Wednesday 8 April 2015

በኢየሱስ ላይ የተሤረ ሤራ (ሉቃ.22፥3-6)

        
                              Please read in PDF


      የተወደደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውር ስላበራ ፣ ለምጻም ስላነጻ ፣ አንካሶችን ስላስኬደ ፣ ደንቆሮችን እንዲሰሙ ስላደረገ ፣ ሽባ ስለተረተረ ፣ ጉንድሾችን ስላዳነ ፣ ጎባጣ ስላቃና ፣ ሙታንን ስላስነሳ ፣ አጋንንትን ስላወጣ (ማቴ.9፥25 ፤ 11፥5-6 ፤ 15፥30-31) ፣ በድካም መንፈስ ተይዘው ለሚሰቃዩት ዕረፍትን ስላደለ (ሉቃ.13፥11) ፣ ኃጢአተኞችን ስለተቀበለና ከእነርሱም ጋር ስለበላ (ሉቃ.15፥2)

 ፣  የታረዙትን ስላለበሰ ፤ ያበዱትንና ከሰው የተገለሉትን ከሰው ወገን ስለቀላቀለ (ሉቃ.8፥26-39) ፣ የተራቡትን ስላበላ (ማቴ.15፥32) ፣ የወደቁትን ስላነሳ ፣ ተስፋ የቆረጡትን ስላጽናና ፤ የታሰሩትን ስለፈታ ፣ የተጠቁትን ነጻ ስላወጣ ፣ ለድሆችም ወንጌልን ስለሰበከ (ሉቃ.4፥17) ፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ለተቅበዘበዙ ፤ ለተጨነቁና ለተጣሉት  የሰው ልጆች አይቶ ስላዘነላቸው (ማቴ.9፥36) ፣  በድቅድቅ ጨለማ ለሚኖሩ የሚደነቅን ብርሃን ስላበራ ፣ መጨረሻ በሌለው ፍቅር ወዳጆቹን ስለወደደ (ዮሐ.13፥1) ፣ በጥርጥር የተፍገመገሙትን በእምነት ስላጸና ፣ በጸጋው ቃል ብዙዎችን ስላስደነቀ(ሉቃ.4፥22) ፣ በመሲሕነት የሥልጣን ቃል በማስተማሩ (ማቴ.13፥53 ፤ ዮሐ.4፥42) ፣ መልካምን እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ስለዞረ(ሐዋ.10፥38) … “የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰብስበው ፥  በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ”፡፡ (ማቴ.26፥3-4)
    ነቀፌታ የሌለበት መልካምነት እንደሚያስከስስ፥ የጽድቅ ሕይወትን ያለነቀፋ በእውነት በኖረልንና ባዳነን በክርስቶስ ሕይወት አይተናል፡፡ ፍጹም ንጽዕና በአለም ወንጌሉን በሚያቃልሉና ለወንጌሉ እውነት በማይታዘዙ ፊት ላለመከሰስ ምክንያት ፤ ዋስትና አይሆንም፡፡ በአንደበቱ ተንኰል የሌለበት ፣ መከራን ሲቀበል ያልዛተው (1ጴጥ.2፥23) ፤ በእውነት ፍርድን የሚያወጣና ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ ፣ ጻድቅ ባርያዬ ተብሎ የተተነበየለት (ኢሳ.42፥2-3 ፤ 53፥11) ጌታችን ኢየሱስ “የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት የሐሰት ምስክር ይፈልጉበት ነበር፥ አላገኙም ፤ ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙምና” አንዳች የሚከሰስበት ምክንያት ሳይኖር ተከሷል፡፡ (ማቴ.26፥59 ፤ ማር.14፥55) አንዲት በደል ያልተገኘበት ጌታ ተከሰሰ፡፡ (ዮሐ.18፥38)
     እንግዲያስ፦ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለነውርና ያለነቀፋ የሚያገለግሉና አምነው የሚኖሩ (ሉቃ.1፥7 ፤ 5 ፤ 1ጢሞ.6፥14) ፣ እንዲሁም “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ሊሰደዱ” (2ጢሞ.3፥13 ፤ ኤር.43፥6-7) ፣ ሊነቀፉ (ማቴ.5፥11) ፣ ሊገረፉ (ማቴ.10፥17 ፤ ሐዋ.5፥40 ፤ 16፥23) ፣ ሊገደሉ (ሐዋ.7፥58 ፤ 12፥2) ፣ ሊጠሉ (ዮሐ.15፥18) ፣ በሐዘን ሊሰበሩ (ኤር.4፥19 ፤ 9፥1 ፤ 10፥19 ፤ 2ጢሞ.4፥10) እንደሚችሉ ጌታችን አስቀድሞ በግልጥ ተናግሯልና እርሱን ያገኘው ሁሉ ሊያገኘን ግድ ነው፡፡ በእርግጥም ሙሽራው ከተዋረደ ሙሽራይቱ ትታይ(ትከብር) ዘንድ ወዴት አለች?!
   ሰይጣንና ወዳጆቹ ለመክሰስ የሚያሤሩት፥ ምክንያት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ነው ፤ ሤራቸውን ግን ከግብ የሚያደርሱት ኢየሱስንና የመንግሥቱን ወንጌል ከማገልገልና ሕይወታቸውንም ሙሉ ለሙሉ ለጌታ አሳልፈው በማይሰጡ “አገልጋዮች ፤ አማኞች” በመጠቀም ነው፡፡ ከጥንት ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክነቱን የሚጠቀመው መንፈሳዊ ለዛና ዘይቤን በመጠቀም ነው፡፡ (2ቆሮ.11፥14) የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ ሕዝቡን ፈርተው ጌታን ለመያዝ ባይቻላቸውም ፥ በይሁዳ በኩል የመግባት ዒላማቸውን ሰይጣን በሚገባ አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ ብዙዎቻችን ክርስቶስን ጨክነን የተከተልን አማኞችና አገልጋዮች ሕመማችንና ቁስላችን “ክርስቶስን እናውቃለን” በሚሉ “ወዳጆች” የተሰበርነው ስብራት ነው፡፡ እውነትም “ክርስቶስን ያልተረዱቱ” ከበደሉን በደል ይልቅ “ያውቃሉ” የተባሉቱ የበደሉን በደል ቁስሉ እጅግ ያመረቅዛል፡፡
   ይሁዳ ከመጀመርያው ጀምሮ ሌባና ያልታመነ ነው (ዮሐ.12፥5) ፤ ይሁዳን የታገሰ የክርስቶስ ኢየሱስ ትዕግስት እንደምን ያለ የሚደንቅ ትዕግስት ነው?! መግቢያ በር ለሚሹ ፥ ካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎዎች ገንዘብ አፍቃሪው ይሁዳ ሤራቸውን ከግብ ሊያደርስ እንደሚችል ሲነግራቸው “ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ።” (ሉቃ.22፥5) ፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛትና “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (ማቴ.6፥24 ፤ 1ጢሞ.6፥10) እንዲል ይሁዳ ስለገንዘብ ብሎ ውድ ወዳጅ ፤ አምላኩንና በብዙ የቻለውን ጌታ ሸጠ፡፡
   ዛሬ ላይ ስለገንዘብ ተብሎ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል እየሆነ ያለውን ለምንሰማና ለምናይ የክርስቶስ ወገን ላለመሆናችን በቂ ማስረጃ ነው ፤ ግብረ ሰዶማውያንን የሚያሰለጥኑና ገንዘብ የሚሰበስቡ ፣ በወላጅ አልባ ሕጻናትና በእስረኞች ስም ማህበር አቋቁመው ቤታቸውን የሚያደራጁ ፣ በወንጌል ስም ተደራጅተው የጌታን ሕዝብና አማኝ የሚበዘብዙ … ስለገንዘብ ሁሉንም ቢሆኑ እፍረት ያልተሳለባቸው አገልጋዮችና ምዕመናን ቁጥራቸው ያስፈራል፡፡
    “አይሁድ” ሰውን በመግደል እንደረከሱ ወይም የጌታን ህግ እንደጣሱ አያስቡም ፤ ነገር ግን  “የፋሲካን በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም።” (ዮሐ.18፥28) በሌላ ንግግር ወደገዢው ቀያፋ ግቢ እንዳይረክሱ አይገቡም ፤ ጌታን ሲገድሉ ግን አይረክሱም፡፡ ትንሹን ያጠራሉ ፤ ተራራ የሚያህለውን ነውርና ክፋት ይውጣሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚያሤሩ ፣ የሚያድሙ ፣ የሚከሱ ፣ የሚያሳድዱ ሰዎች መገለጫ፥ ወንጌልን ሳይሆን የሰው ሥርዓትን በማስበለጥ ይታወቃሉ፡፡ የአይሁድ መሪዎች ለትልቁ የጌታ ሕግ ሳይሆን ለራሳቸው ሥርዓት የሚጨነቁ ነበሩና፡፡ ወንጌሉ የሕይወትና የኑሮ ሚዛን ካልሆነን ኃጢአቱ ከብሮብን ጽድቁ ይዋረድብናል፡፡ የእውነትና የቅንነት መንገድ ማጥሪያና መለኪያ ሚዛኑ የሰው ሥርዓትና “የታላላቅ” ሰዎች አድማ ሳይሆን የመድኃኒታችን ወንጌል ብቻ ነው!!!
   የይሁዳ የአሳልፌ ልስጣችሁ ሴራ ለካህናት አለቆችና ለአይሁድ ደስታ ነው ፤ ሰው በሰው ሞት እንዴት ይረካ ዘንድ ይቻለዋል? ጌታ ለጠላት እንኳ እንድንራራ አስተምሮ ይሁዳ ምነው በመምህሩ ፣ በወደደውና ገመናውን ሸፋኝ በሆነ ጌታ ላይ ለመጨከን ተነሳሳ? ይሁዳን የሚረግሙ ከይሁዳ በማይተናነስ ነውርና ኃጢአት የተያዙ ፣ እንደይሁዳ ላለመሳሳም የሚጠነቀቁ የገዛ ወዳጃቸውን ግን እንደበግ በብር የሚተምኑ ፣ ቀን ከአምልኮ ሥፍራ የማይጠፉ ማታውን ግን ከወንበዴ ጋር የሚያሤሩ ፣ ሁለት መልክ ፣ ሁለት ቋንቋ ፣ ሁለት ጉባኤ ተካፋዮች ዛሬም አሉ፡፡
   አሳልፈው መስጠት የሚችሉበት ምቹ ሰዓት እስኪመጣ አብረው ሻይ የሚጠጡ ፣ ሰላማዊ መስለው ሰባራ ቀን የሚጠብቁ ፣ አብረው የሚዘምሩ ፣ አብረው የሚሰብኩ ፣ አብረው የሚጸልዩ ፣ አብረው የሚስቁ ፣ አብረው አገር የሚመሩ ፣ አብረው መንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሠሩ  … የልባቸውን በር ለሰይጣን ምቹ አሠራር የከፈቱ፥ ይሁዳውያን ሤረኞች ዛሬ በመንፈሳዊው ዓለም ቁጥራቸው ከልክ ያልፋል፡፡ አይሁድ በሞቱ ፣ ይሁዳም ገንዘብ በማግኘቱ የረኩ ይመስላሉ ፤ ኢየሱስ ግን ዛሬም በግርማዊ ዙፋኑ አለ፡፡ ከሳሾች ፣ ሴረኞች ለጊዜው ያሸነፉ ቢመስላቸውም በኢየሱስ መንፈስ ጸንተው የሚኖሩ ግን በእውነት “አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም ፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራዕ.7፥16-17) እንዲህ ላለ ክብር ታጭተናልና ደስ ይበለን፡፡ አሜን፡፡

ጌታ ሆይ!  እውነትንና ማዳንን ለሕዝብህ አብዛ፡፡ አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment