Tuesday 14 February 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አምስት)

Please read in PDF
3.    ለክርስቶስ አገልጋዮች የሆንነው በፈቃዳችን ነው፤ ደኅንነት በደመወዝ መልክ አይገኝም፤ ደኅንነት ሁል ጊዜ ከጸጋ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው፡፡ ደኅንነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ፣ በሠራነውም ሥራና ሰዓት አይወሰንም፡፡ ከጸደቅንና ከዳንን ደግሞ (1ቆሮ.6፥11)፣ ስለጸደቅንበትና ስለዳንንበት ነገር የምናውጀው እውነትና የምንመሰክረው ምስክርነት አለን፡፡
    “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም” (ኤፌ.2፥8-9) እንዲል አሁንም፣ ዘወትር መርሳት የሌለብን ነገር፣ መዳን ጥረትን አይጠይቅም፤ አገልግሎት ግን ስለዳንንበትና እውነት መመስከርና ማወጅን ይጠይቃልና ጥረትን፣ ድካምን፣ የወዝ ጥሪትን፣ መውጣት መውረዳችንን ይሻል፡፡ የምንለፋው ትሁታን አገልጋዮች ሆነን ነው፤ ዋጋችን በእርሱ እንጂ በሰው ወይም በሌላ አካል ፈጽሞ አይደለም፡፡ ስለዚህም በፈቃድ አገልጋይ ከሆንለት ጌታ እንጂ ዋጋችንን ከማንም አንቀበልም፡፡ ጌታ አገልጋዮቹን የጠራቸው በፈቃዳቸው ነው፤ “ተከተለኝ” በሚል አጭርና ግልጥ ጥሪ፡፡ ለ“ልዩ ሥራ” ካልሆነ በቀር ጌታ ማንንም አስገድዶ ጠርቶ አያውቅም፡፡ ሁሉን በፈቃዱ ስለሚጠራ የሚከፍለውንም ዋጋንም በተመለከተ፣ እንደወደደ መክፈል እንደሚችል በግልጥ ተናግሯል፤ (ማቴ.20፥11-15)፡፡

    አገልጋይ በፈቃዱ ራሱን ለጌታ ለየሁ ካለ፣ ዋጋውን ከሰው ፈጽሞ መጠበቅ የለበትም፡፡ በሥራ ትጋትና ጥረት የመጀመርያ ለመሆን[ዋጋን ከሰው ለማግኘት] በማሰብ ማገልገል አደጋ አለበት፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ተመክቶ ከማገልገል በራስ ትምክህት ከሰው ብድራት እየጠበቁ ማገልገል እጅግ አሳዛኝ ውጤትን ያስታቅፋል፡፡ አገልጋይ የሆንነው የተወደድንበትን ትልቁን ፍቅር ክርስቶስን አይተን መሆን አለበት፤ እርሱ ለእኛ መዳን ፈቃዱን በውድ ከሰጠ፣ እኛ ደግሞ ለተሰጠልን ጌታ በፈቃዳችን ጮኸን እውነቱን ልንመሰክርለት ይገባናል፡፡ ይህን አለመረዳት አገልግሎትን እንደግዴታና ጫና እንጂ ተወዶ “እንደሚሠራ ሥራ” አናየውም፡፡ እንኳን በሥራው፤ በሥራው ውጤት በሆነው በመከራው እንኳ፣ “ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው፤ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤” (ሐዋ.5፥40-41) የተባለላቸው ደቀ መዛሙርት በሁሉ ነገር ደስተኞችና ፍጹም ፈቃዳቸውን የሰጡ ትሁታን አገልጋዮች ነበሩ፡፡ እኛስ “ሥራውንም” መከራውንም ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁዎች ነን? ምን ያህልስ ታማኞች ነን?
    ራሳችንን “እንደጠቃሚና ልዩ አካል” ወይም እኛ ባንኖር አገልግሎት የሚበላሽ ወይም የማይሳካ አድርገን ማየትና ማሰብ የለብንም፡፡ ያገኘነውም ሆነ የተቀበልነው ሁሉ ከጸጋውና ከራሱ ከሥጦታ ሰጪው ነውና፣ በራሳችን መመካትን መጀመር የለብንም፡፡ እጅግ የሚደንቀው ነገር የማንጠቅመውን እንድንጠቅም አድርጎ በጸጋው ካቆመን፣ ከጥንትም ፈጽሞ የማንጠቅም ነበርን ማለት ነው፤ በእርሱ ጸጋ ከቆምን ለዘወትር ከእርሱ በቀር ልንናገርለትና ልናገነው የሚገባን የራሳችንም ነገር ፈጽሞ ሊኖረን አልተባለለንም፡፡ ይልቁን ጠቃሚዎች እንድንሆን ለወደደው ጌታችን እጅግ ታማኞችና ፈቃዱን ፈጻሚዎች የፈቃድ አገልጋዮች ልንሆን ይገባናል፡፡
    አገልግሎት ግዴታ የሆነብን የለን ይሆን? ስንቶች ደስተኞች ናችሁ በመዘመራችሁ፣ በመስበካችሁ፣ በመስጠታችሁ፣ ሳትታክቱ በመምክራችሁ፣ በማስተባበራችሁና ሌሎችን በመርዳታችሁ … በመሰበካችሁ፣ በመመከራችሁ፣ በመገሰጻችሁ … ፍጹም ደስተኞች ናችሁ? የአገልግሎት ሰዓት ሊጀመር ሲል የሚበሳጩና የሚነጫነጩ “ተከፋይ አገልጋዮችን” አስታውሳለሁ፡፡ መዳኑን በደስታ ተቀብለን የመዳናችንን አዋጅ፣ እንደሳምራዊቷ ሴት አዋጁን በደስታ አውጀን ሰዎች፣ “አሁን የምናምን ስለ ቃላችሁ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን” (ሐዋ.4፥42) ብለው እንዲመሰክሩ ማድረግ ካልቻልን ንስሐ በመግባት መንገዳችንን ማስተካከል ይገባናል፡፡
4.    ባሪያ ጌታውን ሁል ጊዜ ሊያከብር፤ ሊፈራው፤ ወደእርሱም ዘወትር ማሳየትን ተግባሩ ማድረግ አለበት፡፡ አገልጋይ የአገልጋይነቱ ዋና መለኪያው ለጌታው ያለው ታዛዥነትና አክብሮት ነው፡፡ ባርያ ጌታውን ካልፈራ ትዕቢተኛና አመጸኛ ይሆናል፡፡ የማይታዘዝና የአመጸኛ ባርያ ባሕርይን ጌታ ኢየሱስ፣ “ያ ክፉ ባሪያ ግን፦ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፣ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ ...” (ማቴ.24፥48-49) በማለት አስቀምጦታል፡፡
  ከብልቶቻችን ማበላለጥ እንደማንችል እንዲሁ፣ አገልጋይም በማናቸውም መልኩ ከጌታ ዘንድ ለተላከላቸው ሕዝቦች በማበላለጥ ሊያገለግልና ሊያቀርባቸው አይገባውም፡፡ የአገልጋይ ትኩረት ሁል ጊዜ ጌታው ሊሆን ይገባል፡፡ የሚያገለግለው አንድ ሰው እንኳ ቢሆን፣ ለጌታ እንደሚናገር በፍርሃትና በማክበር ሊያደርገው ይገባዋል፡፡
   ጌታውን የማይፈራና የማያከብር አገልጋይ በበጎቹ ላይ ይቀማጠላል፤ ቅዱስ ነቢይ ሕዝቅኤል ስለዚህ ጉዳይ፣ “ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም” (ሕዝ.34፥3) በማለት ገልጦታል፡፡ “መንጋውን እየተመገቡ” መንጋውን እንዳለማገልገል ያለ ተላላነት ፈጽሞ የለም፡፡ አዎን! እንደባርያ ማገልገልና መታዘዝ ሲገባ፣ ራስን በጌታ ቦታ አስቀምጦ ማዘዝና መናዘዝ ግን ያልተገባና አጸያፊ ነው፡፡
    አገልጋይ ትጋትና ምጡ፤ እንባውም አማኞች ከሐሰተኛ ወንድሞች በደሙ ቅጥርነት ተከልለው በልባቸው ክርስቶስ እንዲሳልና ዘወትርም ወደክርስቶስ እንዲመለከቱ ማድረግ ነው፤ (ማቴ.3፥11 ፤ ሐዋ.20፥28-31 ፤ ገላ.4፥19)፡፡  ካገለገለም በኋላ ደስታው የጌታው መግነንና መክበር ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው እጅግ አብዛኛዎቹ አገልጋዮች ካሰማራቸው ጌታ ይልቅ የአገልግሎቱን “ክብርና ዝና” በቀጥታ ለራሳቸው ሲያውሉ በግልጥ እናያለን፡፡ ጌታ ግን እንደባርያ ያገለገሉትን ታማኝ ባርያዎቹን፣ እርሱም ያገለግላቸዋል፤ ሰማያዊ ምግብንም አዘጋጅቶ ይመግባቸዋል፤ (ሉቃ.12፥45)፡፡
   ደግሞም፣ አገልጋዮቹን ያሰማራው ጌታ አገልጋዮቹን በቀጥታ ሊመለከት ይመጣል[ዘወትርም ይመለከታል] (ሉቃ.12፥42 ፤ 21፥1-4) የሚመጣበትም ሰዓት የትኛውም አገልጋይ፣ “ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት” (ማቴ.24፥50) ተብሎ ተገልጧል፡፡ ደስ ያሰኙትንና በቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ሆነው ያገለገሉትን እንደሚያገለግላቸው እንዲሁ፣ በምድራዊው ነገር ተቀማጥለውና በበጐቹ ሃብትና ንብረት ደልበው በጐቹን ግን ለተኩላና ለዓለማዊነት የተውትን ባሮች፣ “ከሁለትም ይሰነጥቃቸዋል፥ እድላቸውንም ከግብዞች ጋር ያደርግባቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል” (ማቴ.24፥51) እንደተባለ በከባድ ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡
   አገልጋዮች ሆይ ከወዴት ናችሁ? በውኑ ጌታችሁን መፍራት እንዲበዛላችሁ የተጋችሁ ናችሁን? ተላላነትና ቅምጥልነት አልወረሳችሁ ይሆን? … ጽኑዓን ሆይ በርቱ! የደከማችሁ ደግሞ  በንስሐ መንገዳችሁን ወደጌታ አቅኑ!
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …

5 comments:

  1. grum meleekit....biblical....God bless you!!!

    ReplyDelete
  2. ጌታ ሆይ እውነተኛ ኢየሱስ ተኮር አገልጋዮችን አስነሳ

    ReplyDelete
  3. አገልጋይ ትጋትና ምጡ፤ እንባውም አማኞች ከሐሰተኛ ወንድሞች በደሙ ቅጥርነት ተከልለው በልባቸው ክርስቶስ እንዲሳልና ዘወትርም ወደክርስቶስ እንዲመለከቱ ማድረግ ነው፤ …. ወንድሜ እጅጉን ልክ ብለሃል

    ReplyDelete
  4. ኢየሱስ የአምላክ አገልጋይ እንደሆነ ሁሉ የርሱን አርአያ መከተል አለብን።

    ReplyDelete
  5. አገልጋይ ትጋትና ምጡ፤ እንባውም አማኞች ከሐሰተኛ ወንድሞች በደሙ ቅጥርነት ተከልለው በልባቸው ክርስቶስ እንዲሳልና ዘወትርም ወደክርስቶስ እንዲመለከቱ ማድረግ ነው፤

    ReplyDelete