Wednesday 18 January 2017

ጌታ ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? (ክፍል አንድ)

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሲሕነቱን አገልግሎት በግልጥ የጀመረው በጥምቀቱ ዋዜማ ነው፤ በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት መሲሑ እንደተነገረው፥ “የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ፡፡ ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና” (ኢሳ.40፥3-5) ተብሎ የተነገረው ትንቢት በተፈጸመ ማግስት ነው፡፡


    ነቢዩ ኢሳይያስ በጩኸት የሚጣራውን ድምጽ ሰምቶ ማንነቱን መግለጥ ባይቻለው፥ በአዲስ ኪዳን ግን ይህ ድምጽ በመጥምቁ ዮሐንስ አንደበት በንስሐ ግቡ ጩኸቱና በምስክርነቱ ተረጋገጠ፤ (ዮሐ.1፥20)፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የእስራእል ሕዝብ መመለስ እንዳለባቸው በመንገድ[በዋና አውራ ጐዳና] መስሎ ይናገረዋል፡፡ ዝግጅቱ ተራ ዝግጅት ሳይሆን ታላላቅ መሰናክሎችንና እንቅፋቶችን ሁሉ የማስወገድ ሥራን ያካትታል፡፡ መመለስ የልብ ዝግጅትና የሄድንበትን የክፋትን መንገድ ሙሉ ለሙሉ ማስወገድን የሚያመለክት ሃሳብ ነው፡፡ ንስሐ የልብ ውሳኔንና የምንሠራውን ክፋት ሙሉ ለሙሉ መተውንና ማስወገድን ያመለክታል፡፡ እውነተኛ መመለስ በአንደበት የሚነገረው ሳይሆን በራስ ላይ እርምጃን በመውሰድ መወሰን መቻልን አመልካች ድርጊታዊ ምላሽን መስጠት ነው፡፡
      መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ለአንድ ንጉሥ ሊደረግ እንደሚገባ ቅድመ ዝግጅት እንዲሁ ኢየሱስን ለመቀበል መዘጋጀት እንደሚገባ ተናገረ፤ አንድ ንጉሥ አንድን ሥፍራ ከመጎብኘቱ በፊት አገልጋዮቹ ቀድመው መንገዱን ሁሉ እንደሚያዘጋጁ፥ ለመሲሑ ንጉሥ እንቅፋት የሆነውን ኃጢአት ሁሉ ማስወገድና ማጥራት ይገባል፡፡ በሕይወት ጉዞ እንደኮረብታ ከፍ ያለ ትዕቢት፣ ከእኔ በቀር ማንም የለም የሚል ኩሩ መንፈስ እንዲፈርስ፤ በአለማመመን የተሞላ ሸለቆው ልብ፣ በአለመታዘዝ የተመላው የሕሊና ጠማማነት፣ ውሽልሽልና ጽዱ ያልሆነው ስርጓጉጥ ሕይወት ለጌታ ኢየሱስ የሚመች ደልዳላ እንዲሆን መጥምቁ መልእክተኛ ሆኖ ተልኳል፡፡ ይህ በተፈጸመ ጊዜም የእግዚአብሔር ክብር በሕይወታችን ይገለጣል፡፡
    በነቢዩ ትንቢት እስራኤል ከባቢሎን ምርኰ ነጻ እንደምትወጣ፥ መውጣቷንም አሕዛብ ሁሉ እንደሚያዩ፥ በዚህም የታዳጊው የእግዚአብሔር ክብር እንደሚገለጥ በግልጥ ይናገራል፡፡ በፍጻሜው ትንቢት ግን፥  ጌታ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሁሉ በሚሰጠው ነጻነት የእግዚአብሔር ክብር በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ይታያል፡፡ ይህም ክብር እኛ በመታዘዝ ሕይወት ክርስቶስን እንመስልበት ዘንድ የተጠራንለት ነው፤ (1ጴጥ.2፥21)፡፡ ለዚህም ዋና መረሳት የሌለበት ትልቅ እውነት  ልቡናን በንስሐ ማደላደልና ማዘጋጀት ይገባል፡፡
     መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ መንገድን[የገዛ ልባችንን] ለጌታ ኢየሱስ እያስተካከለ ባለበት ወራት፥ ጌታ ኢየሱስ የመሲሕነቱን አገልግሎት ሊጀምርና ሊጠመቅ “ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ”፤ (ማቴ.3፥13)፡፡ በዚያም ተጠመቀ፤ ጌታ ኢየሱስ ግን ስለምን ይሆን መጠመቅ ያስፈለገው?
1.    ሲሐዊ አገልግሎቱን ይፋ ያደርግ ዘንድ፦ የትኛውም ሌዋዊ አገልጋይ “ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠራ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገባበት” ጊዜ ነው፤ (ዘኊል.4፥3)፡፡ ጌታ ኢየሱስ “ሕግንና ነቢያትን ሊፈጽም እንጂ ለመሻር ያልመጣ” (ማቴ.5፥17) ነውና፥ እንደሕጉ ቃል ይፋዊ አገልግሎቱን በመጠመቅ ጀመረ፡፡
     ጌታ ኢየሱስ ይህን ይፋዊ መሲሐዊ አገልግሎት መጀመሩን መጥምቁ ዮሐንስ፥ “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው፡፡ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ፤ (ዮሐ.1፥30-31) በማለት ገልጦ ተናገረ፡፡
    ቅዱስ ዮሐንስ ዘመኑን የፈጀው በምድረ በዳ ነውና፥ ጌታ ኢየሱስ ለእስራኤል ሁሉ እስኪገለጥ ድረስ ጌታን እንደማያውቀው ተናገረ፡፡ በአንድ ወቅት መልአኩ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም የነገራት ሁሉ በእርግጥ እውነት እንደሆነ ምልክት ይሆናት ዘንድ፥ ይኸው ቅዱስ ሕጻን በእናቱ ማኅጸን ሳለ ዘልሎ ነበር፤ (ሉቃ.1፥41)፡፡ ባደገ ጊዜ ግን አላወቀውም፤ መንፈስ ቅዱስ በዘመናት የሚያስደንቅ ሥራን ይሠራል፤ ሰው በመዘንጋት ይያዛል፤ እርሱ ግን ፍጹምና ከማሰብም የማይዘነጋ ነው፡፡
    በኋላ ግን፥ “ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ፡፡ እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ፡፡ እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ፤ (ቁ.32-34) በማለት ምልክቱን ካየ በኋላ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ደፍሮ አላውቀውም ስላለው ጌታ ጮኾ ተናገረ፡፡ ቀድሞ ለጥምቀቱ ከመምጣቱ በፊት የማያውቀው ቢሆንም እንኳ፥ ባየውና ምልክቶቹን በተመለከተ ጊዜ ግን መሲሕነቱን አምኖ ተቀበለ፤ መሰከረም፡፡ ክርስትና ከእውቀት የሚያውቅ መገለጥ ማለታችን ለዚህ ነው፤ እውነተኛ መገለጥ ከእውቀት ያልፋል፤ በእውቀት ደግሞ የቱንም ያህል ከጫፍ ላይ ብንደርስ ክርስቶስ በመገለጡ ካልጐበኘው ከመታበይ በቀር ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በመገለጡ የገሊላ አላዋቂዎች የመሲሑ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል፤ በእውቀት ብቻ የነበሩት ሊቃነ ካህናት ሐናና ቀያፋ ግን ተቺና አራቂ እንጂ ለሕይወት ሽታ የተገቡ አልነበሩም፡፡
    መሲሑ ለእስራኤልና ለሳምራውያን ሁሉ የሚጠበቅ ትልቅ ናፍቆት ነበር፤ መናፈቅ መራብና መጠማት አለበት፤ ለዘመናት መጓጓት ደግሞ ረሃብና ጥሙን ይበልጥ ያረዝመዋል፡፡ የፍጥረት  ሁሉ ዓይኝ ሊያየው የናፈቀውና የጓጓው የመሲሑን ዓይኖች ማየትና በእርሱ ማረፍን ነው፡፡ አረጋዊ ስምዖንና የፋኑኤል ልጅ ሐና የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቁና የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ[ክርስቶስ] ይናገሩ የነበረው በውስጣቸው የነበረውን ናፍቆት በዓይኖቻቸው ዓይተው ስለጠገቡና ስለረኩ ነው፤ (ሉቃ.2፥25 ፤ 38)፡፡ ዛሬ የእኛ ዓይኖች ምንን ለማየት ይናፍቃሉ? ይጓጓሉ? መሲሑን ለማየት የማትናፍቅ ዓይናነ አገር ከመቅበዝበዝና እንደተላላ ከመንገድ ዳር ቆማ የአላፊና አግዳሚው መተረቻና መዘባበቻ ከመሆን በቀር አንዳች ዕረፍት አይሆንላትም፡፡
      ለቅዱስ ዮሐንስ የመሲሑ ሌላው ዋና መገለጫ፥ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ.1፥29) በመሆን መታየቱ ነው፡፡ መሲሑ ኢየሱስ ለመታረድ እንደበግ የተነዳ ነው፤ (ኢሳ.53፥7 ፤ ሐዋ.8፥32)፡፡ መሲሐዊ አገልግሎቱን መጀመሩ፣ ለመሥዋዕትነት ወደመስቀል እየፈጠነና “ስለ ኃጢአት መሥዋዕት በማድረግ” (ኢሳ.53፥10)  የሰዎችን ሁሉ[እኛን ሁላችንን] ኃጢአትን ሊያነጻ መውደዱንና መፍቀዱንም ያሳያል፡፡
    መሲሐዊ አገልግሎቱን ሊገልጥ ተጠመቀ ስንል፥ የተመሰከረለትንና እግዚአብሔር አብ እንድንኖረው የወደደውን ሕይወት በሰውና በእግዚአብሔር በመፈጸም ሊያሳይና በሞቱ መሥዋዕትነት ለሰዎች ሁሉ ድኅነትን ይሰጥ ዘንድ “ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራችና ከኃጢአታቸውም” ፍጹም አዳኝ ሆኖ መጣ፤ (ማቴ.1፥21 ፤ ሉቃ.2፥11)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ በትክክል ተረድቶታል፡፡ መሲሕና የእግዚአብሔር ልጅነቱንም ፍጹም አምኗል፡፡ ኢየሱሰን በትክክል ለመረዳት ከልብና በትክክል መቅረብ ያስፈልገናል፡፡
   አዎን! ይናፈቅ የነበረውን ተወዳጁን፥ “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል” (ዮሐ.1፥46)፡፡ ያገኛችሁት እንኳን ደስ አላችሁ! ያላገኛችሁት እርሱ ኃጢአተኞችን ሁሉ ከነሸክማቸው የሚያቀርባቸውና የሚቀበላቸው የፍቅር አምላክና ወዳጅ ነውና ልትቀርቡትና ልትቀራረቡት ፈጽማችሁ አትፍሩት፤ ቅረቡት ቅመሱትም፡፡
ተወዳጆች ሆይ! የክርስቶስ ፍቅርና መጽናናት ይብዛላችሁ፤ አሜን፡፡

ይቀጥላል …

2 comments:

  1. ሲጽፉ የማይሰለቹ እጆችህን አምላክ ይባርክልህ ወድጄዋለሁ ጽሁፍህን ተባረክ አቦ

    ReplyDelete
  2. God bless you!!! where is the next part, interesting reading!

    ReplyDelete