Monday 2 January 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ“አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ሁለት)

2.  ጫውን በአገባቡ ወይም ዓይኑን ከመሙ[ከመሮጫው መስመር] ሳይነቅል መሮጥ፦ የሯጭ የዘወትር ተግባር ነው፤ ከመስመሩ ዓይኑን ፈጽሞ መንቀል የለበትም፡፡ ከመሙ ወጥቶ ሮጦ ቢያሸንፍ እንኳ አሸናፊነቱ ይሰረዛል፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ወደክርስትና ሕይወት ሩጫ በመቀየር፥ “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤”(ዕብ.12፥2) በማለት ገልጦታል፡፡
   በሩጫው ዓይናችንን ፈጽሞ ከጌታ ልናነሳና ምድራዊ ነገሮች ላይ [እጅግ ጠቃሚ ቢሆኑም እንኳ] ልናደርግ አይገባንም፡፡[1]  ክርስቶስን በትክክል እያየን ሩጫችንን ልንሮጥ ይገባናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ክርስቶስን ልክ በፊታችን እንደተሳለ እንዳናየው የሚያደርግ አዚም ሊኖር ይችላል፤ ልክ የገላትያ ክርስቲያኖች፥ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ.3፥1) እንደተባሉ፥ እኛም የአዕምሮ ችግር ሳይኖርብን ክርስቶስን መረዳት ሲሳነን፥ ለእርሱ ሥራ ቸለተኞች ስንሆንና ሩጫችንን እርሱን ፊት ለፊት ባለማየት ስንመላለስ ወዳለማስተዋል አዚም ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡

    ስለዚህ በማናቸውም ሁኔታ ከዋናው ነገራችን ላይ ዓይኖቻችንን ለዓይን ጥቅሻ እንኳ ልንነቅል፤ ሩጫችንንም ልናስተጓጉል አይገባንም፤ በሰማይም በምድርም ያለ ነገር ቢገጥመን እንኳ፡፡ ጌታ ኢየሱስ እርሱ ዋናችንና ትክክለኛው የሩጫችን መሪ ነው፡፡
3.  ደኋላ የሚስቡና ፍጥነታችንን የሚያዘገዩ ነገሮችን ማስወገድ፦ አንድ ሯጭ በሩጫው ወቅት ወደኋላ የሚስቡትንና የማያስቸኮሉትን ነገሮችን መተው ወይም ማስወገድ ይገባዋል፡፡ ሁላችን እንደምናውቀው አንድ ሯጭ ትጥቁ አጭርና ቁጥብ ነው፡፡ ብዙ መልካም ነገር ያለው ቢሆንም እንኳ፥ እጅግ በጣም ጥቂቱንና አስፈላጊውን ብቻ ነው የሚጠቀመው፡፡ በሌላ ንግግር የማያስፈልገውን ልብስና ጌጥ ፈጽሞ ያወልቃል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ሩጫም ስህተትና ኃጢአት ያልሆኑ ነገሮች እንኳ ለሩጫ የማያስፈልጉበት ወቅት ብዙ ነው፡፡ ሩጫውን በፍጥነት መሮጥ ይገባናል፡፡ በፍጥነት እንዳንሮጥ የሚገታንን ማናቸውንም ነገሮች ማስወገድና መቁረጥ አለብን፡፡ ከሁሉም ነገር ይልቅ ኃጢአት ሩጫችንን ይገታል፤ አብዝቶም ወደኋላ ይይዛል፡፡ ስለዚህ ከጥቃቅኖቹና ስውር ኃጢአቶች ሁሉ ሳይቀር በመጠበቅ ሩጫችንን መሮጥ ይገባናል፡፡
    ዘወትር መርሳት የሌለብን እውነት፥ በሩጫው እንዳንተጋና ተሰናክለን ከመንገድ እንድንቀር የሚያደርገን ክፉ ጠላት አለብን፡፡ እርሱም ኃጢአትና የኃጢአት አባት ዲያብሎስ ናቸው፡፡ ስለዚህም ኃጢአትንም ሁሉ በማስወገድና የኢየሱስን ቃል በማሰብ (ዘሌ.19፥11 ፤ መዝ.4፥4 ፤ 15፥2 ፤ ኢሳ.63፥10 ፤ ዘካ.8፥16 ፤ ማቴ.5፥22 ፤ 12፥36 ፤ ሐዋ.20፥35 ፤ ሮሜ.8፥23 ፤ 12፥5 ፤ 14፥19 ፤ 2ቆሮ.1፥22 ፤ 2፥10 ፤ 5፥5 ፤ ገላ.6፥10 ፤ ኤፌ.5፥4 ፤ ቈላ.3፥8-9) መሮጥ አለብን፡፡  ኃጢአት ለጽድቅ እንዳንቻኮል እግር ያዥ፤ ሰኮና ነካሽ ክፉ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ያለንን ሞገስና መወደድ ከሚያጠለሹ ነገሮች አንዱና ዋናው ኃጢአት ስለሆነ ቆርጠን በንስሐ ማስወገድ ግድ ያስፈልገናል፡፡
     ኃጢአት ምንም ቁልምጫ የማያስፈልገው ነው፡፡ ለየትኛውም ኃጢአታችን ያለድርድር ንስሐ በመግባት ሩጫችንን በንስሐ ማደስ፤ መንገዳችንን፣ ሕይወታችንንና ቤታችንን ልናስተካክል ይገባል፡፡
4.  ከንቱ አንሮጥም፦ በመንፈሳዊው ዓለምም ወደክርስቶስ በምንሮጠው ሩጫ፥ “ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አንሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አንጋደልም”፡፡ ቃሉ እንደሚለው፥ ግብና ዓላማ ለሌለው ነገር ዝም ብለን አንሮጥም፡፡ ይልቁን በነፍሳችን ተወራርደን የምንሮጥለትና የምናገለግለው አባትና አምላክ አለን እንጂ፡፡ ስለዚህም የሚከብደንን ሸክም ሁሉ፥ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ”(ማቴ.11፥28) ላለን ጌታ በማስረከብና፥ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነና በድካማችን ወደሚራራልን ሊቀ ካህናት”(ዕብ.4፥17) በመቅረብ ሩጫችንን በጽናት ልንሮጥ ይገባናል እንጂ ዝም ብለን ልንሮጥ አይገባንም፡፡
    “ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን[ሽልማቱን] እንዲቀበል”(1ቆሮ.9፥24) የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በክርስትና ሕይወት ሩጫውን በእምነትና በጽናት የሚሮጡ ሁሉ አሸናፊና የዘላለም ሕይወት ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ ሁሉም አሸናፊዎች የሚሆኑት አንደኛ እንዲወጡ በማመን ሳያቋርጡ መሮጥን ሲሮጡ ነው፡፡ በክርስትና ሕይወት ሩጫ ሯጮች ሁሉ ልክ አንደኛ ለመውጣት እንደሚሮጥ ሯጭ፣ በእምነት ጉልበት ሳናቋርጥ መሮጥ ይገባናል፡፡ ሽልማቱ ለሁሉ እንደሆነ እንዲሁ፥ አሸናፊዎቹ ሁሉም ናቸው፡፡ ስለዚህ ለአንደኛ መሮጥ እንደሚገባ እንጂ በከንቱ መሮጥ አይገባል፡፡
    በክርስትና ሕይወት ሩጫ ሁለተኛ አሸናፊ የሚባል ነገር[ከንቱ ሩጫ] የለም፤ የምንሮጠው ሩጫ ለክርስቶስና ለወንጌሉ ነውና፥ በራሳችን እንደምንሮጥ ማሰብ የለብንም፡፡ በእርሱ ጉልበትና ኃይል በጸጋውም ብርታት የምንሮጥ ከሆነ፥ ሁላችን አሸናፊዎች ሁላችን ተሸላሚዎች ነን፡፡ ሩጫን ከጸጋና ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ጋር ማያያዝ አይገባም፤ ልጆቹ ብቻ ስለሆንና እርሱን ስላመንን መሮጥና በሕይወታችን ምስክርነቱን መግለጥ እንጂ፡፡ ይህንን ካደረግን ሩጫችን ፈጽሞ ከንቱ አይደለም፡፡
5. ብዙ ድካምና ልምምድ ለሩጫው ራስን ማስለመድ፦ ሯጭ በብዙ ድካምና ልምምድ ራሱን ያሰለጥናል፤ ስለዚህም ነገር ሲል ብዙ ነገሩን ይተዋል፡፡ ወዙና ላቡ ቢንጠበጠብም፣ ጅማቱ ቢኮማተርም፣ ፊቱ ቢጨማተርም፣ ... ከልምምዱና ከሩጫው ፈጽሞ አይዘናጋም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሃሳብ፥ “ ... የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤... ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ፤”(1ቆሮ.9፥27) በማለት በብዙ ልምምድና ማሰልጠን ራስን ማስገዛት እንደሚገባ አበክሮ ይናገራል፡፡ ራሱን አጽንቶ ለሩጫው ባያስገዛ መጣል[አክሊል ማጣት] ሊመጣ እንደሚችል በሚገባ ይናገራል፡፡
    በሩጫው ራስን ማስገዛት እንዳለ እንዲሁ፥ ከመንፈስ ፍሬ አንዱ የሆነውም ራስን መግዛት(ገላ.5፥22)  በክርስትና ሕይወት የክርስቶስንና የወንጌሉን ሩጫ ከሚሮጥ አማኝ ይጠበቃል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን የካደና ሰውነቱን የራሱ ባርያ አድርጎ ለጽድቅ ያስገዛ ቢሆንም እንኳ፥ በብዙ ጥረትና በጽናት መሮጥን እንጂ ፈጽሞ ከውድድር ውጪ መሆንን አይፈልግም፡፡ እንዲያውም ለሩጫው አጥብቆ በመሮጥ ውስጥ ለሚገኘው ራስን መግዛት እንደሚተጋ ይናገራል፡፡
     በሌላ ሥፍራም፥ “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤” (ዕብ.12፥4) በሚለው ቃል ውስጥ፥ ሁሉን ነገር አድርገን ነገር ግን ኃጢአትን በመቃወምና በእምነታችን እስከሞት ድረስ በሚያደርስ መታመን ባንጸና ሩጫችንና ትጋታችን ሁሉ ከንቱ ይሆንብናል፡፡ ስለዚህ በሩጫችን ራስን ለዚህ ነገር ማስለመድና ማሰልጠን እስከምን ድረስ ነው? ብንል፥ እስከሞት ድረስ በማለት በድፍረት እንናገራለን፡፡ ስለዚህም የምንሮጠው፦
       እግዚአብሔርን እስከመምሰል ድረስ ነው፤ “እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ” (1ጢሞ.4፥7) “ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” (ቲቶ.2፥12)፡፡ ይህም በክርስቶስ በደሙ ኃይልና በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ነው፡፡
       መጽናት ምንድር ነው? ቃሉ እንዲህ ይላል፥ “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ፤” (1ቆሮ.15፥58) እንዲል፥ መጽናት ማለት በከባድ ትግልና ውጥረት ውስጥ ጸንቶ መቆምና መደላደል፤ ብሎም በዚያም በጸኑበት ነገር መደሰት ነው፤ (ሐዋ.20፥35)፡፡
     ወዳጆቼ! ይህን ብርቱ ሐዋርያ አስተውላችሁታልን? ምንም ያህል በእግዚአብሔርና በዙፋኑ ፊት የበረታ ቢሆንም፥ አሁንም መጣርና በክርስትና ሕይወቱ ሩጫውን በሚገባ መሮጥ እንዳለበት ያምናል፡፡ እንኪያስ እኛ በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ያለን እንዴት አብዝተን መሮጥና ተግተን ሩጫችንን መፈጸም አይገባንም?! ክርስቶስ እንከተላለን የምንል “ክርስቲያኖች”፥ በእውነት በሩጫችን የምንመለከተው ክርስቶስን ብቻ ነው? ከፊታችን የተሳለውና ዘወትር የሚታየው እርሱ ብቻ ነው? ወደሰባኪ ማድነቅ፣ “ስብከቱን” ሽምጥጥ ብሎም በመከተል ቃሉን ከማጥናትና ከማሰላሰል አልተዘለልንም? እንዲያውም ከክርስቶስ ቃል ይልቅ የሐሰት መምህራንን ቃል በመስማት የምንታለል አይደለንምን? ሌሎቻችን ደግሞ ከሩጫችን ተዘናግተን፥ የምናደንቀው ሰባኪ በዋለበትና ባደረበት ለመገኘት ብኩኖች አይደለንምን? ሰባክያንስ ሰዎች በእኛ ዙርያ ሲሰበሰቡ ወይስ ለክርስቶስ ሲማረኩ ደስ ይለን ይሆን?
      ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! የክርስትና ሕይወት ሩጫችንን ከክርስቶስ ጋር እንድንሮጥ እርዳን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል…




    [1] ጌታ ኢየሱስ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤”(ማቴ.10፥37) በማለት የተናገረው፥ ሰው ለጌታ ሲል ሁሉን መተው፣ የገዛ ሕይወቱን እንኳ መጥላት[መካድ] እንዳለበት እና ክርስቲያን[የክርስትና ሕይወት ሩጫ ሯጭ] ሁሉ ለደቀ መዝሙርነት የተጠራ መሆኑን በግልጥ ያሳያል፥ እንጂ አያስፈልጉም የሚል ሃሳብ በውስጡ የለውም፡፡

1 comment:

  1. Elelelelelelelelelelellelelelleleelel des yilal

    ReplyDelete