Wednesday 25 January 2017

ጌታ ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? (ክፍል ሦስት)

Please read in PDF
3.    ሰው ኃጢአትና ውድቀት ጋር ራሱን ይደምር ዘንድ ይህ ሃሳብ በመንፈስ ቅዱስና በቃሉ ማስተዋል ካልሆንን በቀር፥ ብዙዎች ተሰነካክለው እንደወደቁበት ልንሰነካከልና ልንወድቅበት እንችላለን፡፡ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትስብእትነት ላይ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውቀት ባለመያዛቸው ምክንያት ከጥንት ዘመን ይስት እንደነበር ዛሬም ብዙዎች ሲስቱ እያየን ነው፡፡

 ጌታ ኢየሱስ ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ሳለ፥ በሰው ልጅ ላይ በኃጢአት ምክንያት የመጣውን እርግማንና ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ በመሲሕነቱ ወደምድር መጣ፡፡ እርሱ በደል የሌለበት ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክም ነው፡፡ ቅድስና የባሕርይው፣ ንጽሕና ገንዘቡ፣ ፍጹምነት የራሱ፣ እንከን አልባነትና ኃጢአትን አለማወቁ ማንነቱ ነው፡፡ መጽሐፍም ይህን እውነት ይመሰክራል፤ (ዕብ.4፥15 ፤ 2ቆሮ.5፥21)፡፡ ሰው ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነበር፤ እንዲያውም በሰው ዓይን “መልካም የተባለው የሰው ጽድቅ” ከመርገም ጨርቅ የከፋ እድፋም (ኢሳ.64፥6)፥ የእግዚአብሔርን ክብር አጉዳይና ጽድቅ አልባ (ሮሜ.3፥11)፥ ሰውም ራሱ ደግሞ በፍጥረቱ እንኳ ሳይቀር የቁጣ ልጅ(ኤፌ.2፥3)፥ ያለመታዘዝና የአመጸኛ ባሕርይ ምሳሌ ሆኖ ለዘመናት በኃጢአት ባርነት የኖረ ነው፡፡ ይህንንም የሰውን ዕዳና ፍዳ ማስወገድ የሚቻለው ፍጡራዊ አካል በሰማይም በምድርም ሊገኝ ፈጽሞ ስላልተቻለ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ወደዚህ ምድር መጣልን፡፡
     ኃጢአት ማለት በራሱ፥ እግዚአብሔር ለሚፈልገው ቅድስናና ንጽዕና አለመብቃት ወይም እግዚአብሔር ከሚፈልገው ቅድስና ዘንድ መድረስ አለመቻል ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ በመውጣቱ ምክንያት ሞቷል፤ እናም በዚህ ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ መድረስ ተሳነው፤ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መንፈሳዊ ዒላማም ፍጹም ሳተ፡፡ ኃጢአትንም በመፈጸሙ ምክንያት ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር የተረገመና ለእግዚአብሔርም ፍጹም ጠላት ሆነ፡፡ ነገር ግን፥ “እርሱ ራሱ ልመናን የሚሻ መስሎ በጥንት ዠምሮ ያገኘንን ፍዳ ከእኛ ያርቅ ዘንድ አብን ማለደው፤ እንደገና ደግሞ እንዲያስበን፤ ከእርሱም እንዳይለየን ስለእኛ አብን ይማልደው ዘንድ ባሕርያችንን ነሥቷልና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለበጐ ሥራ ሁሉ ዠማሪ አብነት ሆነን፡፡ ሰው በመሆኑ ከአብ ርዳታን ያገኝ ዘንድ የሚሻ መስሎ ለእኛ ትንሣኤን አዘጋጀልን፤ ለእኛ ባሕርይ አስቀድሞ ልጅነትን አዘጋጀ፤ እርሱ ግን በባሕርይ ፍጹም ነው፤ በባሕርዩ ፈጽሞ ምንም ሕጸጽ የለበትም የተዋሐደውን ሥጋ ከተዋሐደ በኋላ ለእርሱ ብቻ በእውነት ገንዘቡ ሆነ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ ምዕ.79 ክፍል 50 ቁጥር 38) እንዲል፥ በደል የሌለበት ጌታ በነገር ሁሉ የመልካም ነገር ጀማሪ ሆነልን፡፡
     ስለዚህም በሰው ልጅ ላይ ያለውን ኃጢአትና መርገም ሊያስወግድ ክርስቶስ ኢየሱስ ወደምድር መጣ[አማኑኤልም ተብሎ ለእግዚአብሔር ዘመዶቹ እንድንሆን ፈቀደ]፡፡ በተጠመቀ ጊዜም፥ በደል የሌለበት ጌታ ከኃጢአትና ከሰው ልጅ ውድቀት ጋር “የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል” በአንድነት ተቆጠረ፤ (2ቆሮ.5፥21)፡፡ ኃጢአት የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ አምላክ እንደ“ኃጢአት” ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ፤ እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ እርሱ ስለእኛ “ኃጢአት” ሆነ፡፡
    እግዚአብሔር አብ በኃጢአት ሊፈርድ ሲመጣ፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሁላችንን በደልና ኃጢአት ተሸክሞ ነበር፤ (ኢሳ.53፥4)፡፡ ምንም እንኳ ለበደለኛ ሰው የሚራራው አምላክ ነገር ግን ኃጢአትን ከመቅጣት ቸል የማይለው ጌታ፥ የእኛን ኃጢአት በመሸከሙ ምክንያት በእኛ ቦታ የገባው፥ ቤዛና ምትክ የሆነው ኢየሱስ ልንቀጣ የነበረውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ስለእኛ ተቀበለ፤ በእኛ ቦታ ገብቶ ከኃጢአት በመቆጠሩም እኛ የእርሱ ጽድቅና መንግሥቱን ወራሾች ሆንን፡፡
    በተመሳሳይ መልኩ ሕግን ባለመፈጸም ከሚመጣውም እርግማን (ገላ.3፥13)፥ ጌታ ያድነን ዘንድ እርሱ በብቃቱ ሕግን ፈጸመልን፡፡ በሕግ የጸደቀ የለም ወይም በሌላ ቋንቋ ሕጉን ሙሉ ለሙሉ ያለእንከን መፈጸም የቻለ ከሰው ወገን ማንም ሊገኝ አልተቻለም፤ ስለዚህ ሰው ሁሉ በእርግማን ተያዘ፤ ክርስቶስ ደግሞ እርግማናችንን ይሽር ዘንድ መፈጸም ያልቻልነውንና የመረገማችንን ምክንያት የሆነውን ሕግ ያለአንዳች ጉድለት በመሲሐዊ ብቃቱ ፈጸመው፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎም ይህን እርግማናችንን ለአንድያው ሻረው፡፡ ከዚህ የተነሳ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ከኩነኔ ነጻ ሆነው አርነት አጊኝተዋል፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ውጪ ያሉቱ ሁሉ ወይም በእርሱ ጽድቅ ሳይሆን በሕግ ሥራ እንደሚጸድቁ የሚያስቡና የሚጥሩ ኩነኔ ናቸው፡፡
    እንግዲህ ጌታ ኢየሱስ የመጠመቁ አንዱ ዋና ነገር ይህ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደዮርዳኖስ ሲመጣ፥ “… ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር፤”(ማቴ.3፥5-6) ነበር ይለናል፥ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከኃጢአታቸው ሊጠመቁ ከቆሙ ኃጢአተኞች ጋር በአንድነት ተሰልፎ መቆሙን እንመለከተዋለን፤ ይህም የሆነው ዘም ብሎ እንዲያው የሆነ ሳይሆን፥ “ኃጢአት ሆኖ” ስለእኛ ይቆጠር ዘንድ ነው፡፡
   ይህን ድንቅ እውነት በሚገባ አስተውሉ! ይህ እጅግ ትልቅ ፍቅር ነው! ዳሩ ዛሬ ላይ ብዙዎች ከጥምቀቱ ዋዜማ ጀምሮ ለዝሙት፣ ለመዳራት፣ ለጭፈራና ለስካር ይገባበዛሉ፤ በዚህም ራሱን አዋርዶ “እንደኃጢአት የተቆጠረላቸውን” ጽድቅ ጌታ ዛሬም እጅጉን ይበድሉበታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለመዳናችን ይህን ያደረገው አንዴ ነው፤ ቃሉም፥ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥” (ዕብ.10፥26) እንደሚለው፥ ለሁለተኛ ጊዜ አይታይልንም፤ ለሚያምኑትና በእርሱ ለጸኑት ግን፥ “ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል፤” (ዕብ.9፥28)፡፡
    ስለዚህ ከጥፋትና ከበደል መንገዳችን ፈጥነን ልንመለስ፤ የመጠመቁን ትክክል የወንጌል ትምህርት በመያዝም ንስሐ ልንገባ በጽድቅ ሕይወቱም ልንመላለስ ይገባናል፤ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …


2 comments:

  1. ምክንያተ ጥምቀቱን እንዲህ አስተውዬው አላውቅም ይገርማል ወንድሜ ጸጋውን ያብዛልህ ተባረክ

    ReplyDelete
  2. keep up good job. May God bless you abundantly for telling the truth.

    ReplyDelete