Monday 18 May 2015

ቅዱስ ሲኖዶስና የመሰብሰቡ ዓላማ (ክፍል - 1)


“በየቦታው ሁሉ ኤጲስቆጶሳት በያመቱ ሁለት ጊዜ ከጳጳሳቸው ወይም ከሊቀ ጳጳሳቸው ዘንድ ይሰብሰቡ፡፡ መጀመርያ ከጾመ ፵ በፊት ይሁን፡፡ ክፉንና ቁጣን በሚያርቁ ገንዘብ ቁርባናቸውም ለእግዚአብሔር ንጽሕት ክብርት ቅድስት ትሆን ዘንድ፡፡ ሁለተኛውም ከበዓለ መስቀል በኋላ በመከር ወራት ይሁን፡፡ በበጋና በበልግ ወራት ቸነፈር የድንገት ሞት ይበዛልና ከሞት አስቀድሞ ፍቅር ሰላም ይሆን ዘንድ፡፡ ወደጌታችን ወደኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ንጽሕና በሚቀርቡ ገንዘብ፡፡ ከካህናት ወገን ወይም ከሕዝቡ ወገን ቢሆን ኤጲስ ቆጶስ አውግዞ የለየውን ሰው ፍርድ ይመረምሩ ቸልታ እንዳይሆን ወይም ይህን በሚመስል ነገር ሁሉ እንደተገለጠላቸው ይፈርዱ ዘንድ፡፡”
(ፍትሐ ነገሥት አን.5 ቁ.165 ገጽ 61)




    
     ኤጲስ ቆጶሳት በያመቱ ፤ በአመት ሁለት ጊዜ ስብሳባ እንዲያደርጉ ፍትሐ ነገሥቱ ያዛል፡፡ የሚሠሩት የእግዚአብሔርን ሥራ እንደመሆኑ መጠን እርስ በእርስ በመንፈስ ቅዱስ ዓይን ለመተያየት (ዕብ.10፥24) ፣ እርስ በእርስ ለመጽናናት (ፊልጵ.2፥1-5) ፣ እንደሐዋርያት መሰባሰብ በእርግጥም አገባብ ነው፡፡ (ሐዋ.1፥14 ፤ 13፥1-2 ፤ 15፥4)  ከጥንት ሰውን በመልክና በምሳሌው ፈጥሮ (ዘፍጥ.1፥26) ዕለት ዕለት አብሮ በመሆንና በመጫወት (ዘፍጥ.3፥8) ሕብረትን የወደደ ራሱ እግዚአብሔር ፤ በኋላም ለእስራኤል “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። ” (ዘጸ.25፥8) በማለት በግልጥ ሕብረት ወዳድነትን  ያሳየን እርሱ አባታችን ነው፡፡ እንዲሁ ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ “ከእኛ ጋር” (ማቴ.1፥23) ፍጹም ሕብረትን የፈጠረና ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ጌታችንና መድኃኒታችን ነው፡፡
    እርሱ ከእኛ ጋር መሆንን ከወደደ ፥ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የእኛን በሕብረት መሆንንም አብዝቶ ይወዳል፡፡ በምሴተ ሐሙስ ጸሎቱም “እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ …” (ዮሐ.17፥24) በማለት እርሱ ከአባቱ ጋር እንዳለው ሕብረት፥ እንዲሁ ከክርስቶስ ጋር ህብረት ያለው ከአባቱም ጋር ሕብረት እንዳለው በማጽናት ፤ እግዚአብሔር ክርስቶስን በወደደበት መጠን ለሰዎችም ትልቅ ፍቅርና የዘላለምን ሕብረት መመሥረቱን ያሳየናል፡፡ ይህንን ሕብረት ሐዋርያት ስላጸኑት (ሐዋ.2፥2) መንፈስ ቅዱስ ለእነርሱ መውረዱን ታላቁ መጽሐፍ ይመሰክርልናል፡፡ ስለዚህም በልጁ ስም በተሰበሰቡት መካከል የጌታ አይኖች ለሁልጊዜ በዚያ ናቸው፡፡ (ማቴ.18፥20)
    እንግዲህ የቅዱስ ሲኖዶስን መሠብሰብ ዋና አላማም ምንድር ነው? ብንል ከፍትሐ ነገሥቱ ቀኖና  ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ማውጣት እንችላለን፡፡ እኒህም ፦
1.    ለቅዱስ አምልኰ
   የጸሎት መልስ ለምስጋናና ውዳሴ ሰበብና ምክንያት እንዲሆን አምልኮ ግን እግዚአብሔርን በማንነቱ ብቻ የምናመልክበት መንገድ ነውና ፤ አምልኮ ልማዳችን፥ የዕድሜያችን ሁሉ ሥራ ነው፡፡ እንዲሁ “ክፉንና ቁጣን በሚያርቁ ገንዘብ ቁርባናቸውም ለእግዚአብሔር ንጽሕት ክብርት ቅድስት ትሆን ዘንድ፡፡” እንዲል የመጀመርያ የመሰብሰባቸው ዓላማ የጌታን እራት አብሮ ለመካፈል ነው፡፡ የአማኞች ትልቁና ዋና ሥራ ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለልንን ትልቁን የርኅራኄ ሥራ በማሰብ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው፡፡ ይህ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚቀርብ ሳይሆን የዘወትር ቅዱስ ሥራ ነው፡፡(ሐዋ.2፥42 ፤ 46) በተሰባሰብንና ከብዙ ሥፍራ የተገናኘን ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ልናደርገው ይገባናል፡፡
  ሲኖዶሳውያን አማኞች እንደመሆናቸው መጠን “ቁርባናቸውም ለእግዚአብሔር ንጽሕት ክብርት ቅድስት ትሆን ዘንድ፡፡” ከየትኛውም ውይይትና ሥራ ቀድሞ ፥ ለቅዱስ አምልኮ ተገቢውን ትኩረትና ሥፍራ መስጠት ይገባቸዋል፡፡ ከድል በፊት መንበርከክ ፣ በፊቱም እንደውኃ መፍሰስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው፡፡ ከጉባኤ በፊትና በኋላ ጥሩ ጥሩ አጀንዳዎችን ብቻ መቅረጽ ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማሰማመር ፣ ለጋዜጣዊ መግለጫ ራስን ማዘጋጀት ፣ ከውይይት ይልቅ የክርክርን መንፈስ ማጎልበት … ከቅዱስ አምልኮ ምንጭነት የተቀዱ ናቸው ማለት እጅግ ይከብዳል፡፡
   የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መደረግ ከመጀመሩ በፊትና ከተደረገ በኋላ እንደአሞራ በዙርያው የሚያንዣንብቡ ጥቅመኛ ግለሰቦችን ፣ ማህበራትን ፣  የፖለቲካ አካላትን ከጥቂት አመታት ወዲህ በግልጥ ማየት ከጀመርን እንደያልተለመደ ክስተት ሳይሆን ጤናማ ወደመሆን እያዘነበለ ይመስላል፡፡ ሲኖዶሳውያኑም ለእነዚህ አካላት በሮቻቸውን ጠርቅመው ከመዝጋት ይልቅ “ባሻቸው ጊዜ” እንዲገቡ ገርበብ አድርጎ የመተውን ስልት የተያያዙት ይመስላል፡፡ የዚህ በር ጠርቅሞ አለመዘጋት ከጉባኤው  በፊትና በኋላ ብዙ የማይገቡ ነገሮችን ለመስማት ስንገደድ እናያለን፡፡
  የእስራኤል ልጆች በአስጨናቂዎቻቸውና በወደረኞቻቸው ፊት እግዚአብሔር ድልን ያጎናጸፋቸው ከሁሉ በፊት ለእርሱ ፍጹም በመታዘዝ እርሱን በማምለካቸው ፣ በፊቱም እንደውኃ በመፍሰሳቸው ነው፡፡ (ኢያ.7፥6 ፤ 1ሳሙ.7፥5-6) ሲኖዶሳውያን አብዝተው ሊጠነቀቁ የሚገባቸው የአምልኮ ንጽሕናቸውን ነው፡፡ ሊከባበሩ ፣ ሊደማመጡ ፣ በቁጣና በክርክር መንፈስ ከመነጋገር ይልቅ በትህትና ቃል ሊመላለሱ ይገባቸዋል፡፡

  በቤተ ክርስቲያን ችግሮች ውይይት ከመጀመራቸው በፊት ችግሮቹን በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ይገባቸዋል፡፡ በችግሮች ተከራክሮ ወደአምልኮ ከመምጣት፥ እያንዳንዳቸው ችግሮቹን በትልቁ ጌታ ፊት ቢያኖሩት በወንድማማችነት መንፈስ ለመነጋገር ምቹ አካሄድ ነው፡፡ እጅ ከመጫን በፊት በጸሎትና በጾም መትጋትም (ሐዋ.13፥3) ፍሬውን በመልካም የጐመራ ያደርገዋል፡፡
   የመንፈሳዊነት መልካምና ሙሉ ስብዕና ምንጩ ቅዱስ አምልኮ ነው፡፡ አምልኮዐችን ፥ ቅዱስ ፣ ክቡርና ንጹሕ የሚሆነው እኛ ለእግዚአብሔር ባለን መሰጠት ልክ ነው፡፡ እኛ ከኃጢአትና ከርኩሰት ርቀን ፈቃዱን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባልሆንበት መንገድ እግዚአብሔር ፈቃዳችንን ጠምዝዞ በመጋፋት ከእኛ ጋር አብሮ አይሠራም፡፡ ቁርባናችን በፊቱ ያለነውር ሆኖ ፥ የተወደደ እንዲሆን አምልኮዐችን በቅንነትና በእምነት (1ጢሞ.1፥14-15 ፤ ፊልጵ. 1፥15 ፤ ዕብ.11፥6) ከንግግር ጀምሮ (ኤፌ.4፥29 ፤ ዕብ.12፥14-15) በኑሮዐችንም ሁሉ (1ጴጥ.1፥15-16) ፍጹም መሆን አለበት፡፡
    በአንድ ወቅት በኢትዮጲያና በአሜሪካ ያሉቱ “ቅዱሳን ሲኖዶሳውያን”(ተወካዮቻቸው) “ባለመስማማት ተስማምተው” “ቅዱስ ቁርባን ለመፈተትና በአምልኮ ጌታን ለማምለክ” ወደመቅደስ መግባታቸውንና “አብረው ከቆረቡ በኋላ” በፍጻሜው ግን ሳይታረቁ መለያየታቸውን ታዝበናል፡፡ ከዚያኔ ጀምሮ ሳይታረቁም እስከአሁኗ ሰዓት ይኸው አሉ!!! ጌታ የመጣው ለታመምነው ለእኛ ከሆነ  … ከሁለቱ ግን ማን ይሆን ከመሥዋዕት ይልቅ ጌታ የሚሻውን ምህረትን የሚወድድ!? (ማቴ.9፥13 ፤ 12፥7) ከአምልኮው በፊት ፣ ሥጋውና ደሙን ከመፈተት በፊት ፣ ከመቀደስና ኪዳን ከማድረሱ በፊት ፣ ከመስበክና ከመዘመር በፊት ፣ ከሲኖዶስ ስብሰባ በፊት … ማን ነው በትሁት ልብ ለይቅርታ የሚሸነፍ ልብና መንፈስ ያለው?!
   እንኪያስ፦ ሲኖዶሳውያን ሆይ! ትኩረት ከስብሰባው ጊዜ ይልቅ ንጹሕ ፣ ቅዱስና ክቡር ለሆነ ለቅዱስ አምልኮ በሁለንተናችን ወድደን ፈቃዱን ማድረግ (ማቴ.7፥21) ፣ ባልንጀራችንን እንደራስ በመውደድና (ማር.12፥31) ፣ ንጹሕና ነውር የሌለበት አምልኮ (ያዕ.1፥27) ፣ ከአማኞች ሁሉ ጋር በወንድማማችነት መንፈስ (ሮሜ.12፥10 ፤ 2ጴጥ.1፥7) ታቀርቡ ፤ እናቀርብም ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ ፤ በመስቀሉ ፍቅር እንለምናችኋለን፡፡ ይህ ሕዝብንም አገርንም የሚፈውስ እጅግ የበዛ በረከት አለውና፡፡አሜን እንዲህ ይሁንልን ፤ ይብዛልንም፡፡
ይቀጥላል …

1 comment:

  1. yenas meubl yemibal alasfelagi sew Homosexual character post adergo selale Join group lay reject aderegut ebakachihu Abnezer !!

    ReplyDelete