Friday 13 January 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ሦስት)


  6. ውነተኛ ሯጭ ምትክ ሯጮችን ያዘጋጃል፦ እውነተኛ የክርስትና ሕይወት ሯጭ፥ ልክ እንደእርሱ እውነተኛውን ሩጫ የሚሮጡ ምትክ ሯጮችን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ፥ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፤” (2ጢሞ.4፥7-8)፡፡
    ቅዱስ ጳውሎስ የሮጠበትን የፊተኛውን ዘመን እውነተኛ ሩጫ በትክክል ካስታወሰ በኋላ፥ እርሱ ሮጦ በድል እንዳጠቃለለ እንዲሁ፥ ሌሎቹም እንዲነሣሱና እንዲሮጡ ይጋብዛል፤ ደግሞ የጋበዘ ብቻ አይደለም፤ እንደጢሞቴዎስና ቲቶ ያሉትን እውነተኛ ሯጮችን ተክቶ ሩጫውን ፈጽሟል፡፡ በዚህ ዘመን ከሚታዩ አስከፊ የደቀ መዝሙርነት ገጽታ አንዱ እውነተኛ የሩጫውን ተካፋዮች ለክርስቶስ ከማብዛት ይልቅ ሰዎችን በራስ ዙርያ ወደማከማቸት የሚሮጠው ሩጫ መብዛቱ ነው፡፡

    እውነተኛ ሯጭ የራሱን ዓላማና ግብ ብቻ አያይም፤ እንዲያውም ብዙ ነፍሳት ወደእግዚአብሔር መንግሥት ይጨመሩ ዘንድ ይተጋል፤  ለዚህም ዓላማ ሲል የራሱን መብትና ጥቅም እንኳ ሳይቀር ይሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተተኪ የማፍራት ያህል እጅግ ከባድ ዋጋን ያስከፍላል፤ ራሳችን ብቻ አሸናፊዎች ሆነን ሩጫውን እንድናጠናቅቅ ከፈለግን፥ እውነተኛውን የክርስትና ሩጫ ስለመሮጣችን ትክክለኞች አይደለንም፡፡ ቃሉም፥ “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤” (2ጢሞ.2፥2) ይላል፡፡ ለሌሎች አደራ የምንሰጠው አገልግሎትና ሩጫ ከሌለን፥ “አገልግለን” ያላተረፍን ምስኪኖች ነን፡፡  
    “ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር፤” (ሐዋ.13፥25)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ከአይሁድ ነቢያት ሁሉ፥ “ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤” (ማቴ.11፥11) በማለት የተናገረ ቢሆንም፥ “ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ”(ማር.1፥7) በማለት፥ የክርስቶስን የጫማውን ጠፈር መፍታት እንኳ መፍታት የማይገባው መሆኑን ተናገረ፡፡ እጅግም ክርስቶስን አግንኖ ራሱን ግን አዋርዶ አቅርቧል፡፡
    ቅዱስ ዮሐንስ ሰዎች ከክርስቶስ ይልቅ ሰዎች በእርሱ ዙርያ እንዳይሰበሰቡ አብዝቶ ተጠንቅቋል፡፡ ስለዚህም ሁሉም የእርሱ ተከታዮች እንዲሆኑ ቀስት(አመልካች) በመሆን አገለገለ እንጂ፥ ይህን ነገር እንደበታችነት አልቆጠረውም፡፡ በብዙ ክብር የተወደደ ቢሆንም፥ ይህ ሁሉ ከሩጫው እንዳያዘነጋውና ምትክ ሯጮችን ከማፍራት ወደኋላ እንዳይስበው ሲል ዘንግቶታል፡፡
      እናንተ የምትሮጡ ሆይ! ከራሳችሁ ይልቅ ክርስቶስ በእናንተ ሕይወት ይታያልን? ደግሞስ ሰዎች ሕይወታችንን አይተው ልክ እንደእና ክርስቶስን ሊመሰክሩ ይፈቅዳሉን? ተተኪ የማፍራት ነገር ይገደናልን? ሰዎች ሲከተሉን ተደስተን ብቻችንን ስንቀር በክርስቶስ መርካትና መደሰት ይሆንልናል?
7.    ውድድሩ ሽልማታችን ያሸነፈውን ጌታ መውረስ ነው፦ ይህ ሃሳብ እጅግ ጥልቅና ሰፊ ነው፤ ለዚህ ዓውድ ብቻ ግን እንዲሆን ሃሳቡን ብንጨምቀው፥ በክርስትና ሕይወት ሩጫ ፍጻሜ፥ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን”(ኤፌ.4፥13) እንሆናለን፡፡ “የልጁን መልክ በመምሰል” (ሮሜ.8፥29) የድሉን አክሊል እንቀበላለን ማለት እንችላለን፡፡ ይህ ግን ሩጫውን በታማኝነትና በጽናት በመሮጥ ያሸነፉ አሸናፊዎች ሁሉ የሚሸለሙት የድል አክሊል መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
    ሌሎች ቅዱሳንን በመንገዳቸው እንደገጠመው እንዲሁ፥ እኛንም በመንፈሳዊ ሕይወት ሩጫችን ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ደጋግመው ሊከሰቱ ይችሉ ይሆናል፤ (ዘኊል.11፥14 ፤ ኢዮ.3፥1 ፤ መዝ.55፥4) በተለይም ሰይጣንም በብዙ ሊያበጥረን ይፈልጋል፤ (ሉቃ.22፥31)፤ እንዲያውም ሩጫችንን በተደጋጋሚ ሊያዘገየው ይፈልጋል፤ (1ተሰ.2፥18) ነገር ግን በእምነት ጸንተን ልንዋጋው ይገባል፤ ነቅተን፥ በሃይማኖት ቆመን፥ ጎልምሰንና ጠንክረን (1ቆሮ.16፥13) ሩጫችንን ልንሮጥ፣ ጸንተንም ሰይጣንን ልቃወመው (1ጴጥ.5፥9)፣ እንዲያውም መከራ ቢገጥመን እንኳ፥ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መልካምን እያደረግን ነፍሳችንን ለታመነ ፈጣሪ አደራ መስጠት ይገባናል፤ (1ጴጥ.4፥19)፡፡ ደግሞም በጌታ እግዚአብሔር ታምነን ይህን አድርገናልና፥ እርሱም በነገር ሁሉ ይረዳናል፤ (መዝ.118፥6 ፤ ዕብ.13፥6)፡፡
    በመጨረሻ፥ በክርስትና ሕይወት ሩጫ ትልቁ ሽልማት ራሱ ክርስቶስ ነው፤ ከእርሱ ላነሰ ነገር ፈጽሞ ልንሮጥ አይገባንም፡፡ የትኛውም መልካም ነገር እንደምናገኝ ቢነገረን እንኳ፥ የምንሮጥለት ለአንዱ ለክርስቶስ ብቻ እንጂ ለሌላ ለማንም ሊሆን አይገባንም፡፡ ወዳጆች ሆይ! የእስካሁን የክርስትና ሕይወት ሩጫችሁ ለማን ነበር? “አገልጋዮችን” እያየን፥ ከኢየሱስ ዝቅ ያልን ጥቂት አይደለንም፤ ሩጫችሁን ዳግመና ተመልከቱት፤ በእውኑ ዋና ነገር ማን ሆኖላችሁ ይሆን እየሮጣችሁ ያላችሁት?
   ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል…


4 comments:

  1. እውነት ግራ ስጋባበት የነበረውን የአገልጋዮች ራስ መር ጉዞን እንዳጠራ ነው ያደረከኝ መምህር የባረከህ ይባረክ

    ReplyDelete
  2. ዘመንህ ይባረክ ወንድሜ

    ReplyDelete
  3. god bless you !!!

    ReplyDelete
  4. ደስ ይላል! ጌታ ስሙ ይክበር!

    ReplyDelete