Wednesday, 28 January 2015

መምህር ፣ ኢንጂነር ፣ አርቲስት ፣ ዲያቆን ...


                                         Please read in PDF
   
    መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና ጸጋ ልዩ ልዩ እንደሆነ ፤ ነገር ግን መጋረጃን እንደሚያያይዘው ኩላብ የተያያዙና አንድን አካል እንደመሥራት ያሉ እንደሆኑ እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ጸጋዎችን ለቤተ ክርስቲያን አማኞች የሚሰጠው የጸጋ ድኃ እንደሌለና የቤተ ክርስቲያንን ምልአት ለማሳየት ነው፡፡ በጸጋ ትምህርት ትንሽ የሚባል ጸጋ ከሌለ ሁሉም እኩል ሊከበሩና አገባብ ያለው ሥፍራ ፤ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በጳጳስነት ጸጋ እንደ ኤፌሶን ሽማግሌዎች የሚመራ አማኝ ፥(ሐዋ.20፥28) የእርሱ ጸጋ ቃሉን እንደልድያ በመስማት ልቡ ከተከፈተለት ሰው ጋር (ሐዋ.16፥14)  ምንም የጸጋ ልዩነት የለውም፡፡

   አንድ ሰው ሁሉንም ጸጋ (እንደአምባገነን  መሪዎች ጠቅልሎ) ሲይዝ እንደብቁ አማኝና አገልጋይ ከመቆጠር አልፎ ፥ ብዙ “ምስጋናና አድናቆት የሚጎርፍለት”፤ አንድ ጸጋ ብቻ አለው የሚባለው ደግሞ ከአገልጋይነትና ከአማኝነት ዝቅ ተደርጎ ቦታ የሚነፈግበት ዘመን ይህ የእኛ ዘመን ነው ብል ማጋነን አይኖርበትም፡፡ ለዚህም ይመስላል በየአውደ ምህረቱ ወንድም ወይም ዲያቆን ወይም ቄስ ወይም ዘማሪ/ዘማርያን መባል አልበቃ ብሏቸው ዝቅ ብለው በባዶ መንፈስ በትህትና ሊያገለግሉት በሚገባ በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት “በዓለማውያን መድረክ ላይ በሚጠሩበት ማዕረግ” ካልተጠሩ የሚያኮርፉ ፤ ሲብስ የሚከሱ የበዙት፡፡
   ስለዚህ “መምህር ፣ ኢንጅነር ፣ ዲያቆን … እገሌ ” ማለት ወይም “ ዶክተር ፣ ዘማሪ ፣ ሰባኪ ፣ ሊቀ እንትንና እንትን ... እገሌ ” ማለት እንደባክቴርያ እየተባዛች መጥታለች፡፡ አለማዊው የአስኳላ ትምህርት አያስፈልግም ከሚሉ ወገኖች አይደለሁም ፤ እጅግ በጣም ያስፈልጋል ከሚሉት ወገኖች ውስጥ ነኝ፡፡ ይሁንና የዚህን ትምህርት ማዕረግ ተሸክመን መጥተን ከተከበርንበትና ከተሠጠን ዘላለማዊ ልጅነት በላይ በማድረግ በዚያ ካልተጠራን ብለን የምናኮርፍ ፤ አቧራ እያስነሳን አምባጓሮ የምንፈጥር ከሆነ የልጅነት ትርጉሙ የተዛባብን ይመስለኛል፡፡
   በአንድ ወቅት ፈሪ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ እንደወረደ በኢየሩሳሌም አደባባይ የመጀመርያውን አለም አቀፍ የወንጌል ምስክርነት በድፍረትና በኃይል ተመልቶ መሰከረ፡፡ ምስክርነቱ ገዳዮችን ገዳይ የሚል ምንም ማሻማት የሌለበት ነበር፡፡ ስብከቱን ሰምተው ልባቸው ተነክቶ ያመኑቱ ወደሦስት ሺህ የሚጠጉት አማኞች ወደሐዋርያት መጥተው የተናገሩት ነገር ቢኖር “እናንተ ታላላቅ የጌታ ሐዋርያት ፣ ጸጋ የበዛላችሁ ፣ ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ …” የሚል ሳይሆን “ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፦ ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው።” (ሐዋ.2፥37) ነው የሚለው፡፡ ሐዋርያት ወንድሞች በመባላቸው ምንም አልከፋቸውም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎችን ወንድሞች በማለት እንጂ በሌላ ስያሜ አልጠሯቸውም፡፡ ( ሐዋ.2፥29 ፤ 3፥17 ፤ 6፥3 ፤ 13፥26 ፤ 15፥23 ፤ 32 ፤ 33 ፤ ከወንድምነት በላይ አይተው የማይገባ ክብር የሰጧቸውን ሰዎች አጽንተው ደግሞ  ተቃውመዋል፡፡(ሐዋ.10፥26 ፤ 14፥15)
    እንኪያስ ለምን ይሆን ወንድምነት እንዲህ ያነሰብን? አላስተዋልንም እንጂ ወንድምነት መቼም በማንም የማንቀማው ትልቁ ማዕረጋችን ነበር!!! ይህ ግን አለማዊነትን ከመጠማታችን የተነሳ አልታይ ያለን ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ዛሬ እንዲህ ያሉ ስያሜዎች ለመታወቅና “ትልቅ” ለመባል ካለን ምኞት ብቻ ሳይሆን ያለብንን የእግዚአብሔርን የመዳን ቃል ወንጌል አላዋቂነት ፤ የበታችነታችንን ለመደገፊያና የመንፈሳዊ ሕይወታችንን ልምሾነት መሸፈኛነትም ስለምንጠቀምበት ነው፡፡ እንጂማ የጌታ ሐዋርያት የተጠሩበት “ወንድሞች” የሚለው ስያሜ ከምንደርተው ድሪት ይልቅ መተካከያ የሌለው ውድ ስም ነበር፡፡
   በሌላ በኩል በመንፈስ ድሆች መሆንን መጥላታችንን በሚገባ ያሳብቅብናል፡፡ በብዙ ማዕረጋት ተጠርተን ለአንዱም ወገን በሕይወት መድረስ ሳይሆንልን ጠላት መሳለቂያ ያደረገን ጥቂት አይደለንም፡፡ “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብጹዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ.5፥3) የተባሉት ከራስ መተማመንና ብቃት ይልቅ በተቃራኒው ራሳቸውን በዓለም ካለው መንገድና እሴት ከመመራት ራሳቸውን በማራቅ የሚኖሩ ፥ እንዲሁም የተገባቸውን አድርገው ራሳቸውን በመሰወር የሚገባንን አደረግን እንጂ የማንጠቅም ባርያዎች ነን የሚሉትን ነው፡፡
  በመንፈስ ድሆች እንደሆኑ የሚያስቡ አገልጋዮች ራሳቸውን እንደደካማ ይቁጠሩ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ፣ ኃይልና ጉልበት ታምነው የሚገባቸውን እንደሚያደርጉ ያምናሉ፡፡ የግል እሴታቸውን ግን ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጋር አይቀላቅሉትም፡፡ ይህ ማለት የአቴናን አለማዊ የፍልስፍና ጥበብ ከኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ነገረ መለኰት ጋር በመደባለቅ አይፈተፈትም፡፡ አሁንም በሌላ በግልጥ ንግግር በዓለማዊነት ጥበብና ልምምድ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ማገልገል አይቻልም፡፡
   አገልጋይ ወንድሞች መካከል ማገልገላችን ነውርም ፤ ዕፍረትና የበታችነትም አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን ጸጋ አበላልጠን ትልቅና ትንሽ ማለታችነት ዲያቆን በጳጳስ ፊት በዕፍረትና በበታችነት ፤ ጳጳስ በዲያቆናት መካከል አለፍርሃት በድፍረትና ባለማፈር እንዲሁም ደግሞ አንድ ምዕመን ፈጽሞ ክህነት ባላቸው ፊት ማስተማር ፣ መምከር ፣ መገሰጽ … እንዲህ ያለ አገልግሎት እንዳያገለግል ከባድ ግንብ ሠርተናል፡፡ ስለዚህ የተሻለው አማራጭ መንገድ ይህኛው ስለመሰለን አለማዊውን “ማዕረገ ክህነት” ለዚህኛውም ቤት እንደቅጥያ መጠቀምን ወደድን፡፡ ግና ባለመደማመጥ ወደሚብስ የልዩነት ጎራ እንጂ ወደአንድነት አልመጣንም፡፡
   በዓለማውያን ቢሮዎች ውስጥ “እኔ ትልቅ የትምህርት ደረጃ አለኝና ትልቁ ሥፍራ ለእኔ ይገባል” የሚለው መበላላትና ክርክር ነገ ደግሞ በግልጥ አይኑን አፍጥጦ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል “በነኢንጅነር ፣ መምህር ፣ ዶክተር ፣ ዲያቆን እገሌ ወይም ቄስ እገሌ” በኩል እንዳይመጣ በመንፈስ ድሆች የሆኑ አገልጋዮችን ጌታ ለመከሩ እንዲያበዛልን በትጋት መለመኑን ልንዘነጋ አይገባንም፡፡ አንድ አስተማሪ ምሳሌ ላንሳ፦ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበረ አንድ ወንድም የማስተርስ ትምህርት ዕድል አጊኝቶ ወደውጪ በመሄድ ሲጨርስ ተመልሶ ይመጣል፡፡ እርሱ ተመርቆ እንደመጣ ዝግጅት አዘጋጅተው እርሱን በትምህርት ደረጃ የሚደርስበት እንደሌለው በመናገር ሥልጣኑን መረከብ እንዳለበት በተናገሩት ጊዜ አሁኑኑ የማስተርሱን ወረቀት እንደሚቀደውና ፈጽሞ ወንድሙ እየመራ ባለበት ሁኔታ እርሱ ሊሾም እንደማይገባ አጽንቶ ተናገረ፡፡ በዚህም ምክንያት “ባለማስተርሱ” ወንድም ዛሬም በቅን ልብ በወንድሙ ሲገልግል አለ፡፡

   ጌታ ሆይ በቤትህ እንዲህ ያሉ አገልጋዮችን አብዛ፡፡ አሜን፡፡

2 comments:

  1. ena ante lemen diacon tebalk

    ReplyDelete
  2. ድሮ በሰንበት ት/ቤት ስታስተምረን በእውነቱ እንዴት አይነት ልጅ መጣ ብለን ብዙዎቻችን ተገርመን ነበር። ግን ዛሬ ላይ መጀመርያህን ሳይሆን አሁን የቆምክበትን ሳይ አዘንኩ። በጣም ተስፋ ያለህ ልጅ ነበርክ። ዛሬ ግን አንዲት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ሳይሆን ቃልህ መናፍቃንን እጅግ ያስደስታል። ዛሬ ለተነሱበት የተሃድሶ አላማ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስራና አላማ አስፈጻሚ ብለው ከሚጠቅሷቸው ሰዎች ተርታ ከገባህ ቆየህ። አውቃለው ቃላቴ ላንተ ምንም እንዳልሆኑ ግን እንደው ምን ነካህ ወንድሜ
    ጌታ ማስተዋሉን ይስጥህ
    ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባህር መስጠም ይሻለው ነበር፡፡” ማቴ። ፩፰፡፮

    ReplyDelete