Friday, 20 January 2017

ጌታ ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? (ክፍል ሁለት)

Please read in PDF
2.   ገረ ሥላሴን ለማብራራትና ለዓለም ሁሉ ለመግለጥ፦ ትምህርተ ሥላሴ በመጽሐፍ ቅዱስ በምልዐት የተብራራ ትምህርት ነው፡፡ በተለይም ትምህርቱ በግልጥ የተሰበከው፤ በጉልህ የታየውና የተረዳው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሐዊ መገለጥ[በጥምቀቱ] ጊዜ ነው፡፡

     አስተርእዮው[መገለጡ] የራእያት፣ የሕልሞች፣ የትንቢታት፣ የምሳሌዎች ሁሉ መከተቻና ማብቂያ ሆኖ(ዕብ.1፥1) የተገለጠ ነው፡፡ ታላላቅ ትምህርቶችና መገለጦች ታላቁንና ወደር የለሹን መምህር ጌታ ኢየሱሰን ጠብቀዋል፡፡ ነቢያትና ሌሎችና ቅዱሳን ካዩትና ከሰሙት ጥቂት ነገር ተነስተው ሲናገሩ፥ ጌታ ኢየሱስ ግን ልናስተውልና ልናውቀው  በምንችለው መጠን ልክ የባሕርይ አባቱንና የባሕርይ ሕይወቱን መንፈስ ቅዱስን፤ ስለራሱም ገልጦ አስተማረን፡፡ ጌታ ኢየሱስ የሥላሴን ትምህርት በሦስት ዋና ዋና መንገዶች “መስክሯል” ማለት ይቻለናል፡፡ ኸውም፦
2.1.      በመገለጡ፦ በብሉይ ኪዳን እጅግ በጣም በጥቂቱ እንጂ፥ ለዘመናት ተሰውሮ የነበረውን ነገረ ሥላሴ በክርስቶስ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅና በታቦር ተራራ ክብሩን ሲገልጥ በግልጥ ተብራርቷል፤ (ማቴ.3፥16 ፤ 17፥1-5)፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች ላይ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በተለየ አካላቸው በሦስትነት፥ የሰው ልጅን ለማዳን በአንዲት ፈቃዳቸው ተገልጠዋል፡፡ (ስለመገለጥ በሌላ ሰፊ ርዕስ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን)
2.2.     በታላቁ ተልዕኰ ውስጥ፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” (ማቴ.28፥19)፡፡ ሦስቱ ስሞች[አንድ አምላክ] ቤተ ክርስቲያን ታላቁን ተልዕኮ የምትፈጽምበት ዋና የአዋጅ ቃሏ እንደሆነ በጉልህ ተቀምጧል፡፡
    ቤተ ክርስቲያን  ሰዎችን ወደክርስቶስ አካል ለመጨመር የሥላሴን ትምህርት አጽንታ መመስከርና መያዝ ይገባታል፡፡ ያለ ሥላሴ ትምህርት ክርስትና ክርስቶሳዊ መሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡ ስለሥላሴም ደፍሮ የማይመሰክርና በሥላሴም የማያምን እርሱ ቁጥሩ ከመናፍቃን ነው፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክርሰቲያን በየዘመናቱ የሥላሴ ትምህርትን የሚቃወሙ መናፍቃንን በየጊዜው ከመጽሐፍ ቅዱስ ወሰንና ድንበር ሳትወጣ፥ መልስ በመስጠት የመናፍቃንን ትምህርት በመለየት እውነትን ስታጸና የኖረችው፡፡
     ታላቁን ተልዕኮን በአብ፣ በወልድና መንፈስ ቅዱስ ስም ብቻ እንጂ፥ በማንም ስም እንዳናደርግ አምላካዊ ትዕዛዝን ከክርስቶስ ተቀብለናል፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት ላይ ቆመን የትኛውንም መንፈሳዊ አገልግሎት በተገለጠ ስሙ ልናደርገው ይገባናል፡፡
2.3.     በትምህርቱ፦ ክርስቶስ በሚያስተምረው ትምህርቱ ሁሉ እግዚአብሔር አብ የባሕርይ አባቱ መሆኑን ደጋግሞ ያለመታከት ተናግሯል፡፡ በግልጥ ቃልም፥ “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐ.1፥18) የተባለለት ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከአምላክ በቀር በአምላክ እቅፍ መኖርና በትክክል ስለአምላክ ሊተርክ የሚቻለው ከክርስቶስ በቀር ፈጽሞ አይኖርም፡፡ የለምም!
    በትምህርቱም በተደጋጋሚ፥ “አባቴ” በማለትም እግዚአብሔርን አብን ደጋግሞ ጠርቷል፤ ጌታ ኢየሱስ አብን አባቴ ብሎ ደጋግሞ በመጥራቱ፥ የጠራበት መንፈሱ ከአብ ጋር ተካካይነት የነበረው መሆኑን አይሁድ ስለተረዱ በተደጋጋሚ ተቃውመውታል፤ (ዮሐ.5፥14-24 ፤ 6፥32 ፤ 37 ፤ 44 ፤ 46 ፤ 6፥57 ፤ 7፥16-19 ፤ 8፥28)፡፡
     ጌታ ኢየሱስ ስለአብ ብቻ ያይደለ፥ ስለመንፈስ ቅዱስም ብዙ ቦታ ደጋግሞ አስተምሯል፤ (ሉቃ.24፥49 ፤ ዮሐ.14፥16 ፤ 26 ፤ 16፥7-8)፡፡ ከዚህም የተነሳ መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ (ዮሐ.14፥26 ፤ 16፥7)፣ ሌላ አጽናኝ (ዮሐ.14፥16)፣ አስተማሪ መምህር፣ ስለክርስቶስ የሚያስታውስ አስታዋሽ (ዮሐ.14፥26)፣  … በሚል በሌሎችም ስሞች ተጠርቷል፡፡
     እንዲያውም፥ ጌታ ኢየሱስ ሰፊውን የትምህርት ጊዜውን የሸፈነው ስለአባቱ ደጋግሞ በማንሳትና ፈቃዱን ለመፈጸም የመጣ መሆኑን በማውሳት ነው፡፡ ስለዚህም የሥላሴ ትምህርት የትምህርታችንና የመዳናችን ዋና ነገር ስለሆነ በብዙ ልናጠናው፤ አጽንተንም ልንይዘው ይገባናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ቅዱሳን ሐዋርያት በትምህርታቸውና በመልዕክቶቻቸው ትምህርተ ሥላሴን በሚገባ ገልጠው አስተምረዋል፡፡ ለምሳሌም፦
v የመልዕክቶቻቸውን መግቢያ በሥላሴ ስም አሸብርቀው፤ ሠላምታቸውን በሥላሴ ስም ያደርጉ ነበር፤ (ሮሜ.1፥7 ፤ 1ቆሮ.1፥3 ፤ 2ቆሮ.1፥2 ፤ ኤፌ.1፥2 ፤ 1ጴጥ.1፥1)፤
v በመልዕክቶቻቸው ፍጻሜ ላይም መባረክን ሲባርኩ ይጠቀሙ የነበሩት የሥላሴን ስም ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን፥ “እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ፤” (ዘኊል.6፥24-26) በማለት የተጠቀሰው ታላቁ ቡራኬ፥ የእግዚአብሔርን ስም ደጋግሞ እንደሚያነሳ እንዲሁ፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ፥ “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።” (2ቆሮ.13፥14) የሚለው ቡራኬ የታወቀና የተወደደ፤ አሜን ልንልበት የሚገባ ነው፡፡
    ይህ ቅዱስ ትውፊት ዘመናትን አቋርጦ ዛሬም ድረስ የመጣ ነው፤ በትምህርትና በዕውቀት ግን በዛሬው ትውልድ ልቡና የጎለመሰ አይደለምና አብዝተን ልንሠራ ይገባናል፡፡ ሥላሴ የመልዕክታችንና የትምህርታችን  መክፈቻና መደምደሚያ ብቻ ሳይሆኑ፥ የሕይወታችን፣ የነገራችን፣ የትዳራችን፣ የሥልጣናችን … አልፋና ኦሜጋ[ጀማሪና ፈጻሚ] መጀመርያና መጨረሻ ነው፡፡ 
    ብዙዎቻችን ሥላሴን የምንጣራውን ያህል በትምህርት ሥላሴን አናውቅም፡፡ እናምነዋለን የምንለውን እውነት ትናጋችን ተላቆ ካልመሰከረለት ያመንነውን እውነት ያስጠረጥራል፡፡ ካመንን ልንናገር[ልንመሰክር] ይገባናል፡፡ መዝሙረኛውና ሐዋርያው፥ “ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤” (2ቆሮ.4፥13 ፤ መዝ.116፥10) እንዳለ፡፡ ያመነ ሰው ስላመነው ነገር ይመሰክራል፤ አምነን በፍቅር የማንናገርለት እምነትም ይሁን ሃይማኖት ዲዳ ነው፤ ጮኸን የምንመሰክርለት እምነታችን ግን ከጠላት ምርኮን ይበዘብዛልና ሥላሴን የምታምኑ ሆይ! ትምህርቱን አሰምታችሁና ጮኻችሁ ተናገሩ! አስተውሉ! ጸሎትና አምልኮ፤ ዝማሬና ሽብሸባ የክርስትና ዋናዎች ሳይሆኑ አንድ ክፍሎች ናቸው፤ እንደነገረ ሥላሴ ያሉ ጠንካራና መሠረታውያን የሆኑ ትምህርቶችን ማናናቅና ትልቁን ቦታ አለመስጠት ለዘመነኞቹ የሐሰት መምህራን በገዛ እጅ ራስን ለምርኮ አሳልፎ መስጠት ነው!
v ትምህርተ ሥላሴ የመዳናችን መሠረት መሆኑንም ቅዱሳን ሐዋርያት በመልዕክቶቻቸው ገልጠዋል፡፡ አብ ፍጹም ዓለሙን እንዲሁ ወድዷል፤ ልጁንም ስለመዳናችን ሰጥቷል፤ (ዮሐ.3፥16 ፤ ሮሜ.8፥32 ፤ 1ዮሐ.4፥1)፥ ወልድ ደግሞ በሞቱና በትንሣኤው ምሕረትንና እውነትን አገናኝቶ (መዝ.84፥10) ዓለምን አድኗል፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተፈጸመውን መዳን ለሰው ሁሉ ያደርሳል፤ (ዮሐ.14፥16)፡፡
     በመሲሑ ጥምቀት የተብራራውና የተገለጠው ነገረ ሥላሴ የእግዚአብሔርን ማንነት በማወቅና በመረዳት እንድንጸና ተገልጧል፡፡ አዎን! ነገረ ሥላሴ በመሲሑ መገለጡ ያመንን እንድንጸና እንጂ ለክርክር ምላሽ ይሆነን ዘንድ አይደለም፡፡ ክርክር እንዳይኖርበት ለዓለሙ ሁሉ ተገልጧል፤ ይሕኝ እውነት ሊቀበል ያልወደደ በአጋንንት ትምህርት ተታለለ፤ ፈቃዱንም ተከተለ እንጂ የነገረ ሥላሴን የዘላለም እውነትነትና የክርስትና እምነት መሠረትነት አይሽረውም፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ማመንን ለልባችን ስላበዛኽልን እናመልክሃለን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …


1 comment:

  1. ያመነ ሰው ስላመነው ነገር ይመሰክራል፤ አምነን በፍቅር የማንናገርለት እምነትም ይሁን ሃይማኖት ዲዳ ነው፤ ጮኸን የምንመሰክርለት እምነታችን ግን ከጠላት ምርኮን ይበዘብዛልና ሥላሴን የምታምኑ ሆይ! ትምህርቱን አሰምታችሁና ጮኻችሁ ተናገሩ! አስተውሉ! ጸሎትና አምልኮ፤ ዝማሬና ሽብሸባ የክርስትና ዋናዎች ሳይሆኑ አንድ ክፍሎች ናቸው፤ እንደነገረ ሥላሴ ያሉ ጠንካራና መሠረታውያን የሆኑ ትምህርቶችን ማናናቅና ትልቁን ቦታ አለመስጠት ለዘመነኞቹ የሐሰት መምህራን በገዛ እጅ ራስን ለምርኮ አሳልፎ መስጠት ነው!smart article God bless you

    ReplyDelete