Saturday 11 April 2015

“የተሰቀለው … ተነስቶአል ፥ በዚህ የለም፤” (ማር.16፥6)



Please read in PDF

እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ!!!
     የሙታን ትንሳኤ ትምህርት ክርስትና ከቆመባቸው መሠረታውያን ዶግማውያን ትምህርቶች ከሆኑት አንዱና ዋናው ትምህርት ነው፡፡  (1ቆሮ.15፥13 ፤ ዕብ.6፥2) መናፍቃን ከሚመዘኑበት መመዘኛ አንዱ ለትንሳኤ ሙታን ባላቸው የአስተምህሮ አቋም ነው፡፡ የትኛውም አማኝም ሆነ የእምነት አቋም ትንሳኤ ሙታንን በግማሽም ቢሆን ባጠቃላይ ቢክድ በቀደመው ዘመን ከነበሩት መናፍቃን እንደአንዱ መቆጠሩ ምንም የማያሻማ ነው፡፡ ሐዋርያው ለዚህም ነው ፦ “ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት ፤ ደግሞም፦ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።” (1ቆሮ.15፥13-15) በማለት አጽንቶ የተናገረው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ለዚህ በአንቀጸ ሃይማኖቷ “የሙታንን ትንሳኤ እናምናለን” በማለት በግልጥ የምትመሰክረው፡፡

      ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የአርማትያሱ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በቀበሩት ጊዜ፥ አይሁድ ከሙታን መካከል ቢነሳ የበለጠ እንዳይዋረዱ በመፍራት ፥ እንዲይዙት ወይም ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው ተነሳ እንዳይሉ መቃብሩንና የጌታን ሥጋ በተመረጡ ብርቱ ወታደሮች አስጠብቀዋል፡፡ (ማቴ.27፥66) ጌታ ግን ሞትና መቃብር ሊይዘውና ሊገዛው ከቶ ስለማይችል (ሮሜ.6፥9 ፤ ራዕ.1፥18)  ከሙታን መካከል በገዛ ሥልጣኑ ተነሣ፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የጌታን ከሙታን መካከል መነሳትን ከትምህርቱ በሚገባ ሰምተውታል ፤ አምነውታልምና ፥ ሞቶ እንደተቀበረ ወዲያው ወደጲላጦስ መጥተው “ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ፦ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።” በማለት ተናግረውታል፡፡ (ማቴ.27፥63)
    አይሁድ ትምህርቱን በንቀት መልክም ቢሆን አምነው ተቀብለዋል ፤ ነገር ግን ከክርስቶስ እውነት የእነርሱ ክብር ስለበለጠባቸው ክብራቸውን በማሰብ “የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና” በማለት መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ አዘዙ፡፡ ፊተኛው ስህተት በህዝቡ ዘንድ “ኢየሱስ መሲህ ነው” ተብሎ መነገሩ ሲሆን፥ ሁለተኛው ስህተት ደግሞ እርሱ ኢየሱስ ከሙታን መካከል ቢነሳ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ ከሙታን መካከል ተነሳ” ብሎ ሕዝቡ ሁሉ ይከተለዋል የሚል ፍርሃታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ሙሉ ለሙሉ ዕውቅና የማጣት ችግር እንዳይገጥማቸው ቀድመው መጠንቀቃቸው ነው፡፡ ያለእግዚአብሔር ፈቃድ የራስን ክብር መጠበቅ እጅጉን ለሚያሳዝን ውርደት አሳልፎ ይሰጣል ፤ የሰው ክብሩ ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ሲጥለው ብቻ ነው፡፡ ምጽዋታችን ተሸሽጎ ካልተሰጠ ፣ ጸሎታችን ደጅ ዘግቶ  ካልሆነ ፣ ጾማችን ካልተሰወረ (ማቴ.6፥3 ፤ 6 ፤ 18) ... ድንገት ላይሰበሰብ ይበተናል፡፡ በሰው ፊት የተጠነቀቅንለትን ነገር መልሰን አናገኘውም ፤ በእግዚአብሔር ፊት የጣልነውን ግን በክብር ማንሳታችን የታመነ ነው፡፡
    ጌታችን የሞተው ሞት የተለየና እጅግ የከበረ ነው፡፡ በሞቱ እንድንና        ሕይወትን እናገኝ ዘንድ “የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል።” (ዮሐ.3፥14) ነገር ግን የጌታችን ሞት ያለትንሳኤ እጅግ ከባድና ሙሉ ለሙሉ የክርስትናን ትምህርት ውድቅ የሚያደርግ ነው ፤ ምክንያቱም “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸክሟልና” (1ጴጥ.2፥24) እንዲሁም “ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ” (ሮሜ.6፥4) ትንሳኤው ሕይወታችን ነው፡፡ ስለዚህም ሞትን አሸንፎ ከሙታን መካከል የተነሳው የክርስቶስ ትንሳኤ የእግዚአብሔር ልጅነቱንና ኃያልነቱን የተረዳንበት ዋና ምስጢራችን ነው፡፡ (ሮሜ.1፥4)
      ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ከሙታን መካከል በመነሳቱ የሞት አስፈሪነት ድል ተነስቷል፡፡ (1ቆሮ.15፥55) በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች፥ ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚያስቡም ሁሉ ስለሞት ያላቸው አቋም አጋጋዊና እጅግ በመፍራት (1ሳሙ.15፥32) ፥ እንጂ ጳውሎሳዊ ያልሆነበት (2ጢሞ.4፥6) ምክንያቱ ለወንጌል የኖርነውንና ያገለግልንበት ሕይወታችን በኃጢአት ነቀፌታና በነውር የተሞላ ስለሆነብን ነው፡፡ የተሰቀለው ጌታ ከሚያስተምረን ትልቁ የጽድቅ ሕይወቱ በቅድስና ለመኖር የራስን ክብር መጣልና “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ እንዳደረገው”(ፊልጵ.2፥7)እንደተባለው እኛም እንደክርስቶስ ኢየሱስ የየራሳችንን መስቀል በመሸከም ፣ አዲሱን የትንሳኤውን ሕይወት ለመኖር ለኃጢአት በመሞት በጽድቅ ልንኖር ይገባናል፡፡
  እሁድ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ እንደአይሁድ ልማድ የጌታን ሥጋ (በድን) ሽቱ ለመቀባት ሴቶቹ ወደመቃብሩ በመጡ ጊዜ ያልጠበቁት ነገር አጋጥሟቸዋል፡፡ ጌታ ዝጉን መቃብር ሳይከፍት ቢነሳም የጌታ መልአክ ግን “ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?” (ማር.16፥3) የሚለውን ጥያቄ መልሶ፥ ድንጋዩን ከመቃብሩ አፋፍ አንከባልሎ ጠበቃቸው፡፡ ሴቶቹ ወደውስጥ በገቡ ጊዜ መልአኩን በመቃብሩ ውስጠኛው ክፍል በስተቀኝ ተቀምጦ ስላዩት ደነገጡ፡፡ “እርሱ ግን ፦ አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።” ብሎ በሚያጽናና ቃል ተናገራቸው፡፡ (ማር.16፥6)
    መልአኩ ለሴቶቹ የተናገረው ልዩ ምልክትን በመስጠት ነው ፤ “የተሰቀለው” የሚል፡፡ ከሙታን መካከል የተነሳው ያ የተሰቀለው ፣ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ የነበረው ፤ የካህናት አለቆችና መኳንንቶች ለሞት ፍርድ አሳልፈው የሰጡትና (ሉቃ.24፥19) የተዋረደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የጌታችን ልዩ ምልክቱ ሞትና ስቅላቱ ነው፡፡ እርሱም “ሞቼም ነበርሁ” (ራዕ.1፥18) በማለት ራሱን የገለጠ ጌታ ነው፡፡ እርሱ በቁም ሳሉ ከሞቱት ቅምጥሎች ጋር ሳይሆን ግንኙነቱ (1ጢሞ.5፥6) ስለስሙ ከተነቀፉት ፣ ከተሰደዱት ፣ ክፉው ሁሉ ከሚነገርባቸው ፣ ከሚናቁትና ከተገፉት ጋር ነው ፍጹም ትስስሩ፡፡ (ማቴ.5፥11 ፤ 10፥16-23)
    ዛሬ ላይ የመስቀሉ ክርስቶስ ያለው ተገፍቶ ከመቅደሱ ውጪ ነው፡፡ ጌጠኛውና ቅምጥሉ ፣ መስቀል አልባው ፣ ባዕለጠጋውና ሃብትን አጋባሹ ኢየሱስ ደግሞ ከምን ጊዜውም በላይ ተወዶ ሲሰበክ ፣ ተፈቅሮ ሲመለክ እያየን ነው፡፡ ባዕለጠግነትን ከሚጠሉ ወገኖች አይደለንም ፤ ባዕለጠግነትን ከክርስቶስ አስበልጠው፥ ሰማያዊውን ሃብት ሁሉ በምድር ቀይረው ከሚሰብኩት ግን በተቃራኒው የምንቆም ነን፡፡ ነገር ግን ሞትን ድል የነሳው ኢየሱስ የተሰቀለው እንጂ መስቀል አልባውና ባዕለጠግነትን አቀንቃኙ ኢየሱስ እንዳይደለ እናምናለን፡፡ እርሱ በሙታን መካከል የለም ፤ እኛን ለጽድቅ ሕይወት ሊያነቃን እነሆ! ተነስቷል!!!

  ጌታ ሆይ! መነሳትህን እናምናለን! እኛንም ለጽድቅ ሕይወት እንድንኖር ለኃጢአት ሕይወት የሞትን እንድንሆን እርዳን፡፡ አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment