Thursday 4 June 2015

ጰራቅሊጦስ- መንፈስ ቅዱስ


                             Please Read in PDF


  ከግሪኩ “ፓራክሊቶስ” ወይም ከዕብራይስጡ “ፕራቅሊጥ” ከሚለው ግስ የተገኘው “ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ትርጉሙ “ አማላጅ ፣ አስታራቂ ፣ አፍ ፣ ጠበቃ ፣ ትርጁማን ፣ አምጃር ፣ እያጣፈጠ የሚናገር ፣ ስብቅል ካፉ ማር ጠብ የሚል፡፡ … ፤ ናዛዚ ፣ መጽንዒ ፣ መስተፈስሒ ፤ መንፈስ ቅዱስ፡፡” በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተርጉመውታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 ዓ.ም)፤አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.907)


    ጌታችን ወደሰማያት ከማረጉ በፊት ስለመንፈስ ቅዱስ “ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል … ” (ዮሐ.14፥16) በማለት ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን አጽናኝነት በመግለጥ ለደቀ መዛሙርቱ ፥ ልክ እንደ እርሱ መንፈስ ቅዱስም ሁሉን እንደሚያደርግላቸው የተስፋ ቃልን ሰጥቷቸዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን ደግሞ ጰ[ፐ]ራቅሊጦስ የሚለውን ቃል በቀጥታ ፍቺው “ፓራ” ማለት “አጠገብ” ማለት ሲሆን ፤ “ካሌው” ማለት ደግሞ “መጥራት” ብለው በመተርጎም፥ ሲተነትኑት “ሊራዳ ከአማኝ ጎን የሚቆም” በማለት ተርጉመውታል፡፡ ይህም ሊያጽናና ፣ ሊያበረታታ ፣ ሊያረጋጋ ፣ሊራዳ ፣ ሊያማክር ፣ ሊሟገት ፣ ወገንና ወዳጅ ሆኖ ሊቀራረብ ከአማኝ ጎን ይቆማል የሚል ሃሳብን በውስጡ ይይዛል ብለዋል፡፡
    የመንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስነት ማለትም አጽናኝነት ለቤተ ክርስቲያን ዋናና ዘወትር የሚያስፈልጋት ነገር ነው፡፡ አለሙ በክፉ የተያዘ ስለሆነ (1ዮሐ.5፥19) ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደበጎች በተኩላዎች መካከል የተላከችና በሸንጎ ፊት ተላልፋ ልትሰጥ ፤ ልትከሰስ ፤ በየምኩራቡ ልትገረፍ ፣ ወደገዢዎችና ነገሥታት ልትወሰድ (ማቴ.10፥16-20)፣ በጽኑ መከራ ውስጥ ልታልፍ … ግድ ነውና፥ የዚያኔ “የምትናገረውን የሚሰጣት … እንዴት ወይስ ምን ብላ መመለስ እንዳያስጨንቃት በእርሷ አድሮ የሚናገር አጽናኝ መንፈስ ፤ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
     ዛሬ ላይ ቤተ ክርስቲያን ከቤተ መንግሥት ጋር ተደላድላ ፤ ተመቻምቻ ከመቀመጧም በላይ ፥ መከራውን ፈርታ ከነገሥታት ክፋት ጋር እየተባበረች ክፋታቸውን በመምከር ከማረቅ ፣ በመገሰጽም እንዲመለሱ በማድረግ ጌታዋን ብትመስል “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2ጢሞ.3፥12) እንዲል ሙሽራዋን ያገኘው የዚህ ዓለም ውርደትና መከራ እርሷንም ያገኛታል፡፡ ነገር ግን በመከራው ሁሉ ከነገሥታት ብቻ ሳይሆን ከዓለም ፣ ከሥጋና ከሰይጣን ጋር በምታደርገው ትግል ሁሉ አጽናኝ ሆኖ መንፈስ ቅዱስ ከአጠገቧ በመሆን ያጽናናታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ፣ ለቃሉና ጽድቅ ለሆነው መንገዱ ታማኝ ከሆነች አለም እንዲሁ ልትጠላት ትችላለች (ዮሐ.16፥32) ፤ ምክንያቱም በዚህ አለም ሰላምና ምቾት ሊያጋጥማቸው የሚችለው ለብታዊ  ወይም አስመሣይ ሎዶቂያዊ “አማኝ” (ራዕ.3፥16) ለሆነ ብቻ ነውና ፤ ቤተ ክርስቲያን ግን በብዙ መከራ መንግሥቱን ትወርስ ዘንድ ተጠርታለችና ይህን ማመቻመችና በለብታ ማለፍ  አትችልም፡፡ (ሐዋ.14፥22 ፤ ሮሜ.8፥17 ፤ ኤፌ.6፥12 ፤ 2ተሰ.1፥4)
     ብዙ ጊዜ በሥጋ አይን ሲታይ “የኃይል መመጣጠን” አይኖር ይሆናል ፤  “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ” ቁጥራቸው በየዘመኑ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የአሳዳጆች ጉልበት ፣ የገዳዮች ቁጥር ብዙ ጊዜ ደግሞ እጅግ ብዙ ነው፡፡ (መዝ.90፥7) ነገር ግን ይህን ያልተመጣጠነን ኃይል ቤተ ክርስቲያን እንዳትፈራና እንድትበረታ ፤ እንዲህ ባሉ ኃይለኛና አደገኛ ጠላቶች ፊት በድፍረት እንደትቆም አድራጊውና አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
      እርግጥ ነው፦ እኒህ ጠላቶች ለጊዜው ይህን የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጸጋና የቤተ ክርስቲያን መቃወም ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለሳውል የተነገረው ቃል ዛሬም ሕያው ነው፡፡ “የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” (ሐዋ.9፥6) ምክንያቱም አምላካችንና አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ “ቃሉ እንደእሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ” ነውና፡፡ (ኤር.23፥29)
     ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስን አጽናኝነት ልትቀበል በቀዳሚነት ከእርሱ ጋር በቅድስና ለመቆም መጨከን አለባት፡፡ ከማይጠፋው ዘር ከተወለድን (1ጴጥ.1፥23) የሰውነትን ሥራ በመግደል (ሮሜ.8፥13) ከኃጢአት ፍጹም መራቅ ፤ አለማድረግም ይገባናል፡፡ (1ዮሐ.3፥9) ከሥጋ ሥራ ፍሬ ለመራቅና ከመንፈስ ቅዱስ የሆነውን ፍሬ ለማፍራት ፤ በቅድስና እየኖርን በመከራ ሁሉ ታግሰን ለማለፍ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ (ሮሜ.8፥3)
     የዛሬ ዘመን አማኞች ነን የምንል ሁላችን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን አንድ ጥያቄ ፥ የቤተ ሳሚስ ሰዎች የጠየቁትን ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም “በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል?” (1ሳሙ.6፥20) ቤተ ክርስቲያን ይህን ጥያቄ ደግማ ደጋግማ ራስዋን ልትጠይቅ ይገባታል፡፡ በእውን የዛሬው መከራችን በቅድስና ከአጽናኙ ጋር በመኖራችን ነውን? እንዲያ ከሆነ መልካም! አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን በተኩላው ዓለም እንደበጎች በቅድስና ለሚኖሩ አማኞች ዛሬም ከጎናቸው ሆኖ መከራው ወደተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ወደጽናት ፣ ሐዘኑ ወደደስታ ፣ የወህኒ እስራቱ ወደመዝሙር እልልታ … እንዲለወጥና ለሁል ጊዜ ክርስቶስ ከአጠገባችን እንዳለ እንዲሰማን አድርጎ ፍቅሩን በልባችን እያፈሰሰ (ሮሜ.5፥5) የሚያጽናናን መንፈስ ቅዱስ እርሱ መስተፈስሒያችን ነው፡፡
     መከራው እንደሠንሠለት ቢቀጣጠል ፣ የወዳጅ ክዳቱ ቁጥሩ ባያባራ ፣ አለሙ ሁሉ ጠላት ሆኖ ቢነሳ መንፈስ ቅዱስ ይህንን ሁሉ እያሳለፈ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን ፍጹም ተስፋና ደገፌታ ያጸናልናል፡፡ ፍጹም ከእርሱ ጋር በመጽናናት እናርፍም ዘንድ ደግሞ የታረደው በግ እንዲመጣ “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል።” (ራዕ.22፥17) እንዲል ድካማችንን እያገዘ በማይነገር መቃተት በውስጣችን እየማለደ ፤ እያገዘንም አብሮን መከራ ይቀበላል፡፡ (ሮሜ.8፥26-27)
     አሜን፡፡ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ አምላካችናነ አጽናኛችን ሆይ! እንዲህ እናምናለን ፤ እንታመንብሃለን፡፡      

No comments:

Post a Comment