Monday 4 May 2015

ሁለት ብዕርና ምላስ ላላቸው “ሰባኪዎች” ሙግት አለኝ!

     
                                      Please read in PDF            

   ሰሞኑን በISIS ከታረዱት ወገኖቻችን መካከል ኤፍሬም የማነ ስለተባለ ኤርትራዊ ወንድማችን ቀድሞ ሲወራ የነበረው ጀማል በሚል የእልምና ስም እንደሆነና የእምነቱም ተከታይ እንደሆነ ፤ አብሮ ለመሰዋት በመወሰኑ ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር መታረዱን ብዙ ንግግሮችና ጽሁፎችን አድምጠንም ፤ አንብበንም ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ሲነገሩም የነበሩ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ አስተምህሯዊ ንግግሮች ስናደምጥም ፤ ስናነብም ታዝበናል፡፡ በተጨማሪም ጥቂት የማይባሉ ሰባኪዎች የቤተ ክህነቱንና የቤተ መንግሥቱን የሚድያና የስብከት አውደ ምህረትን ተቆጣጥረው “ጀማል ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር ሰማዕት ሆነ” በሚለው ዙርያ የተናገሩትንም ሰምተናል ፤ የጻፉትንም አይተናል፡፡ እኒህ ሰባኪዎች ደስ ሲላቸው ራሳቸውን እንደ“ተመራማሪ” ፥ ሲላቸው ደግሞ እንደየ“ፖለቲካ ተንታኝ” ቆጥረው ሳያበቁ “የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ሙላት” እንዳላቸውም ደግሞ ለመስበክ ደፍረው ሲቀርቡም እናያለን፡፡

    እኛ ክርስቲያኖች ከሌሎች ከየትኛውም የሃይማኖት ተቋማት ጋር የምንኖረው ጌታ ኢየሱስ “ … በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፥ የሚረግሙአችሁን መርቁ ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ … ” (ማቴ.5፥44-45) ብሎ ባዘዘው ክርስቲያናዊ የቅድስና መርህና “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሳለም ኑሩ፡፡”(ሮሜ.1218) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ባስተማረን ቅዱስ ቃል መሠረት ነው፡፡  ለዘመናት በዚህ እውነተኛ ቃል ሲገድሉን ታግሰናል ፣ ሲያሳድዱን መርቀናል ፣ ሲያርዱን ጸልየንላቸዋል፡፡ ነገር ግን ከቃለ እግዚአብሔር ወርደው ፣ ዓለማዊውን ሚዲያ ሲያገኙ “እንደአህያ ጡት ሁለት ነበርን ፤ በሰማይም በምድርም አንለያይም ፤ በአገር ተወላጅነትም ፤ በሃይማኖትም ከጥንት አብረን ኖረናል፤ አክራሪዎቹ ሊወገዙ ፣ ኢ- አክራሪዎቹ ሊወደዱ ይገባቸዋል” የሚል የካድሬ ቋንቋ ተጠቃሚዎች  ፤ መልሰው ደግሞ “እኛና ከእንትን ሃይማኖት ተከታዮች ጋር አንድ አይደለንም ፣ ገዳዮች ፣ አራጆች … ናቸውና ከእነርሱ ልንጠነቀቅ ይገባናል” ብለው ደግሞ እኒሁ ሰዎች የሃይማኖት ካባ ለምድ ለብሰው ራሳቸውን እንደክርስትና ሰባኪ አድርገው ይገለጣሉ፡፡ 
  ኤርትራዊው ወንድማችን ኤፍሬም የማነ ፤ ጀማል ተብሎ በተጠቀሰበትና “አብሬ እሞታለሁ” ባለ ጊዜ ብዙ ሃይማኖታዊ ፤ ማህበራዊ ድህረ ገጾች “ፐ! ምን አይነት ክርስቲያን አፍቃሪ ሙስሊም ነው?!” ብለው ያደነቁትን በየለቀስተኛው ቤት “የሰበኩበትን” ያህል ፤ እኒሁ አካላት ሙስሊም አልነበረም ፤ ክርስቲያን ነው ሲባል ደግሞ አዲስ ሃሳብ አምጥተው በተቃራኒው ባለማፈር ሲሞግቱ እናያለን፡፡
  አገራዊና ማህበራዊ እሴትንና ክርስቲያናዊ እምነትና ትውፊትን ደባልቆ ድንበሩን ማጥፋት የዛሬ ዘመን “ስለጮኹ የተሰሙ የመሰላቸው” ሰባኪዎች ዋና መናፍቅነት  ነው፡፡ የኢትዮጲያ ሕገ መንግሥት ለሁሉም ሃይማኖቶች ያለማዳላት የእኩልነትን ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ (አን.27) በሌላ ንግግር በአገሪቱ ላሉ መልካም የሆኑ አገራዊና ማህበራዊ እሴቶች ሁሉ በአብላጫ ይዘቱ ዕውቅና ሰጥቷል ማለት ነው፡፡  ይህንን ሃሳብ አምጥቶ ወደመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ አስጨንቆ ማስገባት ግን የማይቻል ካለመሆኑም በላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ አለመገዛትን በግልጥ ያሳያል፡፡ አገራዊና ማህበራዊ እሴቶችን የምናከብረው ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ትውፊት ቀጥለን እንጂ ቅድሚያ ሰጥተን አይደለም፡፡ ከዚህ በዘለለ “መዳን በክርስቶስና በክርስቶስ ብቻ ነው፤ በሌላ የለም” ስንል ያለምንም ማመቻመችና ማቅማማት እንጂ በሁለት ምላስና በሁለት ብዕር መካከል ቆመን አይደለም፡፡
   ከክርስትና እምነት ውጪ ያሉ ወገኖች በሊቢያ በታረዱ ወንድሞች ቤተሰብ መካከል ተገኝተው በሥራ መርዳትና ማጽናናታቸው ፤ እንደአገርና ማህበራዊ እሴት እንጂ እንደየክርስትና እምነት ትምህርትና ትውፊት ተወስዶ መለፈፉን አብዝተን እንቃወማለን ፤ እንዲህ ያሉ ካድሬ “የስብከት አገልጋዮችንም” ክርስትናንና ትውፊቱን አይወክሉም ብለን እንናገራለን ፤ ማስተናገድ ፣ ማብላት ፣ ማጠጣት ፣ በገንዘብ መደገፍ ፣ የሃዘንተኛውን እጅ ማስታጠብ … እንደክርስትና ትውፊት ለመቁጠር መዳዳት ጤናማ ሰባኪነትና አገልጋይነት ነው ለማለት መጽሐፍ ቅዱስን መካድ አለብን፡፡ ይህ ግን የማይቻል ነገር ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በግብረ ሰዶማዊነትና በአመንዝራነት ኃጢአት የተያዙና የተከበቡ አገልጋዮች ከክፋታችሁ ተመልሱ ሲባሉ፥ በዚህ ሕይወት መኖርንና ማገልገልን ክርስትና አይከለክልም ብለው እንደቀጠሉበት ፤ በድጋሚ ዛሬም የማይገናኙ ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን በግድ ለማዋሃድ መሞከር ከንቱ ድካም ነው ለማለት እንጨክናለን፡፡
  ወንድማችን ኤፍሬም የማነ በትላንት ስሙ ጀማል ሆኖ እንደሩት “በወንድሞቼ አምላክ አምናለሁ ፤ በእነርሱ የሆነው በእኔም ይሁን” ካለ ወይም ከመጀመርያውኑ ክርስቲያን ሆኖ “የሞተልኝንና ያዳነኝን ፣ አዳኜን ክርስቶስን አልክድም ፤ ሳይበድለኝ አልበድለውም ፤ ከዚህ ይልቅ ሞትን መርጫለሁ” ካለና በዚህ ምክንያ ከታረደ ወይ ከጌታ ጋር እንደተሰቀለው እንደአንዱ ወንበዴ ወይም እንደእስጢፋኖስ ሰማዕት ሆኗል ብለን እንመሰክራለን፡፡ ከዚህ በተለየ መንገድ ግን ራስን አንደቤተ ክርስቲያን “ተመራማሪና ምርጥ አገልጋይ” እየቆጠሩ በፖለቲካው መድረክና በየአውደ ምህረቱ ምርቅና ፍትፍት መፈትፈቱ በግልጥ ቃል እግዚአብሔር የተጣላውን በግድ ለማስማማት የሚሞከር መናፍቅነት ነው ለማለት በቅዱስ ቃሉ ድፍረት እንደፍራለን፡፡
    ኤፍሬም የማነ ሙስሊም ሆኖ ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር በአምላካቸው ታምኖ ለመታረድ ጨክኖ ቢሆንም ሆነ፥ ከመጀመርያው ክርስቲያን ሆኖ አልክድም ብሎ ቢሞት ሁለቱም የሚያኮሩ ድርጊቶች ናቸው፡፡ የሚያሳፍረው ግን ሙስሊም ሆኖ ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር ታረደ ሲባል ክርስትናንና እስልምናን “አንድ ለማድረግ” ምንም ያልቀራቸው “ሰባኪዎቻችንና” ፤ መልሰው ክርስቲያን ሆኖ ነው የሞተው ሲባል ደግሞ “የሚያጨበጭቡትን” መንታ ምላሰኞችንና ብዕረኞችን ማየት ነው፡፡

ጌታ የልብ ብርሃናችንን ያብራ፡፡ አሜን፡፡   

5 comments:

  1. Yale tirtet temeramari poletikegna eyalkew yalehew man endehon goltse new eski ande bota lay daniel sile jemall mehonu yawerabet bota ltasayegn tchlaleh ??

    ReplyDelete
  2. ሁለቱ ተጨማሪ የአይኤስ ሰለባዎች ተለይተው ታውቀዋል!
    (አሌክስ አብርሃም)

    በአይ ኤስ የሽብር ቡድን ከተገደሉና ማንነታቸው ከታወቁ ኢትዮጲያዊያን ወንድሞቻችን በተጨማሪ የሌሎች ሁለት ኢትዮጲያዊያን ማንነት ተለይቶ ታውቋል …የአቧሬ እና ገርጂ አካበቢ ነዋሪ የነበሩት እነዚህ ሁለት ወጣቶች አያልቅበት ስንታየሁ እና ብርሃኑ ጌታነህ ሲሆኑ …አያልቅበት ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ የነበረ ሲሆን ወደሱዳን ከሄደም ሶስት ዓመት ሁኖት ሁኖታል !! ብርሃኑ ጌታነህ የሁለት ልጆች (8እና የ4 ዓመት) አባት ሲሆን ከ4 ወራት በፊት ነው ከአገር ወጥቶ የነበረው !

    እንግዲህ እነዚህ ሚስኪን ኢትዮጲያዊያን ወንድሞቻችን ይህ አሰቃቂ ድርጊት ሰለባ ሁነዋል ቤተሰቦቻቸውም ተረድተው በሃዘን ላይ ናቸው ! ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እየተመኘሁ ሁላችንም እነዚህን ቤተሰቦች እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ከጎናቸው በመሆን እንድናፅናናቸው መልእክቴን አስተላልፋለሁ !

    ReplyDelete
  3. ጅል መናፍቅ:: ሰማእታት ሲባል የሚያምህ ያራጆቹ መንፈስ ስለሰፈረብህ እኮ ነው::

    ReplyDelete
  4. ምንድን ነው የምታወራው; አንተ ራስህ የምትፅፈውን ብታውቅ ጥሩ ነው፡፡

    ReplyDelete
  5. ተሀድሶ የቤተክርስቲያን ጠላት

    ReplyDelete