Friday 29 May 2015

ቅዱስ ሲኖዶስና የመሰብሰቡ ዓላማ (ክፍል - 2)

     

                                                                    Please read in PDF      

 
  “በበጋና በበልግ ወራት ቸነፈር የድንገት ሞት ይበዛልና ከሞት አስቀድሞ ፍቅር ሰላም ይሆን ዘንድ፡፡” እንዲል  “ … ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1ጢሞ.5፥8) በሚራራና በፍቅር ስስት ለሃይማኖት ቤተሰብ ማሰብ ከአማኝ ሁሉ የሚጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነው፡፡ ከአንደኛው ሃሳብ ጋር ብናስተሳስረው የአምልኮዓችን ጤንነት ያለው ለባልንጀራችን ባለን የርኅራኄ ዕይታ ነው፡፡ ባልንጀራችን ለአደጋ ተጋልጦ (ሉቃ.10፥29-37) ፣ ተርቦ ፣ ተጠምቶ ፣ ታርዞ ፣ ታስሮ (ማቴ.25፥37-40) ፤ በስደትና በመቅበዝበዝ ሲኖር ሳለ እኛ ተቀማጥለን ልብስና ምግብ በማማረጥ ያማሩ ቤቶች ሠርቶ ዕቃዎችን በመገጥገጥ እንድንኖር ክርስቲያናዊ አስተምህሮም ሆነ ትውፊቱ በዝምታ ይነቅፈናል፡፡

   እግዚአብሔር የባህርይ ልጁን ሳይራራለት ጨክኖ ወደዚህ ምድር የላከውና (ሮሜ.8፥32) ውድ ልጁም በፈቃዱ የመጣው የሰው መዋረድ ፣ መጎሳቆልና ፍጹም ክብሩን ማጣቱን አይተው በእንዲሁ ፍቅር ራርተው ነው፡፡ (ዮሐ.3፥16) እንኪያስ እኛም የተማርነው “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ ትቶልን …” (1ጴጥ.2፥19) ሄዷልና የባልንጀራችን ቁስል እንደቁስላችን ሊሠማን ይገባል፡፡
     ሲኖዶሳውያንም “ከሞት ከዕርዛት ከሰቆቃ … በፊት ፍቅርና ሰላም እንዲሆን” ትልቁን ኃላፊነት ተሸክመዋል፡፡ በአገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁል ጊዜ ሲኖዶስን ከሌላው ምዕመንና ግለሰብ ይልቅ ይበልጥ ሊያስጨንቅ ፣ ሊያሳስብ  ይገባል፡፡ ምክንያቱም ለአገሪቱ በረሃብ መታመስ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሲኖዶሳዊው ቤተ ክህነት ከተጠያቂነት የሚያድነው ማንም የለም ፤ ሕዝብ እንዳይራብ እግዚአብሔራዊው የዮሴፍና የአጋቦስ ጥበብ የሚገኘው ከቤተ መንግሥት ሳይሆን የእግዚአብሔር ከሆኑት ወይም ለእግዚአብሔር ከተሰጡት ዘንድ ነውና፡ ፡(ዘፍ.41፥39 ፤ ሐዋ.11፥28) ሲኖዶስ በሆነው ንስሐ በመግባት፥ ሊመጣ ባለው ግን በቅዱስ አምልኮ በመትጋት እየሞተ ላለው ወገን አብዝቶ ሊጨነቅ ይገባል፡፡
    አጋቦስ በዓለም ሁሉ ላይ ረሃብ ሊሆን እንዳለ በመንፈስ ቅዱስ ትንቢት በተናገረ ጊዜ “ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ ፤ እንዲህም ደግሞ አደረጉ፥ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።” (ሐዋ.11፥27-30) ቤተ ክርስቲያን ትንቢትንና ራዕይን ብቻ የምትናገር አይደለችም፡፡ ይልቁንም ቀዳሚውን ሥፍራ በመያዝ ሌሎች ወገኖች በትንቢቱ ወይም በራዕዩ ወይም በሕልሙ ሊጎዱ ፤ ለአደጋ ሊጋለጡ ያሉ እንደሆነ አዎንታዊና መንፈሳዊ ምላሽ መስጠት መቻልም አለባት፡፡
    የሕዝቡን መቸገርና ቁስቁልና ብቻ መናገር መፍትሔ አይደለም ፤ እኛ ዘንድ ያለውንም መፍትሔ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባናል፡፡ በተለይ በዚህ ዙርያ “ትልቅ የሚባሉትና እንደሆኑ የሚያስቡት አገልጋዮች” ዋና በሽታና ነውር ይህ ነው፡፡ የወገንን እርዛትና ረሃብ በሚጣፍጥ ቋንቋ ያቀርባሉ ፤ ለራሳቸው ግን ከተቀማጠለ ኑሮ በቀር እርዛቱንና ረሃቡን መካፈል አይፈልጉም፡፡  በብዙ መቶ ሺህና በሚሊየኖች በሚቆጠር ብር የተንደላቀቀ መኪና እያሽከረከሩ የሕዝብን ብሶትና ሮሮ ደግሞ በመጽሐፍና በስብከት መልክ እየቸበቸቡ ፤ አስገድደው አስራትና በኩራት እየሰበሰቡ በቅምጥልነት ላይ ቅምጥልነትን የሚደርቡቱ በሕዝባቸው ላይ እያፌዙና እየዘበቱ ስለመሆናቸው እንዲያስተውሉ ማን በረዳቸው!?
  ሲኖዶሳውያን! ወገን ስንል በኢትዮጲያ ምድር ያሉ ብቻ እንዳልሆኑ ቢረዱ እንመኛለን፡፡ በኢራቅ የሚታረዱና በጥይት ተደብድበው የሚሞቱት ፣ በኢንዶኔዢያ ፣ በማሌዢያ ፣ በሶርያ ፣ በሊቢያ ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በየመንና በሌሎችም በተለያዩ አገራት ስቃይና ግፍ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ወገኖቻችን ናቸውና መገደላቸውን ልንዘነጋ ፤ እየሆነባቸው ያለውም በእኛም እንደሆነ ልንረሳ አይገባንም፡፡
  በተለይም ወገን በስደት ፤ በባዕድ ምድር ሲርመሰመስ የክፉ ጠላት ስለት ሲበላው ፥ በአገር ውስጥ ደግሞ በረሃብና በእጦት ሲሰቃይ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸው ቤትና ንብረት አልበቃ ብሏቸው በግል ሃብትና ንብረት አፍርተው ፤ በባንክ የታጨቀ ብርና ወርቅ ያላቸው አብዛኛዎቹ ሲኖዶሳውያን መነኮሳትና ጳጳሳት ለወገናቸው ግድ የሌላቸው መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቁጣ እየሰቡ ለመሆናቸው ፥ ወገኖቻችን ያሉበትንና እነርሱ የሚኖሩበትን የቅምጥልነት ሕይወት ማቅረብ እንጂ ሌላ ምስክር መጥራት አያሻም፡፡
   ሲኖዶሳውያን ሆይ! የምትወያዩበት ሕዝብና ወገን የውጪ ዕርዳታና ልገሳ ብቻ ሳይሆን የእናንተንም የቸርነት እጅ ይሻልና ችግሩን እዩለት ፣ መንገድም አሳዩት፡፡   
አቤቱ ሕዝብህን  አድን ፤ ርስትህንም ባርክ፡፡ አሜን፡፡      

ይቀጥላል… 

No comments:

Post a Comment