Saturday 14 February 2015

ለአዋጁ ጾም አዋጅ ይታወጅ!

                               
                       Please read in PDF

    ከፊታችን ሳምንት ጀምሮ ላሉት ተከታታይ ሳምንታት “ሁሉም ምዕመን የሚጾመውና” በቤተ ክርስቲያናችን ታላላቅ ከሚባሉ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነው ጾም ፤ ጾመ ሁዳዴ ወይም ዓቢይ ጾም ወይም የጌታ ጾም የሚባለው ነው፡፡ ጌታ ጾምን በጾመበት ወራት ዲያብሎስ በስስት ፣ በትዕቢትና ገንዘብን በመውደድ ኃጢአት በግልጥ ፈትኖታል፡፡(ማቴ.4፥1-11) ንጹሐ ባህርይ መድኃኒት ክርስቶስ ደግሞ ዲያብሎስን ድል አድርጎታል፡፡ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነም ነውና ከዚህ የተነሳ በድካማችን ሊራራልን የሚችል ሊቀ ካህናት ሆኖልናል።” (ዕብ.4፥15)

    ጌታ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን መስሎናል ፤ ስለዚህም ክርስቶስ ጌታችን በነገር ሁሉ እርሱን ትመስለው ዘንድ “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ፡፡ (ኤፌ.5፥27) ከጥንት ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ሃሳብ “በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።” እንዲል (ኤፌ.1፥4) አብረነው እንኖር ዘንድ ነው፡፡ (ዮሐ.17፥24)
  እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የእርሱን የጽድቅ ኑሮ ትኖር ዘንድ በፍቅር ጥሪ አብዝቶ ጠርቷታል፡፡ ጌታ እንድንኖረው ከሚሻው የጽድቅ ኑሮ አንዱ የጾም ሕይወትን ነው፡፡ ጌታችን ወደሰማያት ካረገ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ልትጾም እንደሚገባት “ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።” በማለት ተናግሯል፡፡ (ማቴ.9፥15) ጌታ ወደሰማያት ከሄደ እነሆ ሁለት ሺህ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ስለዚህ ሙሽራው ኢየሱስ ከሚዜዎቹና ከሙሽሪት ጋር እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ በአካል ተለያይቷልና የጾሙ ወራት አሁን ነው ማለት ነው፡፡
   በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የመጾማችን ዋናውና አንዱ ምክንያት የሄደው ሙሽራ ዳግመኛ እንዲመጣ ለመጠባበቅና በመሄዱም ስለማዘናችን ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ናፍቆትና ተስፋ የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣትን መጠባበቅ ነው፡፡ (ዮሐ.14፥3 ፤ ቲቶ.2፥13 ፤ ራዕ.22፥17) ምክንያቱም ተስፋዋ የሆነው የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት የቤተ ክርስቲያን ትልቅ የመጽናናት ጉልበትዋ ነውና፡፡ (1ተሰ.4፥13-18)
  በሁለተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን ለምን ትጾማለች? ብንል በውስጥዋ (በመካከልዋ)  ስላለው ፣ ስለህዝብና ስለዓለም ርኩሰትና በደል ሁሉ በመጸጸት ለማልቀስ ልትጾም ይገባታል፡፡ (ነህ.9፥1) ዕዝራ የሕጉን መጽሐፍ ለህዝቡ ሁሉ ባነበበ ጊዜ ሕዝቡ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ዝም አላለም ፤  ይልቁን “የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ። የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ።” (ነህ.9፥1-2) ይለናል፡፡
  በእርግጥ ሕዝብ በትክክል ወደእግዚአብሔር እንዲመለስ ከተፈለገ ዕዝራ እንዳደረገው ቀድሞ የሕጉን መጽሐፍ  ወደሕዝብ ልብ ማድረስ እንጂ ሌላ ነገር አያስፈልግም ፤ ዛሬም ቢሆን እውነተኛ የሆነ ንስሐና የተለወጠ ጾምን ማየት የምንችለው ወንጌሉ በትክክል ሥፍራውን መያዝ ሲችል ብቻ ነው፡፡ አልያ ጾም ልማድ ፤ ሥርዓትና ወግ ሆኖ ድስትና ጭልፋ ማጥራት እንጂ ቤተ ክርስቲያን የምትተጋለትን ያንን እውነተኛና የማይቀረውን ዳግም ምጽአቱን የምትናፍቅበትና የህዝቡን ኃጢአት ለእግዚአብሔር የምትናዘዝበት አይሆንም፡፡
  ዓቢይ ጾም የአዋጅ ጾም ነው ፤ የአዋጅ ጾም ደግሞ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ሁሉ የሚሳተፍበት ነው ማለት ነው ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ሁለት ነገር እጅግ በጣም በግዴታ መከናወንና መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከጾሙ በፊት ንስሐና ይቅርታ እንዲሁም የምንጾምበት አላማ ምክንያቱ በትክክል መታወቅ አለበት፡፡   የትኛውም መንፈሳዊ ነገር ከመደረጉ በፊት ዕርቅና ስምም ይፈልጋል፡፡ (ማቴ.5፥24) ለዕርቅ ደግሞ ንስሐ ቀዳሚ ነው፡፡ እንኪያ ከጾሙ በፊትም ሆነ በኋላ በእርቅ ለመኖር ወስነናል? እስኪ እኒህን ነገሮች እናስብ?
       ሁለቱ ሲኖዶሶች(የአሜሪካና የኢትዮጲያ) መቼ ነው የሚታረቁት? ለመሆኑ ወንድምን ሳይወዱ እግዚአብሔርን መውደድ ይቻላል? (1ዮሐ.3፥15 ፤ 17) መቼ ነው ጳጳሳቶቻችን እንደእግዚአብሔር ልጆች ይቅር መባባልና እውነተኛ ጾም መጾም የሚቻላቸው? መቼ ነው በጾማቸው እግዚአብሔርን የሚያከብሩት? (ሉቃ.2፥37 ፤ ሐዋ.13፥2)
       በሁለቱ ወንድማማችና እህትማማች በኢትዮጲያና በኤርትራ መካከል ስለፈሰሰው ደም መቼ ነው በጾምና በዋይታ ንስሐ በመግባት ይቅርታ የምንለምነው?
       እንደነሐና ላላንጎና ሌሎች ወገኖቻችን ላይ ስለተፈጸመው ነውርና ኃጢአት ንስሐ የምንገባው መቼ ነው?
       ግብረ ሰዶማውያን ፤ አመንዝራ አገልጋዮችና አጃቢዎቻቸው በመካከላችን  እንዲህ እየፋነኑ ቤተ ክርስቲያን በእንባና በጾም የማታለቅሰው ስለምን ነው? …
  እንግዲህ ለአዋጁ ጾማችን ማነው ለምን እንደምንጾም ዓላማውንና ርዕሱን ሊነግረን የሚቻለው? መጾሙን እንጾማለን ግን አላማው ምንድር ነው? ምን ለማብዛት ምን ለማጥፋት ነው? በውኑ ይህ ሕዝብ አልተቸገረምን? ረሃብና እርዛት ዛሬስ ምልክቱ አይደልምን? ፍትሕ ማጣት አላበሳጨውምን? ግብር ሰብሳቢው አልበዘበዘውምን? ወታደሩ አላስጨነቀውምን? ነጋዴው አላታለለውምን ፤ አላጭበረበረውምን? “የንስሐ አባት” ከልጁ ጋር አልተኛምን? መሪው ተመሪ አልሆነምን? … ታዲያ መንፈሳዊ ፍሬ ያለው ጾም ለመጾም ስለምን ለእግዚአብሔር አንታዘዝም?
  በአጭር ቃል ፦
       ማን ነው የጾማችን ርዕስ ምን እንደሆነ የሚነግረን? ሲኖዶሳውያን ሆይ! ወዴት “ናችሁ”?
       ከጾም በፊት እውነተኛውን የክርስቶስን ወንጌል ሰብኮ ፤ የሕዝቡን ልብ አለዝቦ ታረቁ ባይስ ማን ነው? …
      ይህንን የመንፈሴ አይኖች ይናፍቃሉ፡፡ መቼ ይሆን የማየው? የአዋጁ ጾም የአዋጅ ርዕስ ያስፈልገዋልና … አዋጁን አዋጆች ወዴት ናችሁ?!
      አቤቱ ሕዝብህን አድን ፤ ርስትህን ባርክ ፤ ቤተ ክርስቲያንህን ለንስሐና ለእውነተኛ ጾም አንቃ፡፡ አሜን፡፡


1 comment: