Sunday, 1 February 2015

ከነቢዩ የተሻሉት አህዛብና ግዕዛን


                                 PLease read in PDF

     ትንቢተ ዮናስን ስናጠና የእግዚአብሔር አስተማሪነትና ታጋሽነትን በእውነት ልብ የሚነካ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚንቀው አንዳች ሥነ ፍጥረት እንደሌለ ስናይ ደግሞ የዮናስን መጽሐፍ ይበልጥ ደጋግመን ባለመሰልቸት በትኩረት እንድናየው ያደርገናል፡፡ ምንም እንኳ አህዛብ ቢሆኑም እግዚአብሔር የታላቂቱን ከተማ የነነዌን ክፋት ወደፊቱ መውጣቱ ባየ ጊዜ ከፍርድና ከቁጣ ይልቅ ይመለሱ እንደሁ በማለት የንስሐ ዕድል ሊሰጥ ነቢዩ ዮናስን ወደነነዌ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።” አለው፡፡(ዮና.1፥2)
   እግዚአብሔር ሳያስተምር ፣ ሳይመክር ፣ ሳይዘክር ፣ ሳይገስጽ ፣ ሳያስጠነቅቅ … ለፍርድ አይቸኩልም፡፡ እግዚአብሔር የኃጢአታችን ብዛት አያስጨንቀውም ፤ የትኛውም የኃጢአት ብዛት ትንሹን የእርሱን ምህረት እንደማይበልጥ ያውቀዋልና፡፡ ስለዚህ ነነዌን በፍርድ ከማስተማር በፍቅር ሊያስተምር ታላቁን ነቢይ ላከላት፡፡ ሥልጣን ከኃይል እንዲበልጥ በፍቅር ማስተማርም በፍርድና በተግሳጽ ከማስተማር እጅጉን ይበልጣል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ነነዌን ማስተማር የፈለገው በምህረትና በፍቅር ነው ፤ ዮናስ ግን እግዚአብሔር ከተማይቱን በፍርድና በቁጣ እንዲያስተምር እንጂ በፍቅር ከማስተማርና “ንስሐ ግቡ” ከሚለው ጀምር መባሉን አልወደደውም፡፡ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ፊት መሸሽን እንደመፍትሔ በመቁጠር የዚያን ጊዜ የአለም ዳርቻ ናት ተብላ ወደምትታመነው ከነነዌ ማዶ ሊሄድ ተነሳ፡፡ ዳዊት “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? … ”(መዝ.138፥7) ያለውን ዘንግቶት ነበር፡፡

    ሰው ከእግዚአብሔር ቃል ፈቀቅ ሲል በራሱ ጥበብ ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ከእግዚአብሔር የተለየ ሰው ደግሞ ለሚያደርገው ነገር ሚዛኑ ቅዱስ ቃሉ ሳይሆን የራሱ ህሊና ነውና “መንገዱ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች” ነገር ግን “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳ.16፥25 ፤ 21፥2)
  እግዚአብሔር ላለው ለሁሉም ነገር አለመታዘዝ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ፤ ሰው ጤናው የሚታወከው ፤ የሚኖርባት ምድር የምትጎሳቆለው ፤ የትዳሩ ጎጆ ወደመፍረስ የሚያዘመው ፤ በነፍስ ክሳት በመንፈሱ አለማረፍ የሚሆንበት “የሚረባውንና የሚጠቅመውን ለማስተማር የሚተጋለትን ታዳጊ” (ኢሳ.48፥17) ለመስማት ጆሮውን ሲያክ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪ የእኛ መልካምነት ዘፈንና መጠጥ ፣ ዝሙትና ሴሰኝነት ፣ ማባከንና ክስረት … ብቻ ነው፡፡
   ዮናስ የስደት ጉዞ ወደተርሴስ ሲጀምር ከመርከቡ የውስጠኛው ውስጥ ክፍል ውስጥ ገብቶ በመተኛት ላይ ነበር፡፡ “ … ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር።” እንዲል፡፡ (ዮና.1፥5)
   ነቢዩ ተኝቷል ፤ እግዚአብሔር ግን ነቢዩን ለማስተማር ፦
1.     የምሥራቅ ነፋስን አዘዘ ፦ መርከቢቱን እየረዳ ወደምትፈልገው አቅጣጫ ይዟት ይሄድ የነበረው “ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም …” (መዝ.148፥8) የአምላኩን ቃል በመስማት ታዘዘና መጣ፡፡ (ዮና.1፥4) ዮናስ ግን ባለመስማት ተኝቶ ነበር፡፡
2.    ማዕበል ታዘዘ ፦ ነፋሱ ውኃውን ከሥፍራው ባንቀሳቀሰ ጊዜ ፤ መርከቢቱ በውኃው ላይ ጸንታ እንዳትሄድ ማዕበል ተነሳ፡፡ ታላቁ ማዕበል በተነሳ ጊዜ መርከቢቱ ልትሰበር ቀረበች፡፡ እግዚአብሔር ብርቱዎችን ነቢያትና መምህራን በልዩ ልዩ መንገድ ወቅሷል፤ ገስጿል፡፡ በለአምን በአህያ አንደበት (ዘኊ.22፥28) ፣ የአይሁድ መምህራንን በህጻናት አንደበት (ሉቃ.19፥39) … እንደገሰጸ ዮናስንም እንዲሁ ነገረው ፤ ግን አላስተዋለም፡፡
3.    አህዛብ ቀሰቀሱት ፦ ዮናስ ባለመታዘዙ ለሌሎች የጭንቀትና የሠላም ማጣት ምክንያት “ሐዋርያ ወይም ነቢይ” ሆነ፡፡ ዮናስ ባይኖር በሠላም ይጓዙ የነበሩ አህዛብ መንገደኞች አሁን ተላላው ነቢይ ከእነርሱ ጋር በመኖሩ ምክንያት ማዕበል የሚያማታቸው ሆኑ፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ኃጢአት ሲሠራ የሚታወከው እርሱ ብቻ አይደለም ፤ በዙርያውም ያሉት ጭምር እንጂ፡፡ አዳም በመበደሉ ምክንያት ምድር እንደተረገመች ዛሬ የምናየው የመከፋፋት ፣ የመጨካከን ፣ የመነዋወር ፣ የመገዳደል ፣ የመጠፋፋት … ምንጭ ሁሉ የእኛ የክርስቲያኖች ኃጢአተኝነትና ንስሐ አለመግባት ነው፡፡ ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡
የሚያሳዝነው እግዚአብሔር አሳልፎ ሲሰጠን ነውራችን በዙርያችን ብቻ ሳይሆን በአህዛብም ፊት እንኳ የተገለጠ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ዮናስ የበደለ ሰው መሆኑ በአህዛብ መንገደኞች ፊት ታወቀ፡፡  ነገር ግን እነርሱ ብዙ ቸርነት አደረጉለት፡፡ ነቢይ ዮናስ ተኝቶ እነርሱ ጸለዩ፣ ነቢይ ዮናስ በድፍን ነነዌ ላይ መዓትን ተመኘ ፣ እነርሱ ግን አንድ እርሱን ላለማጥፋት ተጠነቀቁ ፤ አዘኑለት ፣ ነቢይ ዮናስ ነነዌ ብትጠፋ ምን ሊሆን ይችላል? አላለም ፣ እነርሱ ግን “አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን” ብለው ለመኑ፡፡ (ዮና.1፥14) ግና የእግዚአብሔር ፍርድ ይታወቅ ዘንድ ወደባህሩ ጣሉት፡፡ (ዮና.2፥3) ዮናስ ይህን አምኖ ተናዘዘ፡፡
  አገልጋይ መሆን ዕዳ እንጂ መብት አይደለም፡፡ ለብዙዎች በእረኝት መንፈስ እንድንጨነቅና እንድንራራ እንጂ እንደምንደኛ እረኛ በመንጋው ለመፍረድ ብቻ “የተሾምን” አይደለንም፡፡  
4.    ትልቅ ዓሣ ታዘዘ ፦ እግዚአብሔር ላልታዘዘው ነቢይ እንዳይሞት ትልቅ መጋቢና ጠባቂ ዓሣን አዘጋጀለት፡፡ በዓሣው ሆድ ውስጥ ዮናስ ንስሐ ገባ፡፡ እግዚአብሔር ምህረት አብዝቶለት ፤ ደኅንንትም አድርጎለት ከዓሣው ሆድ ውስጥ ወጣ፡፡   ከዚህ በኋላ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት” የሚል ቃል በድጋሚ መጣለት፡፡ (ዮና.3፥2) ታዘዘ ፤ ነገር ግን ዮናስ በልቡ ነነዌ እንደትጠፋ ይሻ ነበር፡፡ (ዮና.4፥1-5)
5.    ቅል ታዘዘ ፦ (ዮና.4፥6) እግዚአብሔር፥ የራሱን እንጂ ቃሉንና ትዕዛዙን ለማይሰማው እልኸኛው ዮናስ መልካምነትን አበዛለት፡፡ የቅል ጥላ ሰጠው፡፡ ዮናስ በፍቅርም ፤ በተግሳጽም አልመለስም ቢልም እግዚአብሔር ግን የሚርቀውን ነቢይ አጥብቆ ፈለገው፡፡ እንዴት ያለ ፍቅር ነው! ዮናስ በጥላዋ ደስ አለው፡፡ ግን ድንገት ደረቀች ፤ ዮናስ ያልተከላትና እንድታድግ ምንም ላልደከመባት ቅል በጣም አዘነ፡፡
6.    ትል ታዘዘ ፦ (ዮና.4፥8) ዮናስ ደስ የተሰኘባትን ጥላ እግዚአብሔር ትልን አመጣና ቅሊቱን እንድትበላ አደረገ፡፡ ዮናስ በጣማ ተናደደ፡፡ ዮናስ ታይታ የምትጠፋ ቅል ለእርሱ እንደምታስፈልግ ቢያምንም ነነዌ ግን (አንድ መቶ ሐያ ሺህ ሰው ገደማ ያላት) የእግዚአብሔር የምህረቱ ጥላ እንደሚያስፈልጋት አላመነም፡፡ ዮናስ ስለቅሊቱ በትል መበላት ተናዶ ሞትን ተመኘ ፤ ስለነነዌ መጥፋት ግን ግድ አልሰጠውም፡፡
  ዛሬም አገልጋይ ተብለው ለራሳቸው ለትንሹ ነገር በመጠንቀቅ ሲኖሩ የሕዝቡ መጥፋትና አለመዳን ግድ የማይሰጣቸው ብዙ ናቸው፡፡ የተራበና የተጠማ ወገንና ሕዝብ እያዩ ብራቸውን በባንክ አስቀምጠው ወለድ የሚበሉ አገልጋዮችንና አብያተ ክርስቲያናትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ሕዝባቸውን በሞትና በዕርዛት እየፈጁ ለራሳቸው ግን ሕንጻ የሚገጠግጡ ቡችሎቻቸውን በገበታ የሚመግቡ ባዕለሥልጣናትና ባዕለጠጎችም የዚሁ ተመሳሳይ መልክ ናቸው፡፡
7.    ፀሐይ ታዘዘች ፦ (4፥8) ቅሊቱ በትል ከተበላች በኋላ ጌታ እግዚአብሔር የሚያቃጥል ፀሐይ አመጣ፡፡ የዮናስንም ራስ አቃጠለችው፡፡ ዮናስ ይበልጥ እስከሞት ተበሳጭቶ ተቆጣ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለምን ይሆናል? ብሎ ዮናስ አላስተዋለም ፤ አልጠየቀምም፡፡

 አህዛብም ፤ ግዕዛንም ከነቢዩ ተሽለው ነቢዩን ወደንስሐ በመጥራት ቢጋብዙትም ዮናስ ግን እስከአሁን ከቁጣው አልበረደም፡፡ ዮናስ ለሞትና ለፍርድ በስልቹነት መንፈስ ይቆጣል ፤ እግዚአብሔር ግን እስከመጨረሻዋ ሰዓት ስለበጐነቱና ምህረቱ ፤ ስለተትረፈረፈው ቸርነቱ ይናገራል፡፡ አገልጋይ “በተሾመበት” ባይቀመጥ እግዚአብሔር ግን ግራና ቀኙን ለማይለይ ሕዝቡ የቸርነት ሥራውን ከመሥራት አልተቆጠበም፡፡ እኛም እንደየሚበዙት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና መሪዎች ሳይሆን እንደትልቁ ጌታ ቸርነት ዛሬንም ፤ አሁንንም አለን፡፡ ተመስገን ፡፡ አሜን፡፡    

No comments:

Post a Comment