Monday 15 September 2014

ሦስቱ ባህታውያን (ክፍል አንድ)



አጭር ልብወለድ
(ምንጭ ብሪቱ መጽሔት ጥር - የካቲት 1991)
(ደራሲ፦ ሊዎ ቶልስቶይ)
(ተርጓሚ፦ ሁነኛው ጥላሁን)

“አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።” (ማቴ.6፥7-8)

     አቡኑ ከአርካንጌልስክ ከተማ ወደ ሶሎቬትስኪ ደሴት በመርከብ እየተጓዙ ነበር፡፡ ቅዱሱን ሥፍራ ለመሳለም የሚሄዱ ምዕመናንም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ የነፋሱ አቅጣጫ አመቺ፣ አየሩም ማለፊያ ነበረ፡፡ ባህሩም ጸጥ ብሏል፡፡ ምእመናኑ ገሚሱ ጋደም ብለው ከፊሉም ከያዙት ስንቅ እየቀማመሱ የተቀሩትም በቡድን በቡድን ተቀምጠው እርስ በእርስ ያወራሉ፡፡ አቡኑ ከነበሩበት ተነስተው ወደ መርከቡ መተላለፊያ መራመድ  ጀመሩና ወደጫፉ ሲቃረቡ ሰብሰብ ያሉትን ሰዎች አዩዋቸው፡፡ አንድ ባላገር ወደባህሩ እያመለከተ አንድ ነገር እያሳያቸው ሲናገር ሰዎቹ ያዳምጡት ነበር፡፡ አቡኑ ቆም ብለው ባላገሩ ወደሚያመለክትበት በኩል ተመለከቱ፡፡ በፀሐይ ከሚያብረቀርቀው ባህር በስተቀር ምንም የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡ ወደሰዎቹም ጠጋ ብለው ባላገሩ የሚለውን ማዳመጥ ጀመሩ፡፡ ባላገሩ አቡኑን እንዳየ ባርኔጣውን በማውለቅ ንግግሩን አቋርጦ ፀጥ አለ፡፡ የሚያዳምጡትም ሰዎች ባርኔጣዎቻቸውን በማንሳት በአክብሮት ተቀበሏቸው፡፡
    “በመምጣቴ አትጨነቁ ወዳጆቼ” አሉ አቡኑ፡፡ ወደባላገሩም ፊታቸውን አዙረው “የመጣሁት አንተ የምትነግራቸውን ለመስማት ብዬ ነው” አሉት፡፡

   “ይህ ዓሣ አጥማጅ ስለባህታውያኑ ምን ነገራችሁ?” ሲሉ አቡኑ ጠየቁ፡፡ ወደ መደገፊያውም መትተው ካንዲት ሳጥን ላይ ተቀመጡ፡፡ “እስቲ ለኔም ንገረኝ፣ ልስማው፤ የምታያቸው ምን ነበር?”
“ራስዎ ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ወደዚያች ትንሽ ደሴት ነው ያመላከትኳቸው፡፡” ብሎ ባላገሩ በስተቀኝ በኩል ወደ ፊት ለፊት አመለከተ፡፡ “በዚያች ደሴት ላይ ነው ባህታውያኑ የሚኖሩት፣ ከኃጢአት እንዲያርቃቸው እግዜርን እየተማጠኑ፡፡”
“ታዲያ ደሴቲቱ የታለች” ጠየቁ አቡኑ፡፡
“ይኸውሎት፣ በእጄ ትይዩ ይመልከቱ፣ ያ ደመና ይታይዎታል? ከዚያ ትንሽ ወደግራ ዝቅ ብለው ስስ መስመር ለይቶ የሚታው ሥፍራ”
አቡኑ ደግመው ደጋግመው ወደ ተባለው አቅጣጫ ተመለከቱ፡፡ ነገር ግን ልምድም ስላልነበራቸው ምንም ሊያዩ አልቻሉም፡፡
“ላየው አልቻልኩም፡፡ ለመሆኑ ምን ዓይነት ባህታውያን ናቸው በዚያች ደሴት ላይ የሚኖሩት?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
“የእግዜር ሰዎች ናቸው፡፡” አለ ባላገሩ፡፡ “ስለእነርሱ የሰማሁት ከብዙ ጊዜ በፊት ቢሆንም የማየት ዕድሉ ፈጽሞ አላጋጠመኝም ነበር፡፡ እናም ካቻምና በጋ ላይ እኔ ራሴ አየኋቸው፡፡”
ከዚያም ዓሣ አጥማጁ ለሰዎቹ የነገረውን ደገመላቸው፡፡ ዓሣ ለማጥመድ ወጥቶ በደሴቷ ጠባብ ሰርጥ ውስጥ ሰጥሞ እንደነበርና የነበረበትን ሳያውቅ እንደቆየ፣ ከዚያም በማለዳ እየተንገላወደ ካንዲት የጭቃ ጐጆ ስለመድረሱና በአቅራቢያው አንድ ባህታዊ ስለማየቱ፣ ቀጥሎም ሌሎች ሁለት ባህታውያን ጭምር ከጎጆዋ ወጥተው አብልተውት፣ ልብሶቹን አደራርቀውለትና የተሰበረች ጀልባውንም በመጠገን እንዴት እንደረዱት በዝርዝር አወጋቸው፡፡
“እና ሰዎቹ ምን ይመስላሉ?” ጠየቁ አቡኑ
    “አንደኛው በጣም ደቃቃ ሰውነት ያላቸው፣ ከትከሻቸው የጎበጡና ፈጽሞ ጥንታዊ የሆኑ ሰው ናቸው፡፡ ያረጀች ትንሽ ካባ የለበሱና ዕድሜያቸው ከመቶ በላይ መሆን ያለበት ነው፡፡ ገብስማ ጢማቸው ወደአረንጓዴነት መለወጥ ጀምሯል፡፡ ነገር ግን የማያቋርጥ ፈገግታ የሚያሳዩና ገጽታቸው እንደሰማይ መልአክ የፈካ ነው፡፡ ሌላኛው ትንሽ ረዘም ብለው የተቀደደ ኮት የለበሱና ሰፊ ወይባ ነጭ ጢም ያላቸው ሽማግሌ ናቸው ሆኖም ጥንካሬያቸው ለጉድ ነው፡፡ ጀልባዬን እንደቧንቧ መክፈቻ ነው ያዞራት፡፡ በጥገናቸው ላይ እንድረዳቸው ዕድል እንኳን አላገኘሁም፡፡ በዚህም ላይ ደስተኛ ናቸው፡፡ ሦስተኛውም ቁመታቸው ረዥም ጢማቸው እስከ ጉልበታቸው የተንዠረገገና ነጭ ነው፡፡ የሐዘን መንፈስ የሚታይባቸው ሲሆን ቅንድባቸውም ከዐይናቸው በላይ ተንጠንጥሏል፡፡ እንደመቀነት ካሰሩት የቃጫ ዘባተሎ በስተቀር ፈጽሞ ዕርቃናቸውን ናቸው፡፡”
   “ካንተ ጋር ስለምን ጉዳይ አወራችሁ?” አቡኑ መጠየቃቸውን ቀጠሉ፡፡
   “ሁሉንም ነገር የሚያደርጉት በአብዛኛው ፀጥ ብለው ነው፡፡ እርስ በእርሳቸውም ብዙ አያወሩም፡፡ ግን አንደኛው ቀና ብለው ከተመለከቱ ሌላኛው ምን እንደሚያስቡ ይገባቸዋል፡፡ ረዥሙን ሽማግሌ እዚያ ለብዙ ዓመታት ኖረው እንደሆነ መጠየቅ ጀመርኩኝ፡፡ ግንባራቸውን ቋጠሩና ሊናገሩ ጀምረው የተቆጡ መሰሉ፡፡ ወዲያውኑ ትንሹ ጥንታዊ ሰው እጃቸውን ይዘዋቸው ሄዱና ፈገግታ እያሳይዋቸው “አቤቱ ይቅር በለን” ሲሉ ትልቁ ሰው ጸጥ አለ፡፡
   ባላገሩ እየተናገረ በነበረበት ጊዜ መርከቧ ወደ ደሴቲቱ እየተጠጋች ነበር፡፡
  “አሁን በእርግጥ ሊያዩት ይችላሉ፡፡”  አለ ነጋዴው፡፡ “አባታችን ቢመለከቱት፡፡”
አቡኑ ተመለከቱ፡፡ በእርግጥም እንደተባለው ጠቆር ያለ ስስ መስመር አዩ፡፡ ትንሿን ደሴት ለጥቂት ጊዜ ሲመለከቱ ከቆዩ በኋላ ከመርከቢቷ የፊት ጫፍ ወደ ኋለኛው ጫፍ በመሄድ የመርከቧን ዋና ኃላፊ አገኟቸው፡፡
“ያቺ የምታያት ደሴት ማናት?” ሲሉ ጠየቁት
“ስም የላትም፡፡ የዚህ አይነት ደሴቶች እዚህ አካባቢ ብዙ አሉ፡፡”
“ከአለማዊ ነገር የተገለሉ ባህታውያን እዚያ ይኖራሉ የሚባለው እውነት ነው?”
“እንደዚያ ይባላል አባታችን፤ ነገር ግን እውነት ስለመሆኑ አላውቅም፡፡ የተወሰኑ ዓሣ አጥማጆች አይተዋቸው ነው የሚሉት፡፡ ምናልባትም እንዲያው የሥራ ፈት ወሬ ይሆናል፡፡”
“እዚያች ደሴት ወርጄ ባህታውያኑን ማየት እወዳለሁ፡፡ ይህንን እንዴት መፈጸም ይቻላል?” ሲሉ ጠየቁ አቡኑ ፡፡
   “መርከቡ መጠጋት አይችልም፡፡ በጀልባ ሆነው ግን መድረስ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ካፒቴኑ መጠየቅ አለበት፡፡”
   ከዚያም ካፒቴኑን ጠሩት፡፡
  “እነዚያን ባህታውያን ቀርቤ ብመለከት እወዳለሁ፡፡ ወደዚያ ልትቀዝፈኝ አትችልም?”
   ካፒቴኑ አቡኑ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ ሞከረ፡፡
  “ወደዚያ መቅዘፍ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ረዥም ጊዜ በከንቱ ማባከን ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ለአባታችን መግለጽ ቢያስፈልግ ሰዎቹ የሚታዩ አይነትም አይደሉም፡፡ እዚያ የሚኖሩት ጅላጅል፣ ሽማግሌዎች ልክ ከባህር ዓሣዎች እንደ አንዱ ዓይነት መናገርም ሆነ ነገሮችን መረዳት የማይችሉ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፡፡”
    “መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ ችግሩ መስዋዕት ቢያስከፍለኝም እዚያ ውሰደኝ፡፡” አሉ አቡኑ፡፡
    ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ መርከበኞቹ ትዕዛዝ ሰጥተው ሸራዎቹ ለንፋሱ አመቺ ሆነው ተስተካከሉና ኃላፊው የመርከቧን አቅጣጫ ለውጦ ወደደሴቲቱ ገሰገሱ፡፡

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment