Monday 20 April 2015

“ISIS” በድርጊቱ እኛን ምን ያስተምረናል?

              
                          Please read in PDF
                             
           

አስቀድመን በድርጊቱ እጅግ ላዘኑ የሟች ቤተ ሰቦችና ክርስቲያኖች ሁሉ የመጽናናትን መንፈስ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ እንዲያድላቸው እንመኛለን፡፡

     አለሙ እጅግ በክፋት እንደተያዘ (1ዮሐ.5፥19) ፤ ክፉዎችም ምድርን ሊያስጨንቋት እንደሚችሉ ታላቁ መጽሐፍ በግልጥ ይነግረናል፡፡ (ማቴ.24፥21) ክፉዎች ምድርን የሚያስጨንቋት በሦስት ብርቱ ምክንያቶች ይመስለኛል ፦
1.     የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእግዚአብሔር ሲለይ፤
2.    ህዝቡ መለየቱን ሳያውቅ ንስሐ ሳይገባ ሲቀር ፤
3.    ያመንነው ወንጌል ጠላትን እጅግ ያስጨነቀው እንደሆን፡፡

      የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእግዚአብሔር ሲለይ ፦ የእግዚአብሔር ህዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ሳለ ብርቱና ማንም የማይቋቋመው እንደሆነ ከጥንት በምርጥ ህዝቡ በእስራኤል ፤ በኋላም በአዲስ ኪዳን የታየ ነው፡፡ እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር በነበሩ ጊዜ ማንም እንደማይችላቸው “«ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ” ፣ (ዘጸ.3፥14) “በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ አልጥልህም፥ አልተውህም።” (ኢያ.1፥5) ፣ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ” (ኢሳ.43፥5) ተብሎ የተገለጠ ሲሆን ፤ ከእርሱ ፊታቸውን ዘወር ባደረጉ ጊዜ ደግሞ አስጨናቂዎቻቸው “የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። … እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር።” (መሳ.6፥1 ፤5) ተብሏል፡፡
  ስለዚህም የእግዚአብሔር ህዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ እየመሰለው የሚለይበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ታቦት ባለመያዛቸው የተሸነፉ የመሰላቸው የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ፤ የእግዚአብሔርን ታቦት ከከተማ ሲያስመጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ እንደተለየ አላስተዋሉም ፤ ከዚህ የተነሳ ታቦቱን አምጥተው ቢዋጉም ፥ እነርሱ ከመገደል ፣ ታቦቱ ከመማረክ ምንም የተረፋቸው ነገር አልነበረም፡፡ (1ሳሙ.4፥3)
    በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን እየመሰለን፥ ተለያይተን የምንኖርበት ጊዜ ካለ ፤ ይህን ባለማወቅ ደግሞ ንስሐ የማንገባበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ በእርግጥ ሰው መበደሉን አውቆ ወደልቡ ካልተመለሰ (ሉቃ.15፥17) ንስሐ የመግባት ዕድል የለውም፡፡ ናዝራዊው ሳምሶን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደተለየ ሳያውቅ ሥራ ሊሠራ ተነሳ፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ መለየቱን ባወቀ ጊዜ ግን ምንም ሥራ መሥራት አልተቻለውም፡፡ (መሳ.16፥20-21) ማወቃችን መበደላችንን ካልገለጠ በቀር ዕውቀት ገዳይ ብቻ ይሆናል፡፡
   ከመንፈሳዊነት ውጪ ያሉብን ልምምዶች ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ፊት ያርቁናል፡፡ በተለይ እንደደሊላ ካሉ ጋር የሚደረጉ ሶምሶናዊ ልምምዶች ትውልድን ወደጥፋት ማዕበል መንዳቱ የማይጠረጠር ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሰዐት ወደረኞቻችን ዓይናችንን አውጥተው ፣ በግዞት ሳያስሩንና ሳይቀልዱብን፥ አዲሱን የዕርቅ መንገድ ንስሐን መጀመር ትልቅ ማስተዋል ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን እየመሰለን ፣ የምንጠፋበት መንገድ ብዙ ጊዜ የማይመልስና የሞት መንገድ መሆኑ አይቀርምና ንስሐ እንግባ፡፡
     ሦስተኛው ጠላት ዲያብሎስ በምድር ላይ ከሚጠላቸው ወገኖች እነማንን ነው? ብንል ወንጌል የጨበጡ ክርስቲያኖችንና በክርስቶስ የሆኑ የጸሎት ሰዎችን ነው፡፡ ከጥንት ደቀ መዛሙርቱ ወንጌልን ጨብጠው የኢየሱስን ክርስቶስነት ስለሰበኩ በሰማዕትነት አለፉ ፤ ቄሳራዊውን የፍጡር ጌትነት ክደው የአዳኙን ኢየሱስ መሲህነት በመስበካቸው አሁን እየሆነ ካለው የሚበልጥ መከራና ሥቃይ ደረሰባቸው ፤ የዲያብሎስን መውደቅ ፣ የሞትን መሸነፍ ፣ የኃጢአትን ድል መነሳት ስለሰበኩና የክርስቶስን የትንሳኤ ኀይልና በሞት ላይ ያለውን ግርማ ስላወጁ አለም በሙሉ ኃይሏ ጠላቻቸው፡፡
    በጥንት የሠላምን ወንጌል የሰበኩ ምላሶች ተቆርጠዋል ፣ አንገቶች ተቀልተዋል ፣ እግሮችና እጆች ተነስተዋል ፣ አፍንጫዎች ተፎንነዋል ፣ ቋንጃዎች ተተልተዋል ፣ ቆዳዎች ተገፈዋል ፣ ሴቶች በብልቶቻቸው ፍህምን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ጠላት ወንጌሉን ለመስበክ በጨከንንና በቆረጥን መጠን እርሱም ዳር በሌለው ጭካኔው እንደሚዘምት እናውቀዋለን፡፡ ዛሬም ቢሆን “ክርስቲያን” የሚለውን ስም ብቻ የጨበጡ ወገኖቻችንን ሲታረዱ ትላንት በኢራቅ ፣ በማሌዢያ ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በኢንዶኔዢያና በግብጽ … አይተን ከሐዘናችን ሳናገግም ይኸው በአገራችን ክርስቲያኖችም ላይ ተደገመ፡፡ (ለእኛ የደነገጥነውን ያህል ግን ለሌሎች ክርስቲያን ወንድሞች ደንግጠን ነበር?) ሩቅ የመሰለው ይኸው ገስግሶ ከደጃችን ደረሰ!!!
   አሁን አንድ ነገር ወደልቤ መጣ ፤ ISIS ያገኙትን ክርስቲያን ሁሉ መግደልን ተያይዘውታል ፤ አስተውሉ! የየትኛውንም አገር ክርስቲያን ለቅጽበት አይራሩለትም፡፡ ማረድና መግደል እንጂ ምንም የመኖር ዕድል አይሰጡም፡፡ እነርሱ ይህን ያህል ላመኑት ሰይጣናዊ እምነታቸው ታማኝና ጨካኝ ናቸው ፤ ነገር ግን እኛ አማኞቻችንን ምን ያህል በወንጌል እውነት እያስታጠቅን ነው? ድንገት በተያዙ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜና ቦታ የወንጌሉን እውነት እስከሞት በመጨከን እንዲመሰክሩ ምን ያህል እየተጋንላቸው ነው?
   ሌላም ነገር ወደልቤ መጣ፦ ISIS በዓለም ባሉ ሁሉም ክርስቲያኖች ላይ ካነጣጠሩ፥ እኛስ በዓለም ላይ ያለን ክርስቲያኖች በጸሎትና ቃሉን በማጥናት ምን ያህል እንተጋለን? እነርሱ በበረሃውና በየባህር ዳርቻው ለማረድና ለመግደል ከተስማሙ፥ እኛስ የጀመሩት የኃጢአት መንገዳቸው እንዳይፈጸም ፣ የቀጠሩት የሞት ቀጠሮ እንዲፈርስ በእውኑ በአንድነት የምንጸልይ ፣ የምንስማማ ነንን? ይህን ሳስብ እጅጉን ይጨኝቀኛል!!! መባላታችንና እርስ በእርስ መነካከሳችን የጠላትን ኃይልና ጉልበት ያበረታው ይመስለኛል፡፡
   “ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እኛ እንደወረደ” እንዲሁም “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ” እንደመጣ እናምናለን፡፡ (ራዕ.12፥12 ፤ 17) ጥቂት ስለቀረው ብዙ መግደል ፣ ብዙ ማጥፋት ፣ ዓለሙን ሁሉ በብርቱ መከራ መግዛት ይሻል ፤ ነገር ግን በመግደልና በማረድ ለማሳመን የሚጥረው የጠላት መንገድ መሸነፉን በግልጥ የሚያሳይ ነው፡፡ ዲያብሎስ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ተዋርዶ ቢሸነፍ፥ ደቀ መዛሙርቱን በመግደል የረካ መሰለው ፤ ዛሬም የዲያብሎስ ደቀ መዛሙርት ክርስቲያኖችን በማረድ የረኩ የመሰላቸው፥ ስለተሸነፉና መሸነፋቸውን መግለጫ መንገድ ቢያጡ ነው፡፡
   እናምናለን! በጉ በጽዮን ተራራ አለ! እናምናለን! የታረዱትን የሚያጽናና የታረደው በግ ሙሽራው ኢየሱስ በሰማያት አለ! እናምናለን! የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሚስቲቱ ቤተ ክርስቲያን ራስዋን የምታዘጋጅበት ሰዐት አሁን እንደሆነ! ስለዚህም ፦ ቤተ ክርስቲያን ሆይ!
-      ሙሽራሽ “ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንዲያጐናጽፍሽ” (ራዕ.19፥7) በንስሐ ቤትሽን ተመልክተሽ አጽጂው!
-      መከራውና ሥቃዩ እነሆ በደጅ ነውና ሙሽራይቱ ሆይ! “ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበይ እንጂ የሠራሽው እንዳይጠፋብሽ ለራስሽ በመጠንቀቅ” (2ዮሐ.8) በምድር ላይ በታማኝነት ለልጆችሽ የጠራውን የወንጌል እውነት አስጨብጪ፡፡
    መከራው ካልቀረልን ለሙሉ ደመወዝ (ማር.10፥29 ፤ 2ዮሐ.8)፣ ከምድራዊ ብዕልና ሀብት ይልቅ ለወንጌል እውነት እንድናደላ (ዕብ.11፥26) በምክር ቃል ልንጸና ፤ ልናጽናና ይገባናል፡፡ መከራው ሲመጣ ብቻ መጮኹ ፣ ማዘኑ ፣ ማልቀሱ ፣ ጉባኤ መጥራቱ … መፍትሔ አይደለም ፤ መከራውን በመታገስ (ሮሜ.12፥12) ፤ በቅድስና (1ጴጥ.2፥20) ፣ ባለማጉረምረም በደስታ ፤ ደስ እያለን እንድንቀበል (ማቴ.5፥12) መትጋት ፤ መሥራት ይገባናል፡፡

    ክርስቲያን የሚለው ስማችን ይህን ያህል የጠላትን ልብ ካሸበረ፥ ወንጌላችን ገና ምድርን እንዲከድን ኪዳን አለንና ደስ ይበለን፡፡ አሜን፡፡

2 comments:


  1. ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።

    ትንቢተ ሶፎንያስ
    ◈ 2፥12 እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ።
    ◈ 3፥10 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል።
    ትንቢተ ዕንባቆም
    ◈ 3፥7 የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ።
    ትንቢተ ሕዝቅኤል
    ◈ 29፥10 ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ።
    ◈ 30፥4 ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል።
    ◈ 30፥5 ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
    ትንቢተ ኢሳያስ
    ◈ 20፥4 እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጕስቍልና ይነዳቸዋል።
    ◈ 20፥5 እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል
    መዝሙረ ዳዊት
    ◈ 68፥31 መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
    ◈ 72፥9 በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።
    ◈ 74፥14 አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።

    ReplyDelete