አቡኑ ከመርከቢቷ የፊት ጫፍ ላይ ወንበር ቀርቦላቸው ሲቀመጡ ሌሎቹም
ሁሉ መጥተው ወደ ትንሿ ደሴት መመልከታቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥሩ የማየት ችሎታ ያላቸው ሰዎች በደሴቷ ላይ የሚገኙትን አለቶችና የጭቃ
ጎጆዋንም ማየት ችለው ነበር፡፡ ከመሃላቸው አንዱ ሦስቱን ባህታውያን ጭምር መለየት ችሎ ነበር፡፡ ካፒቴኑ አጉሊ መነጽር አምጥቶ
ከተመለከተ በኋላ ለአቡኑ እየሰጣቸው፦
“ትክክል ነው፡፡ ከባህሩ ጠረፍ ላይ ከትልቁ አለት እንዲህ ወደ ቀኝ ሲሉ
ሦስቱ ባህታውያን ቆመው ይታያሉ፡፡” አለ፡፡
አቡኑ በመነጽር ተመለከቱ፡፡ ወደትክክለኛው አቅጣጫም አዞሩት፡፡ የተባለው
እውነት ነው፡፡ ሦስቱም እዚያው ቆመዋል፡፡ አንደኛው ረዥም ሌላኛው ትንሽ አጠር የሚሉና ሦስተኛው ደቃቃ ትንሽ፡፡ ሦስቱም ከባህሩ
ጠረፍ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመው ነበር፡፡
ወዲያው ገመዶች ተዘርግተው መልህቅ ተጣለና ሸራዎች ተጠቅልለው ሲታሰሩ መርከቡም
ተርገፍግፎ ቀጥ አለ፡፡ ከመርከቡ ላይ ጀልባ እንዲወርድ ተደርጐ ቀዛፊዎቹ እየዘለሉ ሲገቡ አቡኑም በመሰላል መውረድ ጀመሩ፡፡ ከጀልባዋ
ውስጥም ገብተው እንደተቀመጡ ቀዛፊው ወደ ደሴቷ መቅዘፉን ተያያዘው፡፡ ድንጋይ ቢወረወር ከሚደርስበት ርቀት ሲቃረቡም ሦስቱ ባህታውያን
እንደቆሙ ታዩዋቸው፡፡ ረዥሙ ዘባተሎ ከምንተፍረታቸው ግድም ከማድረጋቸው በስተቀር ራቁታቸውን ሆነው፣ አጠር የሚሉት የተቀዳደደ ኮት
ለብሰውና ጥንታዊውም በጐበጠ ትከሻቸው ላይ ትንሽ አሮጌ ካባ አድርገው ሦስቱም እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል፡፡
ቀዛፊዎቹ ወደ ውሃው ዳርቻ ተጠግተው ጀልባዋ ከታሰረች በኋላ አቡኑ ከጀልባዋ
ወጡ፡፡
ባህታውያኑ ጐንበስ ብለው እጅ ሲነሷቸው አቡኑ መረቋቸው፡፡ ባህታውያኑም
ይበልጥ ዝቅ ብለው አጐነበሱ፡፡ አቡኑም እንዲህ ሲሉ አናገሯቸው፡፡
“እናንት የእግዜር ሰዎች፣ እዚህ በምናኔ እየኖራችሁ ለአህዛብ ሁሉ መዳን
ለፈጣሪያችን ክርስቶስ እንደምትጸልዩ ሰማሁኝ፡፡ እኔም አገልጋዩ ነኝ ለመባል የማልበቃ፣ በእግዜር በጎ ፈቃድ መንጋዎቹን ለመጠበቅ
የተጠራሁ በመሆኔ እናንተን የእግዜርን አገልጋዮች ለማየትና የምችልም
ብሆን መመሪያ ልሰጣችሁ ፈለግሁኝ፡፡”
ባህታውያኑ በፀጥታና በፈገግታ እርስ በርሳቸው ተያዩ፡፡
“ከኃጢአት ለመራቅ የምታደርጉትንና እግዜርን እንዴት እንደምታገለግሉ ንገሩኝ፡፡”
አሉ አቡኑ፡፡
የመሀለኛው ባህታዊ በረዢሙ ተንፍሰው ወዳረጁት ጥንታዊ ሰው ተመለከቱ፡፡
ረዢሙ ባህታዊም ግንባራቸውን ቋጠሩና ያረጁትን ጥንታዊ ሰው አዩዋቸው፡፡ አንጋፋው ጥንታዊው ባህታዊ ፈገግ ብለው እንዲህ አሉ፡፡
“የእግዜር አገልጋይ ሆይ፣ እንዴት ብለን እግዜርን አንደምናገለግል አናውቅም፡፡
እኛ የምናገለግለው ራሳችንን ነው፡፡ የምንቀበለውም ራሳችንን ነው፡፡”
“ታዲያ እንዴት ብላችሁ ነው ለእግዜር የምትጸልዩት?” ጠየቁ አቡኑ፡፡
ጥንታዊው ባህታዊም መለሱላቸው፡፡
“እንዲህ ብለን እንጸልያለን፡፡ አንድም ሦስትም የሆንከው አቤቱ ይቅር
በለን፡፡ እኛም ሦስታችን ይቅር የምናባባል እንሁን፡፡”
“ባህታዊው ይህን ከማለታቸው ሦስቱም በአንድነት ወደ ሰማይ ቀና ብለው ፀሎቱን
ደገሙት፤ “አንድም ሦስትም የሆንከው አቤቱ ይቅር በለን፡፡ እኛም ሦስታችን ይቅር የምንባባል እንሁን፡፡”
አቡኑ የሰሙት ነገር ፈገግ አሰኛቸው፡፡
“ስለቅድስት ሥላሴ ሰምታችሁ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን የምትጸልዩት
በተሳሳተ መንገድ ነው፡፡ እናንተ የእግዜር ባህታውያን የምወዳችሁ ሆኛለሁ፡፡ እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንደምትፈልጉና እንዴት ማገልገል
እንዳለባቸው ግን እንደማታውቁ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ የሚጸለየው እንደዚያ ተብሎ አይደለም፡፡ እኔን አዳምጡኝና አስተምራችኋለሁ፡፡
የማስተምራችሁም ራሴ በፈጠርኩት መንገድ ሳይሆን በጌታ ወንጌል መሠረት ማለትም እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ለሱ እንዲጸልዩለት ባዘዘው
መንገድ ነው፡፡”
ከዚያም እግዚአብሔር ራሱን እንዴት ለሰዎች እንደገለጸ በዝርዝር አብራሩላቸው፡፡
ስለእግዚአብሔር አብ፣ ስለ እግዚአብሔር ወልድ፣ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ካስረዱዋቸው በኋላ እንዲህ አሉ፡፡
“እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ዘር ለማዳን ወደዚህች ምድር መጥቶ እንዲህ ብለው
እንዲጸልዩ ሰዎችን አስተምሯል፡፡ አዳምጡና ከእኔ በኋላ እየተከተላችሁ ድገሙት፡፡”
አቡኑ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው
“አባታችን ሆይ” ብለው ጀመሩ፡፡ ባህታውያኑም በየተራ
“አባታችን ሆይ” አሉ፡፡
“በሰማይ የምትኖር”
ባህታውያኑም ደገሙላቸው፡፡
“በሰማይ የምትኖር” …
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment