Tuesday 9 September 2014

የተወደደችው የጌታ አመት (ሉቃ.4፥19)



እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም በፍቅር አሸጋገራችሁ!!!

    ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለማቋረጥ ከብዙ ህዝብ ጋር ለአምልኰ በመገኘት ለተከታዮቹ ደቀ መዛሙርት የሚደነቅ ምሳሌ የሚሆን ልምድ አለው፡፡(ማቴ.13፥54፤ ማር.1፥21፤ ሉቃ.4፥16፤ ዮሐ.7፥14) ጌታ ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር ዘወትር “መሰብሰብን ባለመተው” ለደቀ መዛሙርቱ አብነት ሆኗል፡፡(ዕብ.10፥24) ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት፤ ቃሉን ለመመርመርና ለማስተማር መሆንን ጌታ በእውነት እኛንም አስተምሮናል፡፡ ናዝሬት ጌታን ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆንም እርሱ ግን ወዳደገባትና ወደሚያውቃት ከተማ ምኩራብ መጥቶ አስተማረ፡፡ ዕድገታችንን፣ ማንነታችንን፣ ገመናችንን፣ ልጅነታችንንና፣ ውድቀታችንን … ምናልባትም “ልካችንን” በሚያውቁን ሰዎች ፊት ማገልገል ከባድ ህመም ይኖርበት ይሆናል፤ ጌታ ግን አድርጎታልና ልጆቹ በህይወቱ ልንታዘዝ፤ ህይወቱም ሊያስተምረን ይገባል፡፡
    ጌታ  ወደምኩራብ በገባ ጊዜ የኢሳይያስን ትንቢት ጥቅልል አንስተው ሰጡት፡፡ እርሱም ተነስቶ መጽሐፉን በመተርተር ማንበብ ጀመረ፡፡ አይሁድ ምንም እንኳ ወደ ተስፋው ፍጻሜ ባይደርሱም፤ የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ብቻ ሳይሆን መጻህፍትን በመቅደሱና በየምኩራቦቻቸው በአግባቡ የማስቀመጥ ልማድ ነበራቸው፡፡ በምኩራባቸው የእግዚአብሔር ቃል ጥቅልል ትልቁንና የመጨረሻውን ሥፍራ በክብር ይይዛል፡፡ ትልቅና የመጨረሻው አምልኰ ለእግዚአብሔር ቃልና ላስተማረን ትምህርቱ ልዩ ክብርን በመስጠት መታዘዝ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ቤት “መጻህፍት መደርደርያ” የተመሉት በልቦለድና በፍልስፍና “ጥቅልል ጽሁፎች” ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቃል ቸል በማለት ለሌሎች “ፍጡራን ጥቅልሎች” ትልቅ ክብርና ሥፍራ የሰጠ ትውልድ ይህ የእኛ ዘመን ትውልድ ነው ብል ያልተጋነነ እውነት ነው፡፡

    ጌታ የኢሳይያስን የትንቢት ጥቅልል መጽሐፍ አንስቶ ያነበበው እንደህጉ ትዕዛዝ ነው፡፡ (ዘዳግ.6፥6-10) የእግዚአብሔርን ቃል ዕለት ዕለት ማንበብ፣ ማጥናትና መመርመር እንዴት የሚደንቅ ልበ ሰፊነት ነው!? (ሐዋ.17፥10) ብዙ ጊዜ ሰንበት ትምህርት ቤትና ሠርክ ጉባኤያት የመከታተል ልማድ አለኝ፡፡ ሁሌም የማዝነው ግን በተለያዩ ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ጊዜ ማጠርና በተለያዩ ነገሮችም በመያዙ ነው፡፡ አዎ! ጌታ ኢየሱስ መምህራችን ከሆነ ትልቁንና ሰፊውን የአውደ ምህረትና የህይወት ሰዓት መውሰድ ያለበት የቅዱስ ቃሉ ንባብና ጥናት፤ መታዘዝም ነው፡፡  
   ጌታ ያነበበው የመጽሐፉ ክፍል ኢሳ.62፥1-2 ያለው ሲሆን ክፍሉ የሚናገረውም ስለራሱ ነበር፡፡ ክፍሉ የሚያስደንቅ፤ የመሲሁን ህይወት ብቻ ሳይሆን መሲሁ ለሁሉም ሰው በተአምራቱ የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሰጥ አስረጅ ንባብ ነው፡፡ የአይሁድ መምህራን(ረበናት) ይህ ክፍል የመሲሁ መሆኑን ቢያውቁም ጌታ ግን በእነርሱ ፊት ይህን የመሲሁን ሥራ ሊሠራ፤ የተወደደችውንም የጌታ ዓመት ሊሰብክ እንደመጣ በግልጥ ተናገረ፡፡
     የእስራኤል ልጆች “ከሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት በኋላ አምሳኛው ዓመትን እንዲቀድሱት” በሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ታዘዋል፡፡ የስሙ ትርጓሜ “ቀንደ መለከት” እየተባለ በሚጠራውና በአምሳኛው ዓመት በሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል ላይ ባርያዎች ነጻ ወጥተው ወደቤተሠቦቻቸው ይመለሳሉ፣ የተሸጡና በዕዳ የተያዙት ርስቶች ለመጀመርያዎቹ ባለቤቶቻቸው የሚዛወሩበትና ዕዳዎች ሁሉ የሚሰረዙበት፤ ምድርም ሳትታረስ በየሃምሳኛው በዓል ላይ ከሰዎችና ከእንሰሳት ጋር ሐሴት ታደርጋለች፡፡(ዘሌዋ.25፥3-55)
    ኢሳይያስ አስቀድሞ እስራኤላውያን ከሚማርኳቸው ከባቢሎን እጅ ነጻ እንደሚወጡ ተነበየ፡፡ ጌታ ግን የትንቢቱ ፍጻሜ እንዲህ ላለው ቁሳዊና ለዚህ አለም ምድራዊ ሀሳብ ሳይሆን ፍጹም ለሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት የመጣ መሆኑን ትንቢቱን ከራሱ ጋር በማዋሀድ ተናግሯል፡፡ የተወደደችው የጌታ አመት የተባለችው የተወሰነ አመትን ሳይሆን የመዳኑ ነገርና ወንጌል የሚታወጅበትን ሙሉውን የመሲህ ኢየሱስን ዘመን የሚያመለክተውን ነው፡፡
   እንደተነገረው ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ ለአገልግሎት የተቀባው መድኃኒት ኢየሱስ እንደትንቢቱ ቃል ለድሆች ወንጌልን ሰብኳል (ማቴ.5፥1-7፥24፤ 11፥6)፣ ለታሰሩት መፈታትን(ማር.5፥1-14)፣ ለዕውሮችም ማየትንና(ማቴ.15፥31፤ ማር.10፥49) የተጠቁትንም ነጻ ያወጣ መሲህ ነው፡፡ እርሱ ከኃጢአት ደመወዝ ወይም ከኩነኔ(ሮሜ.6፥23፤ሮሜ.8፥1)፣ ከኃጢአት ኃይል(ሮሜ.8፥2)፣ ከኃጢአት መገኘት(ሮሜ.7፥22)፣ ከዘላለም ባርነት (ገላ.5፥1)፣ ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን እጅ(ሉቃ.1፥71)፣  በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን አንድ ጊዜ ሊሽር ተገልጧልና(ዕብ.9፥26) በእውነትም ዘመኑ የተወደደች ናት፡፡
    ደግሞም የጌታ አመት የተወደደች የተባለችው እርሱ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸክሞ፤ በመገረፉ ቁስል ፈውሶን”(1ጴጥ.2፥23) ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ህሙማንን ድካምና ደዌ በመቀበልና በመሸከምም ነው፡፡(ማቴ.8፥16) በእርግጥም ይህን ያየች ነፍስና መንፈስ ከጌታ የተነሳ ዘመኗ የኢዮቤልዩ፤ አመቷም የተወደደ ነው፡፡ ጌታ ለጠፉ ኃጥአን ደኅነንትንና ወንጌልን የምሥራች ብሎ ሰብኰ፤ ለተጣሉት፣ ከወገን ተገልለው ልባቸው ላዘነና ለተሰበረ የቀረበ አጽናኝ በመሆኑ፣ የራቁትን በፍቅሩና በርህራሄው በማቅረቡ ዘመኑ የምህረት፤ አመቱ የይቅርታ ተብሎልናል፡፡
   ምንም እንኳ ባለመድኃኒቱ ባደገባት በናዝሬት የተናቀ ቢሆንም ለዓለሙ ግን የሚበቃና የተትረፈረፈ መድኃኒት ሆኗል፡፡ በናዝሬት አድማጭና ተቀባይ ባይኖረውም ኃጢአተኝነታቸውን አምነው የቀረቡትን ግን በዘመናት በዕረፍቱና መውደዱ ውስጥ አርፈዋል፡፡ አገልጋይቱ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! የተሾምሽው ዘመኑን  በቅዱስ የወንጌሉ ቃል ምስራች የተወደደ የጌታ አመት መሆኑን ትሰብኪ ዘንድ ነው! አንተም አማኙ ሆይ! ዕረፍትህ፤ የአመቶችህም መባረክ በቅዱስ ቃሉ ነውና ቃሉን ብላው አንብበው፤ ጉልበት ይሆንህና ድል ታደርግበትም ዘንድ ታዘዘው፡፡

ጌታ የተጨመረልንን ዘመን የተወደደ ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡       

No comments:

Post a Comment