Friday 24 February 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ስድስት)

Please read in PDF

5.    ጌታ ኢየሱስ ራሱን እንደአገልጋይ ቆጠረ (ማቴ.20፥28)፤ “እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” በማለት፣ እንደአገልጋይ እንጂ “እንደጌታ” አለመምጣቱን ተናገረ፤ (ማር.10፥45 ፤ ፊል.2፥8)፡፡ ስለዚህም መብቱን ሁሉ ለእኛ ሲል ትቶ፣ ሕይወቱንም ጭምር ሊሰጥ መጣ፤ (ዮሐ.10፥11)፡፡ ኢየሱስ በማገልገሉ እኛ ወደድኅነተ ሥጋ ወነፍስ፣ በሞት ጥላ ሥር በጨለማ ውስጥ የነበርን ሕዝቦች በእርሱ መምጣትና መገለጥ፣ ዝቅ ብሎ እንደባርያ  ማገልገል ወደሚደነቅ ብርሃንና ወደበዛ ሕይወት መጣን፤ አገልጋይ ለራሱ እንደማይኖር ጌታ ኢየሱስም ለአባቱ ትእዛዝና ፈቃድ እንጂ ለራሱ አልኖረም፤ ይህንንም በአንደበቱ፥ “አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ” “እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” (ዮሐ.14፥31 ፤ 15፥10) ሲል ተናገረ፡፡

    ሥጋ በመልበሱ “ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረው ጌታ”(ዕብ.2፥9)፣ በአገልጋይነቱ ዝቅታ አብን ፈጽሞ ታዝዟል፤ ደስም አሰኝቷል፡፡ ክርስቶስ በጽደቅ ሕይወቱ ለአባቱ “እንደባርያ” በመታዘዝ ፍጹም ሰውነቱን አሳይቷል፡፡ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥” እንዲልም፣ መታዘዙ በነገር ሁሉና የአባቱን ፈቃድ በሚያስከብር ኑሮ ጭምር በመኖር ነበር፡፡ ወገኖቼ! በአገልጋይነታችሁ የአባታችሁን ፈቃድና ታላቅነት በሚያስከብር ትምህርትና ሕይወት መኖር ካልቻላችሁ መንገዳችሁንና ትምህርታችሁን በንስሐ መርምሩት፡፡ አዎን! ክርስቶስን የምታምኑ ሆይ! የተጠራችሁበትን ስም የሚያስከብር ኑሮ ኑሩ፡፡
    አዎን! አገልጋይ ምንም መብት በራሱ ላይ የለውም፤ በጌታ ዘመን የነበረው የባርያ አስተዳደር፥ ጌታው እስከገዛው ድረስ ሙሉ ለሙሉ ለጌታው ፈቃድ ኗሪ እንጂ፣ ለራሱ ምንም መብት ያልነበረው ነበር፤ ስለዚህም በዋጋ ተገዝቷልና ሙሉ ለሙሉ የጌታው ንብረት ነው ማለት ነው፡፡ እኛም “በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፤” “በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ[እንደተገዛችሁ] ታውቃላችሁ” (1ቆሮ.6፥20 ፤ 1ጴጥ.1፥18) እንዲል፣ በስሙ ያመንን በጌታችን ኢየሱስ በደሙ ዋጋ ተገዝተናል፤ ስለዚህም ክርስቶስ አድርጉ ያለንን ማድረግ፣ ካደረግንም በኋላ ራሳችንን እንደማይጠቅም ባርያዎች ልንቆጥር ይገባናል፤ [ምስጋና እንደሚገባን ልንቆጥር አይገባንም ማለት ነው] የፈጸምነው ግዳጃችንን ነውና፡፡
     በማናቸውም ነገር ክርስቶስ አድርጉ ካለን አንዲት ቃልና ነቁጥ ሳናጎድል ልናደርገው ይገባናል፡፡ ሁል ጊዜ ኢየሱስ አገልጋዩ መሲሕ ቢሆንም፣ አምላካዊ ሥልጣን ያለው ፍጹም ፈራጅና ዋጋ አደላዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” (ማር.13፥31) ያለውን አምላክና ጌታ በዘመናችን ሁሉ መዘንጋት የለብንም፡፡
6.    አገልጋይ ትጉህ፣ ንቁና ሥልጣኑንም  በአግባቡ ሊጠቀም ይገባዋል፤ (ማቴ.24፥45) ማገልገል መልካም ነው፣ ኤጲስ ቆጶስነት በተመለከተ፣ “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው” (1ጢሞ.3፥1) የሚለው የአገልጋይነትን መልካምነት ያመለክታል፤ ዳሩ ደግሞ መትጋትን መዘንጋት የለብንም፤ ብዙ የተቀበለ ብዙ ከእርሱ ይጠበቃልና አጥብቆ ሊያገለግል ይገባዋል፤ (ሉቃ.12፥45)፡፡ እንዲያውም ለአገልግሎቱ [ለሥራው]ምሥጋና ሳይጠብቅ፣ ከእርሱ ዘወትር የሚጠበቀውን ማድረግ አለበት፤ ተግባሩን መፈጸም ግዴታው ነውና፤ (ሉቃ.17፥10) ተግቶ ቢያገለግል እንኳ ክብሩን ለራሱ መውሰድ የለበትም፤ ተግተው አገልግለው ምንም ክብርና ሽልማት እንደሌላቸው(ማቴ.7፥23) ሰዎች መሆን የለበትም፡፡ ቅዱስ ቃሉም፣ “ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (2ዮሐ.8)፣ በማለት የሚያስጠነቅቀን በምድር በታማኝነት ላገለገልነው አገልግሎት ሙሉ ደመወዛችንን እንዳናጣ ነው፡፡
      አገልጋይ ክርስቶስ የሰጠውን ማናቸውንም ሥራ በንቁነትና በትጋት ሊሠራ ይገባል፡፡ ትንሹን ኃላፊነትን ችላ ማለት የለበትም፡፡ መክሊት መቅበር ወይም ያለማትረፍ ወይም ያለመመስከር ስንፍና በክርስቶስ መንግሥት ከባድ ቅጣት አለው፡፡
     ጌታ በምድር ሳሉ በስሙ አገልግለው ነገር ግን መከበር መሞገስና መወደስን በምድር ከሰዎችና ከአጋንንት የወሰዱትን አገልጋዮች በሰማይና ምድር ሁሉ ፊት እንደማያውቃቸው በግልጥ ተናግሯል፤ (ማቴ.7፥23)፡፡ በእርግጥም፣ ባርያ ካገለገለው ጌታ በቀር “ከሌላ ጌታ” ደመወዝና መከበርን ፈጽሞ አይጠብቅም፡፡ የምናገለግለው በትክክል ጌታ ኢየሱስ መሆኑን በትምህርታችን ካልመሰከርን ድርጊታችን ጠማማ ሹመት፤ ሽልማታችንም ከክፉው ነው፡፡ አደገኛ ጋኔናዊ ድርጊቶች ምንጫቸው የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡ አገልጋይ ለዚህ ተላልፎ የሚሰጠው የተሰጠውን የአገልግሎት “ሥልጣን” ወሰኑን በመተላለፍ ራሱን በጌታው ቦታ ሲሾም፣ በሌላው ሸክላ ላይ መሰልጠን ሲፈልግ ነው፤ ከጌታ ኢየሱስ ውጪ ሌሎች ጌታ የሚገለጡትና አገልጋይ የሚስተው በዚህ ሰዓት ነው፡፡
   እንዲያውም አንድ ሸክላ በሌላ ሸክላ ላይ ሊኮራ አይገባውም፤ ሠሪው እንዳፈለገው ሊያደርገው ይቻለዋልና፡፡ አንድ አገልጋይም በሌላ ተገልጋይም ሆነ አገልጋይ ላይ ሊመካና ሊኩራራ መጀመር የለበትም፡፡ ይህ ዋዘኛና ተላላ ከማድረግም በላይ ለትዕቢት አሳልፎ ይሰጣል፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …


4 comments:

  1. ወዳጄ ዘመንህን እግዚአብሔር ይባርክልህ፤ ተባረክ

    ReplyDelete
  2. እጅግ አስተማሪ ጽሁፍ ነው፤ በርታ እደግ ተመንደግ

    ReplyDelete
  3. የምናገለግለው በትክክል ጌታ ኢየሱስ መሆኑን በትምህርታችን ካልመሰከርን ድርጊታችን ጠማማ ሹመት፤ ሽልማታችንም ከክፉው ነው፡፡ አደገኛ ጋኔናዊ ድርጊቶች ምንጫቸው የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡

    ReplyDelete
  4. thank you lord for this blog.

    ReplyDelete