Friday, 6 February 2015

ጌታ የማያውቃቸው “የጌታ አገልጋዮች”


                                 Please Read in PDF

     ምስክርነት አንዱ የአምልኮ መገለጫ ነው፡፡ አንድ አማኝ “ክርስቶስ እርሱ ኢየሱስ ነው ወይም ክርስቶስ እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው” (ማቴ.16፥16 ፤ ሐዋ.9፥20 ፤22)ብሎ ወደቤተ ክርስቲያን አካል ሲጨመር አንዱ የየዕለት ዋና ተግባሩ ምስክርነት ነው፡፡ ያመንነውን በመናገር ብቻ የምንመሰክር አይደለንም ፤ በሕይወትና በምግባር(በሥራ) እንጂ፡፡ “በጸጋ ድነናል”(ኤፌ.2፥5) ካልን ልክ እንደመዳናችን ማመናችንም ከእኛ የሆነ አይደለም፡፡ ጸጋው በእምነት ካዳነን “ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ” ከእኛ ሥራ የተነሳ አይደለም፡፡(ኤፌ.2፥8)
  እኛን ለማዳን አብ ልጁን ወደምድር ሲልክ ፤ እኛ ምንም የተገባን አልነበርንም፡፡ ስለዚህ “በእንዲሁ ፍቅር”(ዮሐ.3፥16) ወዶን በልጁ ሞት አዳነን፡፡ የልጁን ማዳንም እንድንቀበልም በልባችን የእምነትን አቅም ያኖረው እርሱ ነው፡፡ ነጻ ምርጫችንን ጠብቆ ፥ አምነን ወደእርሱ በመጣን ጊዜ ግን እንድናምነው ጉልበት የሆነን ያዳነን ያው ጌታ ነው፡፡ እንዲሁ “መልካሙን ሥራ ለማድረግም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነልን አዲስ ፍጥረት መወለድ(መፈጠር) ያስፈልገናል፡፡ (ኤፌ.2፥10)

   ከክርስቶስ ኢየሱስ በአዲስ ልደት ያልተወለደ መልካም ለማድረግ አቅም የለውም፡፡ “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው”ና (ዮሐ.3፥6) ከመንፈስ ቅዱስ የሆነውን የመንፈስን ሥራ(ፍሬ) ለማፍራት አይቻለውም፡፡ ምክንያቱም “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና …  ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና” (ሮሜ.8፥5-6) ስለዚህም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ “ … ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የተወለዱ” (1ጴጥ.1፥5) በምንም አይነት መንገድ “ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት አይለውጡም፡፡” (ይሁ.4)
   ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው (ሥጋ ለብሶ በተመላሰበት ዘመኑ) ድውያንና ኃጢአተኞችን ካለባቸው ነገር ከፈወሰ በኋላ ከሚሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች “ወደ መንደሩ አትግባ” (ማር.8፥26) ፤ “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” (ዮሐ.5፥14) ፤“ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ”(ዮሐ.8፥11) የሚሉት በዋናነት ይገኙባቸዋል፡፡ ካመነ በኋላ ወደኋላ የሚመለስን አማኝ ጠላት ከፊት ይልቅ ሰባት እጥፍ እንደሚሰብረውና እንደሚያጠቃው (ማቴ.12፥45) ፤ ደግሞም “በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ እንደሚሆንባቸው” የተረገጠ የታላቁ መጽሐፍ እውነት ነው፡፡ (2ጴጥ.2፥20) ሶምሶን የገዛ መንገዱን ተከትሎ የወላጆቹንና የአምላኩን ቃል ችላ ባለ ጊዜ ያገኘው ክፉ ውርደት ነው፡፡ (መሳ.14፥3 ፤ 16፥21 ፤ 25) ይሁዳም ቢሆን በብዙ ምክር ቢነገረውም ከማስተዋል ቸል ብሎ(ሉቃ.22፥22 ፤ ሐዋ.1፥18) በክፋቱ በጸና ጊዜ ያገኘው እጅግ ክፉ ነው፡፡
   በአገልጋዮች መካከል ዛሬ እየሰማን ያለነው ነገር እጅግ አስነዋሪ ፥ አህዛብና አለማውያን በእግዚአብሔር እንዲዘብቱ የሚያደርግ ድርጊትን ነው፡፡ ከአንዱ ቤተ ሃይማኖት ግብረ ሰዶማዊነት አብቦ በብዙ ደጋፊዎች አጃቢነት ይፈካል ፤ ከሌላኛው ቤተ ሃይማኖት ደግሞ ሴሰኝነትና ልቅ አመንዝራነት ገደቡን ጥሶ ይፈሳል፡፡ የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር አይን ባወጣ ነውር የሚመላለሱና ንስሐ ለመግባት በእልኸኝነት የሚመላለሱ “አገልጋዮችና አጃቢዎቻቸው” ጽሁፎቻቸው ፣ መጻህፍቶቻቸው ፣ ግጥሞቻቸው ፣ ዜማ መዝሙራቸው ፣ ስብከቶቻቸው … ፍጹም መንፈሳዊና የብርሃን መልአክ የሚመስል መሆኑ “አውቀን” እንኳ ዛሬም ብዙዎች አለማስተዋላችን ነው፡፡ (2ቆሮ.11፥14)
   በእርግጥ ቅዱስ ፣ ነውር የሌለባቸው ፣ ጻድቃን … ያልናቸውና ብለን የተሟገትንላቸው አገልጋዮች ድንገት አድራሻቸው አመንዝራነት ፣ ግብረ ሰዶማዊነት ፣ ሴሰኝነትና የከፋ ነውር ሲሆን ጌታ ሳያውቃቸው እንደሰው ልማድ በማወቃችን ተሸማቅቀናል ፤ አፍረናልም፡፡ የእነርሱ ወገን ተብሎ መጠራትንም ተጠይፈናል፡፡ የተጠየፍናቸው እኛ ንጹሐን ፣ ንዑዳን ፣ ክቡራን ፣ ምንም ነውር የሌለብን ሆነን ሳይሆን ለራሳቸው ስድ ሆነው ሕዝቡን እንዲነወሩ ወደስድነት ስለለቀቁት በመቃረንና በመቃወም እንደሌዋውያን ለእግዚአብሔር ሥራ በማድላት ወግነን ነው፡፡ (ዘጸ.32፥25-26) ኃጢአተኞች ብንሆንም በእግዚአብሔር ምህረት ላይ እየዘበትን ሌሎችን ከሚያሰናክሉ የአፍ አማኞች ወገን አይደለንም፡፡ አንድ ነገር ታወሰኝ ፦እንዲህ የሚል የአንድ ወንድም ጸሎት፥ “ጌታ ሆይ “ከኢየሱስ እንደነበሩ አወቁአቸው” ተብሎ እንደተጻፈ ፤ እኚህ ነበሩ አይሁንብን” አሜን፡፡ አዎን አሜን፡፡
  ጌታ ኢየሱስ “ማንም እርፍ በእጁ ይዞ ወደኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” (ሉቃ.9፥62) ብሎ ሙታናቸውን ለሚቀብሩ ሙታን ተናግሯል፡፡ አማኝም ሆነ ያመነ አገልጋይ ጌታ ኢየሱስን ሁል ጊዜ በማየት ካላገለገለ “ለእውነት እንዳይታዘዝ በሚያደርግ አዚም ” መያዙ አይቀርም፡፡ (ገላ.3፥1) እውነተኛ አገልጋይ ከተማው ወንጌል ፤ አላማው መስቀል ነው ፤ ከዚህ በቀር ምንም ምን አድራሻ የለውም፡፡ ዳሩ በተቃራኒው የሚሰለፉ ደፋር አገልጋዮች እንዳሉ ታላቁ ጌታ ፤ ጌታ ኢየሱስ ነግሮናል፡፡ እኒህ አገልጋዮች “በጌታ ስም ትንቢት ሊናገሩ ፣ በስሙ አጋንንትን ሊያወጡ ፣ በስሙ ብዙ ተአምራትንም ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡” (ማቴ.7፥22-23) ይህ ብቻ ሳይሆን ከላይ እንዳልኩት አገልግሎታቸው ፣ መዝሙራቸው ፣ መጻህፍቶቻቸው ፣ ስብከታቸው … ውብ ሆኖ ብዙዎችን ሊማርክ ይችላል ፤ ነገር ግን የጌታ መልስ አንዲት ብቻ ናት “ከቶ አላወቅኋችሁም ፤ እናንተ ዓመጸኞች ከእኔ ራቁ” ወይም “እናንተ ርጉማን … ከእኔ ሂዱ” (ማቴ.7፥23 ፤ 25፥41) የምትል፡፡
    እኒህን የአምልኮ መልክ ብቻ ይዘው ኃይሉን የካዱትን (2ጢሞ.3፥2) ፣ ጥበበኞች ነን ሲሉ የደነቆሩትን (ሮሜ.1፥22) የማያውቃቸው ከመጀመርያው ነው፡፡ እርሱ ለሚመለስ ኃጢአተኛ እንጂ ሊሰበር አንገቱን ለሚያደነድን ሰነፍ የማያዳላ እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለኃጢአት ፍርድ የማይቸኩለው “የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ፥ ፍርድንም የሚያመለክት ሆኖ ፥ ሌሎችን ግን የሚከተላቸውና ፤ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ሆኖ፥ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር ስለማይችል ነው።” አዎ! ግብረ ሰዶማውያኑም ፣ አመንዝራውና ሴሰኛው ምዕመንም ይሁን አገልጋይ  ከልቡ ዳግም ወደኃጢአት ላይመለስ፥ እንደጌታ ትምህርት ቢመለስ የእግዚአብሔር እጅ ዛሬም ለማዳና ያላጠረች ፤ የምትቀበል ናት፡፡ ከኃጢአታቸው ጋር መቼም መች አንተባበርም ፤ አምላካችን ቅዱስ ነው ፤ እንዲገለገልም ፤ እንዲመለክም የሚሻው በቅድስናና በንጽዕና ብቻ ነው!
   አመንዝሮችንና ግብረ ሰዶማውያንን ፣ ዘፋኞችንና ጠንቋዮችን … በመካከሏ ይዛ ቤተ ክርስቲያን ነኝ ብላ የምትሟገት ፤ ዳሩ ስለኃጢአቷ ንስሐ የማትገባዋን ቤተ ክርስቲያን ጌታ በጅራፍ እንደሚነሳባት  እናምናለን! እጅግ የሚያሳዝነው በአደባባይ የበደለ አገልጋይ ንስሐ እንዲገባ ፣ የበደላቸውን ይቅርታ እንዲጠይቅ ፣ ኃጢአቱን በመናዘዝ ይቅርታ እንዲያገኝ ከመምከር ፣ ከመገሰጽ ፣ መንገድ ከማሳየት ይልቅ በጭፍን የተሳሳተውን አገልጋይ “ያንተ ኃጢአት ከሌላው በምን ይለያል? ፤ ምነው አንተ ብቻ ነህ እንዴ ኃጢአት የሠራኸው? ፣ ኃጢአት ባንተ አልተጀመረ?! ፣ ስለሚበልጣቸው በዚህ አጥምደው ጣሉት … የሚሉና  … እርሱን የምትናገሩ እርሱን ለመናገር ሞራል የላችሁም ፣ ኃጢአት የሌለበት ብቻ እርሱን ይናገረው ፣ ሠራ … ታዲያ ምን ይጠበስ?...” የሚሉ አንዳንዴ በክርስቶስ ቦታ ፣ አንዳንዴ በበዳዩ ሥፍራ ፣ አንዳንዴ በሰይጣን ሥፍራ ተቀምጠው መፍረድ አይሉት ፣ መርዳት አይሉት ፣ መከላከል አይሉት … የሚሠሩትን የማያውቁ ደጋፊዎችና አጃቢዎች በዳዩን ንስሐ ከመግባት እያዘገዩና እልኸኛ እያደረጉት እንደሆን ቢያስተውሉ እጅግ መልካም ነው፡፡ እውነተኛ የአማኝ ልብ፥ ለበደለው ጥፋቱ ግልጽ ይቅርታን የሚጠይቅና ለአምልኮ ንጽሕናው የሚተጋ እንጂ ከጌታ ፍርድ የማያስጥሉ የእንቧ ካብ ደጋፊዎችን ተከልሎ የሚያስሟግትና ዳር ሆኖም የሚያይ አይደለም፡፡
     እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ እውነተኛ ፍቅር ደግሞ ከእውነት ጋር ብቻ ይተባበራል እንጂ ሐሰትንና ኃጢአትን አያሽሞነምንም፡፡ ስለዚህም ፈራጁ ጌታ በፍቅርና በርኅራኄ እንዲመጣ ንስሐ እንግባ! እልኸኛ ልባችንን በትህትና እናዋርደው እንጂ የቤት ልጅ በመሆናችን በከንቱ ልንታበይ አይገባንም ፤ እርሱ ለአብርሃም ልጆችን ድንጋይ ከተባሉት ከአህዛብ መካከል ሊያስነሳ እንደሚችል ሲናገር እንዴት ብሎ የጠየቀው አንድም የለምና፡፡ ጌታ የማያውቃችሁ የጌታ አገልጋዮች ሆይ መንገዳችሁን በመንገዱ ፊት አሁኑኑ አጥሩ፡፡  

       እኛን ከኃጢአተኞች ኃጢአት ጋር ከመተባበር ጌታ ይርዳን፡፡ ከኃጢአተኞች ጋር የሚተባበሩትንም ልብ ይስጣቸው፡፡ አሜን፡፡

1 comment: