡፡ እርሱ በፈቃዱ ጽድቅን ባያደርግልን እኛ ጻድቃን መባል አይቻለንም ነበር፡፡

    ReplyDelete