Saturday 23 May 2015

ድል የነሣው ጌታ - አርጓል!



   
  ጌታ ወደሰማያት ያረገው ከአባቱ ዘንድ የተላከበትን ዋናውን ዓላማውን “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤” (ዮሐ.17፥4 ፤ 13፥31) በማለት ፈጽሞ (ዮሐ.19፥30) ያከናወነ መሆኑን ተናግሯል፡፡ (ዮሐ.19፥30) ጌታችን ከአባቱ ዘንድ የተላከበት ዋና ዓላማው፥ የሰውን ልጅ ከዘላለም ሞትና ቀንበር ማዳን ነው፡፡ (ሉቃ.9፥56 ፤ 19፥10 ፤ ዮሐ.3፥15 ፤ 17 ፤ 8፥15) ይህንን በመስቀል ላይ በሠራው የፍቅር ሥራው ፈጽሞታል፡፡ ድል መንሳቱንና የሰው ልጆችን መዳን መፈጸሙን ስናነሳ ፥ በጌታ የሆነውን ሁለት ነገሮች ማስታወስ ግድ ይለናል፡፡


    አንደኛው፦ ደካማ ሆኖ በመታየት፥ በአይሁድ እጅ ከባድና አስጨናቂ መከራን ባለመዛት (1ጴጥ.2፥23) በአንደበቱም ክፉ ሳይገኝበት የተቀበለ ሲሆን (ዮሐ.8፥46 ፤ 1ጴጥ.2፥22) ፤ ሁለተኛውና ከፍ ያለ ምስጢር ያለው ደግሞ፥ ሐሙስ ማታና አርብ በጌቴሴማኒና በቀራንዮ ላይ በነፍሱና በመንፈሱ ላይ የሆነውን ነገር ያስተዋልን እንደሆነ ነው፡፡ ይኸውም ኃጢአትን በተመለከተ ለሰው ልጆች ዋጋን ሲከፍል ነፍሱ ተሰቃ አዝናለች ፣ መንፈሱም ታውካለች፡፡ (ሉቃ.22፥44-45) ይህንንም ግድ ያለፈበትና አባቱ ኃጢአትን ሲቀጣ፥ እርሱም የሰውን ኃጢአት ሁሉ ተሸክሞ መገኘቱና ጽኑ ፍርድም ስለሰው ልጅ ሁሉ መቀበሉ ነው፡፡ ይህንንም ፍርድ በተቀበለ ጊዜ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ብሎም ጮኾ ተናግሯል፡፡ (ማቴ.26፥46)
   የሰውን ሁሉ በደልና ነውር ፤ ኃጢአትንም በመሸከሙ  ምክንያት በሰው ላይ ሊተላለፍ የነበረው ፍርድ ሁሉ ፤ ቤዛችን በመሆን በእርሱ ላይ አርፏል፡፡ ከዚህም የተነሳ ጌታችን ኃጢአት ሆኖ ተቆጥሯል፡፡ (2ቆሮ.5፥21) ይህን አስከፊ ነገር ጌታ ከመፍራት የተነሳ አልተሰቀቀም ፤ የመሰቀቁ ነገር ግን ከባህርይው ጋር የማይስማማ ሆኖ ሳለ እርሱ የእኛን ኃጢአት ተሸክሞ መገኘቱ ነው እንጂ ፤ ምክንያቱም ጌታችን ኃጢአት ምን እንደሆነ አያውቅምና ፥ ዳሩ ይህንንም ታግሶ አለፈ፡፡
   ይህንን የፍርድ ስሜት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም ማን ከሰው ወገን ሊረዳው ወይም ሊያውቀው አይችልም፡፡ ጌታችን በአይሁድ እጅግ ከባድ መከራን ተቀብሎ በነፍሱ አዝኖና በመንፈሱ ታውኮ “በእግዚአብሔርም እንደተቀሰፈ እንደተቸገረም ተቆጥሮ” (ኢሳ.53፥4) ነፍሱን ከሥጋው በመለየት አለልክ ዝቅ ዝቅ ብሎ ፤ እስከሞትም ተዋርዶ ወደመቃብር ወርዷል፡፡ (ፊልጵ.2፥8) ደግሞም ይህን አለልክ ዝቅ ዝቅ ያለውን ጌታ “እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና … ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው … ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገው”፡፡ (ሐዋ.2፥24 ፤ 33-34) አከበረውም፡፡ እርሱም “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ … ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ … ”፡፡ (ዕብ.1፥3 ፤ 8፥1) ይህ እንግዲህ የጌታችንን ድል መንሳት ያሳያል፡፡
   በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ባለው የሥርየት መክደኛ ላይ ስለሕዝቡ ኃጢአት ደምን ይዞ ለማፍሰስ ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ ዘወትር ይገባል፡፡ (ዘሌዋ.9፥7 ፤ 16፥15-19 ፤ ዕብ.5፥1-3)  በሥርየት መክደኛው ላይ ያሉትም ኪሩብ ወደደሙ እንዲያዩ ተደርገው መሳላቸውና እግዚአብሔርም ሕዝቡን ይቅር ለማለት በሥርየት መክደኛው ላይ ያለውን ደም ማየቱ ፥ አንድ ብርቱና ዘላለማዊ መልዕክትን በምሳሌነት ያሳየናል፡፡ ሊቀ ካህኑ ደምን ሳይዝ ወደቅድስተ ቅዱሳን ቢገባ ወዲያው ይሞታል ፥ ያ ሞት የጽድቅ ፍርድ ውጤት ነው ፤ ማለትም ራሱ ሊቀ ካህኑ  ነው የሚሞተው፡፡ ደም ይዞ ቢገባ ግን የጽድቅ ፍርዱ ቢኖርም የሚያርፈው በሊቀ ካህኑ ላይ ሳይሆን በደሙ ላይ ነው፡፡
   ስለዚህ ይህ ሁኔታ በብሉይ ኪዳን ደም የእግዚአብሔር ጽድቅ ጥያቄ ምላሽ መሆኑን በምሳሌነት ያሳያል፡፡ ጌታችንም በመስቀል ላይ በሠዋው መሥዋዕቱ ፤ ባፈሰሰው ደሙ የኃጢአት ማስተሥረያ ሆኗል፡፡ (1ዮሐ.2፥2) ያፈሰሰው ደሙም እግዚአብሔር ከእኛ ይፈልግ ለነበረው የጽድቃችን ጥያቄ ፍጹም ምላሽ ነው፡፡ የዚህ ጽድቅ ጥያቄ ምላሽ “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” (1ቆሮ.15፥55) የሚል የድል ዝማሬን መንፈስ ቅዱስ አስቀኝቷል፡፡ ስለዚህ ድል የነሳው ጌታችን እንደሄኖክ በመሠወር (ዘፍ.5፥24) ፤ እንደኤልያስ በእሳት ሠረገላ (2ነገ.2፥11) ያይደለ በመራቅ “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” (ሐዋ.1፥9) እንዲል በበዛ ክብር ወደሰማያት አርጓል፡፡ ባረገም ጊዜ መላዕክት “ወደሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል” (ሐዋ.1፥11) በማለት መስክረውለታል፡፡   
     የጌታችን ዕርገት ሁለት ልዩ መልዕክቶች አሉት ፤ አንደኛው የሰው ልጅ ዕዳ ሙሉ ለሙሉ መከፈሉንና ይህንንም ክፍያ አምኖ በሕይወት ምስክርነት የሚመጣ የትኛውም አማኝ በሰማያት ድል ከነሳው ጌታ ጋር በክብር እንደሚከብር “ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።” (ራዕ.3፥21) የሚል ዘላለማዊ ኪዳን ተገብቶለታል፡፡ ይህም በዙፋን የሚያስቀምጥ ዘላለማዊ ኪዳን ሰውን ቀድሞ በቅድስናና እግዚአብሔርን በመምሰል ወደተፈጠረበት ፍጹም ክብሩ መመለሱን የሚያበስር ትልቅ መለኮታዊ ምስጢር ነው፡፡ በእውነት ዕርገቱ ታላቅና ህሊናን የሚያልፍ ድንቅ መገለጥ ነው፡፡

  የጽድቅን ፍርዳችንን ተቀብሎ እኛን ከሞት በማዳን ወደሰማያት ያረገው ጌታ ውዳሴ ፣ ክብር ፣ ዕልልታ ፣ አዲስ ቅኔና ምስጋና ይገባዋል፡፡ አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment