Friday 20 February 2015

ይድረስ ለአይ ኤስ አይ ኤስና መሰል ባልንጀሮቻችሁ!




                                        
                                            Please read in PDF


   ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በአንድ የቲያትር ድርሰታቸው ላይ እንዲህ ማለታቸው ይታወሰኛል፦ (በትክክል ካላልኩት ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡)
“አንቺ ወንጌል አጋዳይ
             እኔን ይዘሽ ወደሰማይ ወደሰማይ”
ብላቴን በቲያትር ድርሰታቸው ውስጥ “ወንጌል የምትባል ሚስት አግብተው የደረሰባቸውንና ያገኛቸውን መከራ በቅኔ” ሲያወጉ ይታያል፡፡ ወንጌል ከሥጋ ከደም ጋር ያይደለ፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊው ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነውና የምትጋደለው (ኤፌ.6፥12) የክፋት ሠራዊት አጋንንት የሁል ጊዜ ጠላቶቿ ናቸው፡፡ ወንጌል ከአጋንንት ጋር ዘወትር ተጋዳይ ናት ማለት ነው፡፡

    ስለዚህም ወንጌል ብዙዎችን “ትገፋለች ፥ የሚገፏት ደግሞ በኃይል ይናጠቋታል” (ማቴ.11፥12) ማለትም ኃጢአተኞችና ያልተጠበቁ ሰዎች ወደእግዚአብሔር መንግሥት በመግባት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ ፤ ይህ ብቻ ግን አይደለም “ተናጥቀው የሚያገኟት ብርቱዎች ናቸውና” ብርቱ መከራ ፤ የማያቋርጥ ስደት ፤ ሞት ፤ ከፍ ያለ ሥቃይ ቢገጥማቸው ጽኑና ቆራጥ መንፈሳውያን ስለሆኑ አንዳች አይፈሩም ፤ ብርቱዎች ናቸውና፡፡
     በእርግጥም በስሙ ብቻ ልናምን አልጠራንም ፤ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናልምና” (ሐዋ.14፥22)፡፡ የመከራው አይነት ብዙና የማይቆጠር ነው፡፡ አንዳንዴ ከአህዛብ ፥ ብዙ ጊዜ ግን ከገዛ ወገኖቻችን እንቀበላለን፡፡ ከዘመነ ሰማዕታትና ከተወሰነው ጊዜ በቀር ቤተ ክርስቲያን መከራን የተቀበለችው ከገዛ ወገኗ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስንም የተሰሎንቄ አማኞችንም ያሳደዱትና መከራ ያጸኑባቸው የገዛ ወገኖቻቸው ናቸው፡፡ (1ተሰ.2፥15)
    እናንት! የአይ ኤስ አይ ኤስ መሪዎችና አባላት! በግብጻውያን ወንድሞቻችን ላይ ያደረጋችሁት ነገር ምንም የሚደነቅና የሚያስደነግጥ አይደለም ፤ (1ጴጥ.4፥12) ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን ሙሽራ ክርስቶስ ኢየሱስ “በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን እንደተቀበለ … እኛም እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ መከራን ለመቀበል እንወጣ ዘንድ ይገባናልና፡፡” (ዕብ.13፥13) የዚያኔ መልዕክቱ የተጻፈላቸው ዕብራውያን ከአይሁድነት ፊታቸውን ወደክርስቶስ ዘወር እንዲያደርጉ የፍቅር ጥሪ ቀርቦላቸዋል ፤ ከይሁዲነት ወደክርስቶስ ፊትን መመለስ በዚያ ዘመን ከፍ ያለ ውርደትን ያስከትላል፡፡ ግን ሊሆን ግድ ነበር፡፡ የምትመጣዋን ከተማና የሚመጣውን ጌታ ተስፋ እንደርጋለንና የእናንተ (በእናንተ የሚሠሩ አጋንንት) ተቃውሞ ያዘገየናል (1ተሰ.2፥18) እንጂ ፈጽሞ የወንጌል ሥራችንን አያቋርጠውም፡፡

   ወንጌል አጋዳይ ፣ እጅግ መከራ የበዛባት መሆኗንና ፤ ስለወንጌል በምንወዳቸው መካከል የተጠላን ፣ የተናቅን ፣ ከመቅደሳቸው ገፍትረው እንደሚያስወጡን ፣ ያለስማችን ስም እንደሚሰጡን ፣ ከፍ ሲል ደግሞ እንደእናንተ ደማችንን እንደሚያፈሱት …  የምንወደው ጌታችን አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ማቴ.24፥25 ፤ ዮሐ.16፥33) ምንም እንደ“ሸክላ ዕቃ” ተሰባሪ በሆነው ሰውነታችን ስለወንጌል መከራንና ስደትና በመቀበል ክርስቶስን ብንመስለውም (2ቆሮ.1፥5 ፤ ሮሜ.8፥17 ፤ ፊሊጵ.3፥10) እውነት ለመናገር፦ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም ፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም ፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።” (2ቆሮ.4፥8-11)
    ይህ ግብጻውያን ወንድሞቻችንን ለምታሳድዱና እዚህ አገር ቤትም ሆነው ወንጌሉንና ክርስቶስን ለምትገፉ ለእናንተ በዓይናችሁ ፊት ቢታይም፥ እንዳላየ ሆናችሁ እንደምትቃወሙ እናውቃለን፡፡ ለእኛ ግን የእናንተ መግደል ሕይወት ፣ ስድባችሁ ክብር ፣ ነቀፌታችሁ ሞገስ ፣ አሽሙራችሁ ሽልማታችን ፣ ዛቻችሁ ድፍረት ፣ ማስፈራራታችሁ ብርታት ፣ ስም ማጥፋታችሁ የማስታወቂያ ሰሌዳችን ሆኖልን ይኸው አለን!!! ክብር ለሞተልንና ላዳነን ጌታ ፤ ጌታ ኢየሱስ ይሁን ፡፡ አሜን፡፡
   አይ ኤስ አይ ኤስና ወንጌል ለአህዛብና ላላመኑ ሁሉ እንዳይደርስ በኃይል የምትቃወሙ ሁሉ ሆይ! እንኳን እናንተ … በብዙ ሺህ ጦር የታጠቁና በብዙ ወታደር ይንቀሳቀሱ የነበሩት ሮማውያኑ ነገሥታት ኔሮን ፣ ድምጥያኖስ ፣ ትራጃን ፣ ሐድዌን ፣ አንቶንዮስ ፓየስ ፣ ማርቆስ አውሬሊያኖስ ፣ ዲዮቅልጥያኖስና ሌሎች ብዙዎች በሥጋችን ላይ ጥቂት መከራ አደረሱብን እንጂ አንዳች ሊያደርጉን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ከጥንት የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታችን “ቤተ ክርስቲያኔን፥ … የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” (ማቴ.16፥18) በሚል ዘላለማዊ ኪዳኑ ይጠብቃታልና ፈጽሞ አልቻሉአትም ፤ እናንተም አትችሉአትም፡፡
   ወንጌል በሰበክን ቁጥር የገዛ ወዳጆቻችን ጠላት እንደሚሆኑብን በይሁዳ ፣ በዴማስ ፣ በአርዮስ አይተናል፡፡ የዛሬዎቹ ይሁዳውያን ፣ ዴማሳውያን ፣ አርዮሳውያን ፍጹም አያስፈሩንም፡፡  የወንጌል ተቃዋሚዎች አይኖቻቸው እያየ ምርኮ ለአምላካችን መንግሥት እየበዛ ነውና ፤ ይህን የነፍሳት ወደክርስቶስ መንግሥት መፍለስ ያየ ሰይጣን በመግደልና በማሳደድ ይህን ቁጥርና ጉዞ ለመግታት ቢያስብም ከእርሱ እስርና መግደል በኋላ፥ ገዳዩ ሞቶ  “የእግዚአብሔር ቃል ግን ማደጉንና መብዛቱን የሚያቆመው እንደሌለ አንዳች አንጠራጠርም፡፡”(ሐዋ.12፥24)
     እንኪያስ! መሰደድ ፣ መናቅ ፣ መገፋት ፣ ከመቅደስና ከምኩራብ መባረር ፣ መገደል … ለእኛ ወግና ማዕረጋችን እንጂ ውርደታችን አይደለምና ከቶም አናዝንም ፤ ለእናንተና ለባልንጀሮቻችሁ ግን ወደልባችሁ ዘወር ትሉ ፤ የሞተላችሁንም ጌታ በማየት ንስሐ በመግባት ትመለሱና ትድኑም ዘንድ  በትልቅ ንስሐና እንባ እናለቅሳለን እንጂ ሥጋቸውን ለገደላችኋቸው ግብጻውያንና ኢራቃውያን እንዲሁም በሌሎች አገር ላሉ ወንድሞቻችን ቅንጣት ታህል አንከፋም ፤ ፊታችንም አይጠቁርም፡፡ እርሱ ጌታችን በሕይወታችን ብቻ ሳለን የሚከብርብን ሳይሆን በሞታችንም ነውና በሞቱትና በመከራ ላይ ባሉ ወንድሞቻችን ደስ አይበላችሁ፡፡ አሜን፡፡
   አሳዳጆቻችን ፣ ወደረኞቻችን ፣ ስም አጥፊዎቻችን ፣ ተሳዳቢዎቻችን ፣ ይህን ሁሉ ሲያደርጉብን ወደተዘጋጀልን የዘላለም ክብርና የአክሊል ሽልማት እያቻኮሉና እየገፉን እንደሆነ ነው፡፡ በእርግጥም አላስተዋሉም ፤ የእነርሱ መግፋት እኛን ወደተገፋው ነገር ግን ሞትን ድል አድርጎ ወደተነሳው የትንሳኤ በኩርም ወደሆነው ወደኢየሱስ ክርስቶስ እየገፉን እንደሆነ በፍጹም አላስተዋሉም፡፡ ይልቁን ደግሞ የሰማዕታትንና የእግዚአብሔርን ቅዱሳን አንገት የሚቆርጡ እጆች ይዝላሉ ፣ የሚሳደቡ አፎችና የስድብን ነገር የሚጽፉ እጆችም ፍጹም ይደክማሉ ፣ የአሳዳጆችና የስም አጥፊዎችም ጉልበት እንደሰም ይቀልጣል ፣ ጥላቻችሁም ልባችሁን ያደክም እንደሆን እንጂ እኛን ፈጽሞ አይነካንም ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ግን በብዙ ጥላቻ ፣ በእልፍ አሽሙረኞች ፣ በአዕላፍ አሳዳጆች ፣ በአዕላፋት ገዳዮችና ደብዳቢዎች ፣  በትዕልፊት ተቃዋሚዎች ፣ በምዕልፊት አራጆች ፤ አሰቃዮች ፊት … አይኖቻቸው እያየ ምድርን ሁሉ ይወርሳል ፤ እመኑ! ተቃማዊ ሁሉ አቅሙ ዝሎ “ማንም ሳይከለክለን የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክን ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጠን እናስተምራለን።” (ሐዋ.28፥31) አይ ኤስ አይ ኤስና ባልንጀሮቻቸው ሆይ! ሳታውቁ ክርስቲያኖችን ያጠፋችሁ ወይም ቁጥራቸውን የቀነሳችሁ መስሏችሁ በማረድ ፣ በማሳደድ ፣ በማንገላታት ፣ በስም ማጥፋት ፣ በጥላቻ የአምላካችንን ወንጌል ስለሰበካችሁ በዚህ እጅግ ደስ ብሎናል!!! (ፊልጵ.1፥15-18)
    ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ይሆንና ይመጣ ዘንድ ግድ ያለውን መከራ በስምህ የተጠራ ሕዝብ ፤ በስምህ መከራ ስላገኘው እናመሰግንሐለን፡፡ አሜን፡፡

2 comments:

  1. tebarek chemero chemero yibarkehe

    ReplyDelete
  2. ክርስቲያን መሞት ሳይሆን መግደል ነዉ ሚፈራው። ቤታችን በሰማይ ነው። ክሪስትያን እየገደለ ሳይሆን እየሞተ ሚያሸንፍ ነው። እግዚአብሔር ኢትዮጲያን ይባርካት።

    ReplyDelete