Saturday, 28 February 2015

የጠፉትን ለምን ነው የማንፈልገው?


           


    በኦሮምኛ አንድ የማስታውሰው ተረት አለ ፤ እንዲህ የሚል፦ “Loon bade loon jiruuf barbaadan”  ትርጉም “የጠፋ ከብት ላለው ከብት ሲባል ይፈለጋል” ፡፡ የተረቱ ጽንሰ ሐሳብ የጠፋውን ከብት የማይፈልግና ፈልጎም የማያገኝ ሰው በበረት ያለውንም ከብት ይነዱበታል ለማለት ነው፡፡ በእርግጥም የቤት እንሰሳን አጥብቆ አለመፈለግ በደህና በበረት ለሚኖረውም ምንም ዋስትና አንዳች ደኅንንት አይኖረውም፡፡

   የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮ የጠፉ በጐች መፈለግ ነው ፤ ምክንያቱም  የበግ ዋና ባህርይው ከእረኛው በተለየ ጊዜ ብዙም ሳይርቅ የሚጠፋና የሚቅበዘበዝ መሆኑን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህን ሐሳብ በሚገባ ያስረዳሉ፡፡ (1ነገ.22፥17 ፤ ሕዝ.34፥5-6 ፤ ዘካ.10፥2 ፤ ማቴ.9፥36 ፤ 1ጴጥ.2፥25) በግ ከመንጋው  መካከል ተለይቶ ብዙም ሳይርቅ ቢሄድ እንኳ ከመንጋው ተመልሶ የመገናኘት ዕድሉ አጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡ “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ ቢያውቅም” (ኢሳ.1፥3) ፤ በግ ግን በጣም ተቅበዝባዥና የእረኛውን ክትትልና ጠብቆት ዘወትር የሚሻ እንሰሳ ነው፡፡
  እንደበግ ተቅበዝባዥ እንሰሳ ከሌለ እንደበግ ምሪት የሚፈልግ እንሰሳ የለም ማለት ነው፡፡ ትንሽ ነገር ያስበረግጋቸዋልና ቶሎ ቶሎ ሊጐበኙ ይገባል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በግና እረኛ ልዩ ትስስር ስላላቸው ነው ፤ ዳዊት “ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። … ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ …” (መዝ.23፥3 ፤ 6) በማለት የዘመረው፡፡ በእርግጥ ፥ እውነተኛ እረኛ በጐችን ወዴት ሊሄዱ እንደሚገባቸው ፣ የት መሠማራት እንዳለባቸው ከፊት ቀድሞ ይመራል እንጂ ከኋላ ሆኖ አይነዳም፡፡
   በግና እረኛ ልዩ ትስስር እንዳላቸው ጌታ ኢየሱስም “ … ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል ፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።” በማለት አስቀምጦታል፡፡ (ዮሐ.10፥3)  እረኛው የራሱን እንጂ ሁሉን በግ መጥራት አይሆንለትም፡፡ ስለዚህም እረኛ በስማቸው ለመጥራት የራሱ የሆኑ በጎችን እንደሚያውቅ ሁሉ “ … ጌታ[ም] ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል”፡፡ (2ጢሞ.2፥16) በዚህ ሳያበቃ እውነተኛ እረኛ ነፍሱን ለበጎቹ አደጋ ላይ በመጣል አሳልፎ እንደሚሰጥ ሁሉ (ዘፍ.31፥39 ፤ 1ሳሙ.17፥34) ክርስቶስ ኢየሱስ በጎቹ ለምንሆን ለእኛም ራሱን ፍጹም አሳልፎ የሠጠ ነው፡፡ እረኛው ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ያንን የሞት መከራ አልፎ ከበጎቹ በሰላምና በደስታ እንደሚኖር እንጂ ሞቶ እንደሚቀር  ከቶውንም አያስብም፡፡
  
   ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን መልካም እረኛ (ዮሐ.10፥11) ፣ የበጎች ትልቅ እረኛ (ዕብ.13፥20) ፣ የእረኞች አለቃ (1ጴጥ.5፥4) ከተባለው ሙሽራዋ ኢየሱስ የተማረችው ትምህርት ለመንጋው ከማይራሩ ጨካኝ እረኞች እርሷ በመራራት፥ ለራሷም በመጠንቀቅ በጎችን ማሠማራት እንደሚገባት ነው፡፡ (ሐዋ.20፥29) ቤተ ክርስቲያን ለራሷም ተጠንቅቃ ለሌላውም መንጋ በመራራት የምትጠነቀቀው በመጀመርያ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መቀበል ስትችል ነው፡፡ ያለኢየሱስ መንፈስ ወይም ያለመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ምንም ናት፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ምሪትን ለመቀበል የተዘጋጀች ሆና ልትገኝ ይገባታል፡፡ የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን አማኞች የይሆናልንም ፤ የአይሆንምምንም ምሪት ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበሉ ፤ ለተቀበሉት ምሪት የሚታዘዙ ነበር፡፡ (ሐዋ.8፥26 ፤ 16፥7)
   እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን የእረኝነት ተግባር በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ልታደርግ ከተጠራች ታላቅ አደራ ተጥሎባታል ማለት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በፊት የነበረችው ቤተ እስራኤል በጎችን በአግባቡ ባለመጠበቋና ለበጎቹ የመጽናናትን ቃል ከሠራዊት ጌታ እየተላኩ ያመጡ የነበሩትን ነቢያትንና ካህናትን በመግደሏና በማሳደዷ (2ዜና.36፥15-16 ፤ ማቴ.23፥37) ምክንያት የኪዳኑን ጥላ ብቻ ይዛ መቅረቷና ቤቷ የተፈታ ወና ሆኖ መቅረቷ ይታወቃል፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሕዝቅኤል በአንደበት እጅግ በማዘን እንዲህ ተናግሯል፦ “የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም።” (ሕዝ.34፥4-6)
   ይህ የትንቢታዊ ወቀሳ ቃል የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ ይመለታታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአስር አመት ጊዜ ውስጥ አስራ አንድ ሚሊየን ማጣቷን በአንደበቷ አምናለች ፤ ስንቱን እንደፈለገችና እንዳገኘች ወይም ለመፈለግ እንዳሰበች የተናገረችው ነገር ግን ስለመኖሩ ምንም አልሰማንም፡፡ በግልጥ የምናውቀው ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየቻቸውንም ሆነ የጠፉባትን ለመፈለግ አይደለም የእኔ ናቸው የምትላቸውንም በአግባቡ እየያዘች እንዳልሆነ በግልጽ እያየን ነው፡፡ ዳሩ የወለደቻቸውን ልጆቿን መርሳትና “አንዴ እንደው ሄደዋልና አይመለሱም” ብላ ተስፋ የምትቆርጥ እናት ትኖራለች ብሎ መገመት እጅግ ይከብዳል፡፡ ለማውገዝ የሚሰበሰበውና ቁርጥ አጀንዳ የሚይይዘው  ሲኖዶስ ምናለ ለመሰብሰብ ፤ የጠፋውንም ለመፈለግ ትንሽዬ አጀንዳ ቢይዝ?!
  አዎ! የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዛሬም እንዲህ ይላል፦ “የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም…” እውነታው ማስተባበያ የማንሰጥበት ያፈጠጠ ነው ፤ “እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።”(ሕዝ.34፥10) የሚለው ተግሳጽ ሊያገኘን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
   እረኝነት ሙያ እንጂ አደራ ስላልመሰለን ለምንዳችንና ለቀን አበላችን ቅድሚያ ፣ ስብከትም ኑሮ ማደላደያም ሰለመሰለን ከተማ እንጂ የገጠሩን ሕዝብ አውቀን አይናችንን ጨፍነን እንዳላየ ሆነን ፈጽሞ ዘንግተናል፡፡ የጠፋውን የምንፈልገው ያለው ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ነው ፤ አልያ ግን የወጣውንና ያልተመለሰውን ያየ የትኛውም ጠላት አይኑን “በቤት ወዳሉት” ማማተሩን ለመናገር ነቢይ መሆን አያሻም፡፡ በተለያየ ምክንያትና በውግዘት የተለዩትን ፍትሐ ነገሥቱ “ኤጲስ ቆጶስ ሆይ የበደለውን አውግዘህ ብትለየውበውጭ አትተወው፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን መልሰው እንጂ፡፡ የጠፋውንም ፈልግ፡፡ ስለኃጢአቱ ብዛት እድናለሁ ብሎ ተስፋ የማያደርገውን በሁሉ ጠፍቶ ይቀር ዘንድ አትተወው፡፡ እንዲህም  ኤጲስ ቆጶስ የኃጥኡን ኃጢአት ሊሸከም ይገባዋል፡፡” እንደሚለው “በዱር የጠፋውን በግ(ኃጢአተኛ ወይም ኢ- አማኒ) ወይም  በቤት ውስጥ የጠፋውን ድሪም(ምእመን) እስኪያገኘው ድረስ መፈለግ”(ሉቃ.15፥8) የሚገባ አደራ ነው፡፡

ጌታ አስተዋይና ቅን ልብን ለሁላችን ያብዛ፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment