Wednesday, 22 April 2015

“ጌታ ሆይ፥ በISIS ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው”




በድጋሚ በግፈኛው ISIS ለተሰው ክርስቲያን ኤርትራውያን ፣ ኢራቃውያን ቤተሰቦች ጌታ መንፈስ ቅዱስ መጽናናትን እንዲያድላቸው ብርቱ ጸሎታችን ነው!!!
    የአንዲት ሕያው ቤተ ክርስቲያን ልዩና የሁል ጊዜ መገለጫ፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ለሁሉ በማዳረስ ማስፋትዋና የደቀ መዛሙርትን ቁጥርና እጅግ የሚታዘዙትንም ማብዛቷ ነው፡፡” (ሐዋ.6፥7) የባለበት ሂድ ወይም የእየቀጨጩ ዕድገት ጤናማነቱ ተፈጥሮዐዊም ፤ መንፈሳዊም አይደለም፡፡ በብዛትም በጥራትም ማደግ የጤናማ ተፈጥሮዐዊና መንፈሳዊ ዕድገት መገለጫ ነው፡፡ ወንጌሉ ሕያው ነውና ተበትኖ ፤ ተሰብኮ እንደዋዛ አይቀርም ፤ ሕያው ፍሬንም ያፈራል እንጂ፡፡
     ክርስትና ገና ጉዞውን በጀመረበት ቀደምት ጊዜያት፥ በአንድ የስብከት ርዕስና በአንድ ብርቱ ተአምራት ስምንት ሺህ የሚጠጉ አማኞች ወደአንድ መቶ ሐያው የጌታ ቤተሰብ ተጨመሩ፡፡ ሥራውን ሠሪው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ የቁጥሩ አጨማመር ከመደመርም ከብዜትም ይልቃል፡፡ እኛ የቀደምንበት አገልግሎት ጠላትን አለጊዜው ያጎለምሳል ፤ ጌታ የቀደመበት አገልግሎት ግን ጠላት ተኩላ እያለ ሥራውን ያሠራል፡፡(ማቴ.10፥16)

     ክርስትና ገና ከኢየሩሳሌም ሳይወጣ ፤ ያመኑት የመጀመርያው ወደስምንት ሺህ የሚጠጉ ክርስቲያኖች በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ እስጢፋኖስ በስምንት ሺህ አማኞች ላይ አሳላፊ ሆኖ እያገለገለ ባለበት ወራት፥ “የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤” (ሐዋ.6፥9)
      ጌታን በአድመኝነት አሳልፈው የሰጡት እኒያው ሰዎችና መሪዎች ዛሬም በእስጢፋኖስ ላይ ተነሳሱበት፡፡ ተኩላው ይጮኻል ፤ ያደባል ፤ በጎቹም ተኩላዎቹ ባሉበት ዓለም ይሠማራሉ፡፡ ለጌታ ያልራሩ ገዳዮች እንዲሁ ለእስጢፋኖስ ስስ አንጀት የላቸውም፡፡ “እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። … ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም።” (ሐዋ.6፥8 ፤ 10)
     እስጢፋኖስ በተቃዋሚዎቹና በገዳዮቹ ፊት ምስክርነቱን የሰጠው በግልጥ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ምስክርነት በእግዚአብሔር ፊት ለዘወትር ቃሉን በማጥናት ፤ በጸሎትም በመትጋት የሚመጣ ነው፡፡ እስጢፋኖስ የመሰከረው ምስክርነት አይሁድን መልስ ያሳጣና ድንቅ ምስክርነት ነው፡፡ ምስክርነቱን መቃወም ስላልተቻላቸው የሐሰትን ክስ በሚገባ አቀናበሩበት፡፡ (ሐዋ.6፥13-14)
      ሊቀ ካህናቱም ፊት በቀረበ ጊዜ ሳያፍር ፣ ሳይፈራ ለሕዝቡ የተነገረውን የመሲሁን ይመጣልን ከሥሩ ጀምሮ ተረከላቸዋል ፤ ባልተቀበሉትና በገደሉት መሲህ ፊት ለፊት አምጥቶ ገተራቸው፡፡ ፊት ተሟግተው ባላሸነፉት ጊዜ ከተበሳጩት መበሳጨት ይልቅ፥ የአሁኑን ምስክርነት “በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።” (ሐዋ.7፥54) ጠላት በተሸነፊ ጊዜ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራል” እንጂ ምንም አቅም የለውም፡፡ በሌላም ሥፍራ ጌታችን “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል እንደማይቻላቸው” ተናግሯልና በነፍሳችን ላይ ምንም ሥልጣን የላቸውም፡፡ (ማቴ.10፥28 ፤ 1ጴጥ.5፥9) ግና ጠላት ነፍሳችንን ያገኘ እየመሰለው ሥጋችንን አብዝቶ ያሰቃየዋል፡፡
    እስጢፋኖስ ስለመሲሁ እውነተኛ ምስክርነትን ከሰጠ በኋላ ሹመት ፤ ሽልማት አልገጠመውም፡፡ በቃሉ ተናግሮ የመሰከረውን የመሲሁን መሞትና በክብር ትንሳኤ ተነስቶ በአባቱ ቀኝ በሕያውነት መቆም በሰሙ ጊዜ “በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ” ፤ (ሐዋ.7፥57-58) ዓለም የአብ አንድያ ልጁን “ከወይኑ አትክልት ውጪ አውጥታ እንደገደለችውና” (ማቴ.21፥39) “ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ።” ተብሎ እንደተነገረለት እንዲሁ እስጢፋኖስንም “ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት።” (ሐዋ.7፥58)
   እስጢፋኖስ ሲወገር አንድ ጎበዝ የገዳዮችን ልብስ ይጠብቅ ነበር፡፡ ሟቹ እንዲገደል ትዕዛዝ እየሰጠ የገዳዮችን ልብስ ይጠብቃል ፤ እየጠበቀም መወገሩን ያያል፡፡ እስጢፋኖስ በመጨረሻይቱ ሰዓት እንደመሰከረለት መሲህ ኢየሱስ፥ ስለሚወድሩት ጠላቶቹ “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው” የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጣ፡፡  የሚረግምን መባረክ ፣ የሚጠላን መውደድ ፣ ክፉ ለዋለ መልካም ብድራት መመለስ (ማቴ.5፥43 ፤ ሮሜ.12፥20-21) በደሙ ከዳነ አማኝ የሚገኝ የቅድስና ፍሬ ነው፡፡ ክርስቲያን ተብለን ስለተጠራን ብቻ ይህ ፍሬ አይኖረንም ፤ በጸጋው ከዳንን ፍሬውንም ልናፈራ ይገባናል፡፡ የየዋህነትና የብልኀነት መንገድ (ማቴ.10፥16) አሁን ነው መጀመር ያለበት፡፡ ለመመስከር ቀድሞ በልብ ማመን ይገባናልና ከሞትን አይቀር ለጠላት ምህረትን አድርገን እንሙት፡፡
   የእስጢፋኖስ የምልጃ ልመና የገዳይን ልብ ለንስሐ ጠርቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምርጡን ሐዋርያ ጳውሎስን ያገኘችው በእስጢፋኖስ ጸሎት ነው፡፡ ገዳዮችን መሳደብ ፣ መዝለፍ ፣ በከንቱ መራገም አይገባንም ፤ ይልቁን ካራና ስለት ለጨበጠ እጅና ልባቸው ጸሎትና ምልጃ ያሻል፡፡ ምክንያቱም እኛም በክርስቶስ ደም ከሞተ ሥራ ህሊና (ዕብ.9፥14) ዳንን ፣ ከቁጣ ልጅነት ወደጸጋ ልጅነት ተመለስን እንጂ፥ (ኤፌ.2፥3) እኛም የዲያብሎስ ሠራተኞች ነበርንና፡፡(ዮሐ.8፥44) እንኪያስ ላልተገባን ሰዎች ክርስቶስን በማመናችን እንደ“የተገባን” ከተቆጠርን ፤ ላልተገባቸው እኛም ምህረትን ልንለምን ፤ ልንማልድላቸው ይገባል፡፡
    ቤተ ክርስቲያን ለሞቱት ብቻ ሳይሆን ለገዳዮችም እጅግ እጅግ አብዝታ ልትጸልይ ይገባታል፡፡ አምላካችን አመጸኞችን ሲምር ለመታየቱ እኛም ከታላቁ መጽሐፍ ቀጥሎ ሕያው ምስክሮች ነን፡፡ ጳውሎስ የእስጢፋኖስን ቤተሰብ አጥምቋል፡፡(1ቆሮ.1፥16) የእስጢፋኖስ ቤተሰብ እንዴት ያለ ድንቅ ቤተሰብ ነው?! በልጃቸው ገዳይ እጅ አጎንብሰው የተጠመቁት?! ኦ! ክርስትና እንዴት ያለ ድንቅ የምህረት መንገድ ነው!? ኦ! ኢየሱስ ፍቅርህ እንደምን ከህሊና መረዳት በላይ ይሰፋል?!
     ISIS ይህን ድርጊት የሚያደርጉት የሞተላቸውን ጌታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነው፡፡ ክርስቶስን ያላወቀ ሳውል ክርስትናን ይገፋ ፤ ክርስቶስን ያሳድድ የነበረው ልክ አምላኩን እንደሚያገለግል ሰው በመቅናት ነው፡፡ ISISም ይህን የሚያደርጉት አምላካቸውን የሚያገለግሉ እየመሰላቸው ነው፡፡ እንኪያስ! ከእኛ መካከል የመታረዱና የመገደሉ ጽዋ ለማን እንደሚደርስ አዋቂው ጌታ ብቻ ነው! መቼም ይሁን መች ግን እስጢፋኖሳውያን ሆነን ብዙ ሳውሎች ከገዳዮች መካከል እንዲመለሱ የምንጸልይ ስንቶች እንሆን? የጸለዩትስ ስንቶች ይሆኑ?
      አዎን! እንጸልያለን፦ “ጌታ ሆይ፥ በISIS ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ፤ ይቅርም በላቸው”፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ ይህን እውነት “በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች፡፡” በማለት አስቀምጦታል፡፡ አሜን ጌታ ሆይ ይቅር በላቸው ፤ ደግሞም ተመልሰው የስምህ ምስክር እንዲሆኑ እርዳቸው ፤ የጳውሎስ ዕጣ ለእነርሱም ትውጣላቸው፡፡ አሜን፡፡


2 comments: