Sunday 31 May 2015

ለመኪና ሸላሚዎችና ተሸላሚዎች “አማኞች” ምክር ቢሆን!



    “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” (ዘዳ.25፥4 ፤ 1ቆሮ.9፥9)

  ቅዱስ ነቢይ ሙሴ፥ እስራኤል የሚገለገሉባቸውን እንሰሳት በተለይም በሬ እያበራየ ባለበት ወቅት ጤንነቱ እንዲጠበቅ በቂ ምግብ ማግኘት እንዳለበት ሕዝቡን ያዛል፡፡ ይህም በመራራት ፣ የሚሰጡትን አገልግሎት በማሰብ እንሰሳቱን መንከባከብ ፣ ተመጣጣኝና የሚበቃቸውን ያህል መብልን ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ይህ ለእንሰሳት የተነገረው ቃል ፥ በአዲስ ኪዳን ቃል በቃል ለጌታ ወንጌል አገልጋዮች የአገልግሎት መርሕ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

   የእግዚእብሔርን መንግሥት መከር የሚያገለግል ሠራተኛ አገልጋዮች ወደመከሩ ሲሄዱ (ማቴ.9፥37-38) በመከሩ ውስጥ የመከሩ ጌታ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አስቀምጧል፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ስለመከሩና ስለመከሩ ሠራተኞች የተናገረው “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዝኖላቸው …” ነው፡፡ እንዲሁም የመንግሥቱን ወንጌል የሚሰብኩ ቅንና ታማኝ ሠራተኞች እንዲነሱ ጸሎት ዋናውንና ትልቁን ሥፍራ እንደሚይዝ በማሳሰብ ጭምር፡፡ ጌታ “እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።” አዝኖ ለተጨነቀ ሕዝብ የሚራራና የሚጨነቅ ሠራተኛን ለመከሩ እንዲሰጥ፡፡ (ማቴ.9፥38)
     ከጸሎት መልስ በኋላ የሚነሱት ታማኝና ልባም ሠራተኞች ደግሞ ወደመከሩ ተሰማርተው የጌታን ወንጌል ሲሰብኩና ሲያስተምሩ (ማቴ.9፥35 ፤ 28፥20) ፣ ህሙማንን ሲፈውሱ (ማቴ.9፥35 ፤ 10፥1 ፤ 8 ፤ ሐዋ.5፥12 ፤ 14፥8 ፤ 19፥11) ፣ ርኩሳን መናፍስትን ሲያስወጡ (ማቴ.10፥1 ፤ ሐዋ.16፥16-18) እያበራዩ ነውና አፋቸው ሊታሰር ስለማይገባ እንደብሉይ ኪዳን ካህናት (ዘሌ.6፥16 ፤ 26 ፤ 7፥6) ከመከሩ ሊገለገሉ ወይም በመከሩ ከሚገኘው ፍሬ ለኑሮአቸው ሊመገቡ ይገባል፡፡ ጌታችን “ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋል” እንዳለ፤ (ማቴ.10፥10  ፤ ሉቃ.10፥7) በመከሩ ውስጥ ካሉት ጋር መብላትን ፣ መጠጣትን ፣ መልበስን ፣ ደመወዝን መቀበልን ጌታችን ፈቅዷል፡፡
    የጌታችንን አገልግሎት በገንዘባቸው ያገለገሉ ሴቶች እንዳሉ (ሉቃ.8፥3) ሳስብ ጌታችን እንዴት ያለ ትሁት ሰው እንደነበር በልቤ አደንቃለሁ!!! ለራሱም  “ራሱን እንኳ የሚያስጠጋበት የሌለው ድኃ” ሆኖ የአባቱን ፈቃድ እንደልጅነቱ በፍጹምነት አገልግሏል፡፡ (ሉቃ.10፥58) የጌታን ሕይወት ህሊናቸው እየመሠከረላቸው ያለነቀፋ የኖሩት (ሐዋ.23፥1) ቅዱሳን ሐዋርያትም የኢየሱስን የአገልግሎት ሕይወት ሳያፍሩበት ኖረውታል፡፡ ጌታችን ሁሉ እያለው በአገልግሎቱ ግን የሌሎችን አገልግሎት ተቀብሏል፡፡ እኛን ባዕለጠጋ ሊያደርግ እርሱ በሁሉ ድኃ ሆኗል፡፡ ይልቁን በአገልግሎቱ ውስጥ ያገኘውን በረከት ሁሉንም ከወዳጆቹ ጋር እኩል ተካፍሎ በልቷል፡፡(ዮሐ.6፥5  ፤ 21፥10) ደቀ መዛሙርቱም በመከሩ ውስጥ የተገኘውን ፍሬ ወደግል ኪሳቸው ሳይሆን “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም። … በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፥ …” ተብሎ ተመስክሮላቸዋል፡፡ (ሐዋ.4፥32 ፤ 34)
           “የሚጠፋውን አክሊል ከሚያገኙት አይደለንም!” (1ቆሮ.9፥25)
      የትኛውም የመከሩ ሠራተኛ የመንግሥቱን ወንጌል ካገለገለ በኋላ ፥ ጌታችን እንዳለ “እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፥ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ፡፡” (ሉቃ.17፥10) በማለት በወንጌሉ ሥራ የመጣውን ክብርና ሽልማት ለራሳቸው እንዳያደርጉ አስተምሯቸዋል፡፡ አባት ለልጆቹ ቀለብን ስለሰፈረ ፣ ባርያ የታዘዘውን ስላደረገ ምስጋናና ሙገሳ አይገባውም ፤ ምክንያቱም አባት ለልጆቹ ቀለብ የመስፈር ግዴታ አለበትና ፣ ባርያም እንዲሁ፡፡ ወንጌል መስበክም ለታማኝና ለእውነተኛ የመከሩ ሠራተኛ ግዴታው ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።” (1ቆሮ.9፥16) በማለት አጽንቶ የተናገረው፡፡
   ሐዋርያት ከአገልግሎቱ የሚመጣውን ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር እንጂ ለራሳቸው እንዳይሆን አብዝተው ተጠንቅቀዋል፡፡ (ሐዋ.10፥26 ፤ 14፥28) ካገለገሉ በኋላ እነርሱ ተዋርደዋል ፣ ተርበዋል ፣ ተጠምተዋል ፣ ተራቁተዋል ፣ ተጎስመዋል ፣ ተንከራትተዋል ፣ እጅግ ደክመዋል ፣ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነዋል (1ቆሮ.4፥11-12) እንጂ አገልግለው በአንድም ሥፍራ ከሰዎች ሽልማትም ሆነ ሹመትን አልጠበቁም ፤ አላደረጉትምም፡፡
   ይልቁን የሁሉም ሠራተኞች አይኖች “የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን።” (1ቆሮ.9፥25) እንዲሁም “የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።” (1ጴጥ.5፥4) በማለት የተከታዮቻቸውን አይንና ልብ በዘላለማዊው ሽልማት ላይ እንዲተክሉ አጸኑ እንጂ ከዚህ አለም አንዳች እንዲጠብቁ አላሏቸውም፡፡
     አዎ! የክርስትና ሕይወት ሽልማቱ ለዘላለም የማይጠፋ አክሊል ነው፡፡ ይህ ግን ፥ ይህን የማይጠፋ አክሊል እንዳናገኝ በእሽቅድምድሙ ሥፍራ ከእሽቅድምድሙ ውጪ የሚያደርጉንን ነገሮች ሁሉ መቃወም ስንችል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ለአንድ እሽቅድምድም ያለው ሽልማት አንዴ እንጂ ሁለቴ አይደለም፡፡ እኛ አማኞች እንድንሮጠው በታዘዝነው የክርስትና ክርስቶሳዊ ሩጫም ሽልማታችንን የምንቀበለው ከአንዱ ፤ ከመከሩ ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ሰማያዊውን አገልግሎት እያገለገልን ሽልማትን ከምድር መቀበል ወይም መጠበቅ ወይም መስጠት በወንጌል ተቃራኒ መንገድ ላይ መገኘት ነው፡፡
    ለአገልግሎታችን በዚህ ምድር ከተሸለምን ፤ በሰማይ ምን ይሆን የምንጠብቀው? በመንፈስ ዘርተን ምነው በሥጋ እናጭዳለን? ለክርስቶስና ለወንጌል ከሮጥን ምነው ሽልማቱን ዝቅ ብለን “ከሥጋ ለባሽ ደካማ” ጠበቅን? ተቀበልንስ? ለኑሮ የሚያስፈልገንን ከወንጌሉ መከር ከተቀበልን ዘንዳ ሽልማታችንን የሚያረክስ ሲመጣ ምነው ዘወር አላልን? “ክብሩን ጌታ ይውሰድ ፥ እኛ ልናንስ እርሱ ጌታችን ሊልቅ ይገባል”(ማቴ.3፥11) ምነው አላልን?  
  ሽልማቱን ሰጪዎችስ እናንተ በማን ቦታ ናችሁ? በእውኑ በአገልግሎቱ ጌታ ፣ በሩጫው ባለቤት ፣ ለመከሩ ሠራተኞችን በሚያሰማራውና በሚሸልመው ቦታ ናችሁን? ለሠራተኛው ሽልማትን ሰጪ ያሠማራው ጌታ ብቻ እንደሆነ ገና አላስተዋላችሁምን? በእውኑ እናንተን በምክርና በተግሳጽ ቃል የሚያቀና ማን ይሆን? ደግሞስ ይህች “መሸላለም” ከየትኛው መድረክ ላይ ተቀድታ ይሆን ወዲህ ብቅ ያለችው?
    ማን ነበር?
“መጪውን ጊዜ ሳስብ ቤተ ክርስቲያንን ከሚገጥሟት ተግዳሮቶች በጣም የሚያሳስበኝ እምነትን ሙልጭ አድርጎ ሳይክድ ፣ ውኃ እየቸለሰበት ትርጉም አልባና አቅመ ቢስ የሚያደርግ ዓለማዊነት ነው”  ያለው?
ደግሞስ ማን ነበር?
“የዚህ ዘመን አገልጋዮች ሽልማታቸውን በምድር ጨርሰዋልና በጌታ ዘንድ ምንም የሚጠብቁት ብድራትና ሽልማት የላቸውም፡፡” ያለው?

      አዎ! ምድሪቱ ገና ከጉስቁልና ፣ ከመንፈሳዊነት ጥማትና ረሃብ ፣ ከአለማዊነትና ከክፉ ምኞት ልክፍት ፣ ከጥንቆላና ከምዋርት ፣ ከዘረኝነት ፤ ከጎጠኝነትና ከብሔርተኝነት መርገም ገና ያልተላቀቀች ብቻ ሳይሆን በአገራችን ያለው ድንበሩ አለቅጥ የሰፋው የድሆች ቁጥር ፣ የተራቡና የታረዙ ፣ ወላጅ አልባ ሆነው የተበተኑ ህጻናትና ደጋፊ ያጡ አዛውንት እውን ከቤተ ክርስቲያን ደጅ ሆነው ሳይታዩን ቀርተው ነው እኛ ልክ ሥራውን እንደጨረሰና በድል እንዳጠናቀቀ ሰው የምንሸላለመው? በእውኑ በዚህ ሽልማታችን እግዚአብሔርን ልናስቀናው እንሻለንን?!

   አቤቱ ጌታችን! ለመከሩ የታመኑና የራሳቸውን ክብር የማይፈልጉትን የታመኑ ሠራተኞችን አስነሳልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment