ነገር ግን ሁለተኛው ባህታዊ ቃላቶቹን
አቀላቅለው አሳስተው ተናገሩ፡፡ ራቁታቸውን ያሉት ረዥሙ ባህታዊም አጣርተው አልደገሙትም፡፡ ጢማቸው አፋቸውን ሸፍኖት ስለነበር የተጣራ
ድምፅ ሊያወጡ አልቻሉም፡፡ ጥንታዊው ደግሞ ጥርሶቻቸው ስለረገፉ በግልጽ የማይሰማ ነገር ነው ያጉተመተሙት፡፡
አቡኑ እንደገና ደገሙላቸው፡፡ ባህታውያኑም እንደገና ደገሙት፡፡ አቡኑ በትንሽ
ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ባህታውያኑም በአጠገባቸው ቆመው አፍ አፋቸውን አፍጠው እየተመለከቱ የሚሏቸውን ይደግሙላቸው ነበር፡፡ ቀኑን
ሙሉ እስከአመሻሽ ድረስ ሊያስተምሯቸው ደከሙ፡፡ አንዲቷን ቃል አስር፣ ሃያ፣ መቶ ጊዜ እየመላለሱ አስጠኗቸው፡፡ ቃላት እየተቀለቀሉባቸው
ሲቸገሩ ያርሟቸውና እንደገና ከመነሻው ያስጀምሯቸዋል፡፡
የጌታን ጸሎት ሙሉ ለሙሉ እስከሚያስተምሯቸው ድረስ አቡኑ ከባህታውያኑ
ዘንድ ቆዩ፡፡ በመጨረሻም ያለ አቡኑ ድጋፍ እያንዳንዳቸው በራሳቸው ሙሉ ጸሎቱን ወረዱት፡፡
አቡኑ ወደ መርከቡ ሊመለሱ ሲነሱ ጨለማው እየከበደ ከባህሩም ጨረቃ እየወጣች
ነበር፡፡ ባህታውያኑን ሲሰናበቱ ሁሉም እስከመሬት አጐንብሰው ሸኟቸው፡፡ እሳቸውም እያንዳንዳቸውን ካጐነበሱበት ቀና እያደረጉና እያቀፏቸው
ባስተማሯቸው መሠረት እንዲጸልዩ ካዘዟቸው በኋላ ወደ ጀልባዋ ገቡ፡፡
ወደ መርከቡ እየተመለሱ ሳለ ባህታውያኑ የጌታን ጸሎት ጮክ ብለው ሲደግሙ
ይሰማቸው ነበር፡፡ ወደ መርከቡም ሲቃረቡ ድምጻቸው ባይሰማም እንኳ እዚያው ባህሩ ዳርቻ ላይ እንደቆሙ በጨረቃዋ ብርሃን ይታዩ ነበር፡፡
አጭሩ ከመሀል፣ ረዢሙ በስተቀኝ፣ መሀከለኛው በስተግራ ነበሩ፡፡ አቡኑ ከመርከቡ ገብተው ወደ ወለሉ ከወጡ በኋላ መልህቁ ተነሳና
ሸራዎች ተዘርግተው መርከቡ በንፋስ ኃይል ተንቀሳቀሰ፡፡ ከዚያም ወደ ኋለኛው ጫፍ ሄደው ተቀመጡና ወደ ትንሿ ደሴት መመልከታቸውን
ቀጠሉ፡፡ መጀመርያ ላይ ባህታውያኑ ይታዩ ነበር፡፡ መርከቡ እየራቀ ሲሄድ እነሱ ለዓይን እያነሱ ሄደው ትንሽቷ ደሴት ብቻ ትታይ
ጀመር፡፡ ከዚያም ደሴቲቱ ራሷ ለዐይን ርቃ ባህሩ ብቻ በጨረቃዋ ብርሃን ማንጸባረቁን ቀጠለ፡፡
ምዕመናኑ ወደ እንቅልፍ ዓለም ነጐዱና በመርከቢቷ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ አቡኑ
ብቻ መተኛት አላሰኛቸውም ነበር፡፡ ከመርከቢቷ የኋላ ጭፍ እንደተቀመጡ ደሴቲቱ ትታይ ወደነበረችበት ቦታ ፈዘው እየተመለከቱ ስለመልካሞቹ
ባህታውያኑ ምን ያህል ልባቸው በደስታ እንደተሞላ አሰቡና እነዚያን ቅን አማኞች ለመርዳትና የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር ዕድሉን
ስለሰጣቸው ፈጣሪን አመሰገኑ፡፡
አቡኑ ከተቀመጡበት ሆነው ለዐይን ወደራቀችው ደሴት በማየት ለረዥም ጊዜ
በሀሳብ ፈዘው ቀሩ፡፡ ከዚያም የጨረቃዋ ብርሃን በማዕበሉ ላይ ሥፍራ እያቀያየረ ሲያንጸባርቅ የሚያዩት ነገር ብዥ አለባቸው፡፡ ወዲያውኑ
በጨረቃዋ ፈለግ አቅጣጫ ነጭ ሆኖ የሚያንጸባርቅ ነገር ያያሉ፡፡ ወፍ ወይስ ዳክዬ ይሆን እንዲህ ነጭ ሆኖ የሚታየው? ወይንስ የትንሽ
ጀልባ ሸራ? አቡኑ ለማጣራት አፍጠው አዩ፡፡ በሀሳብም ሰጠሙ፡፡ “ባለሸራ ጀልባ ወደእኛ እየፈጠነ ነው፡፡ ግን እንዴት እንዲህ ፈጥኖ
ሊደርስብን ይችላል? አሁን ቅርብ ጊዜ እኮ በጣም ሩቅ ነበር፡፡ ይኸው
ታዲያ ከመቅጽበት እየቀረበን ነው፡፡ ደግሞም ባለሸራ ጀልባ አይደለም፡፡ ብቻ አንድ ነገር ወደእኛ እየገሰገሰ ሊደርስብን ነው፡፡”
እያሉ ከሀሳባቸው ጋር ይሟገታሉ፡፡ ምን እንደሆነ ሊያውቁት አልቻሉም፡፡ ጀልባም፣ ወፍም፣ ዓሣም አይደለም፡፡ በጣም ከመርዘሙ በስተቀር
የሰውን ቅርጽ የሚመስል ነው፡፡ እንዲያው በሰፊ ባህር መሀል ሰው ይገኛል ማለት ደግሞ የማይሆን ነው፡፡ አቡኑ ከተቀመጡበት ተነሱና
ወደ መርከቡ ኃላፊ ሄዱ፡፡
“ተመልከት፣ ያ የሚታየው ምንድነው?”
“ምን ይመስልሃል ወዳጄ? ምን ይሆን?” አቡኑ መጠየቃቸውን አላቆሙም
ነገር ግን አሁን ራሳቸው በግልጽ ሊያዩት የሚችሉት ነው፡፡
ባህታውያኑ
ግራጫ ጢማቸው ነጭ ሆኖ እያንጸባረቀ መርከቡን የቆመ በሚያስመስል ፍጥነት በባህሩ ላይ ይገሰግሱ ነበር፡፡
የመርከቡ ኃላፊ ዙርያውን አየና በድንጋጤ ደርቆ ቀረ፡፡ ከዚያም ቆቡን ወርውሮ
ከፍ ባለ ድምጽ ጮኸ፡፡
“እግዚኦ ፈጣሪዬ! ባህታውያኑ በደረቅ መሬት የሚጓዙ ይመስል በባህሩ ላይ
ወደእኛ እየተጣደፉ ነው፡፡”
ሰዎቹ የኃላፊውን ድምጽ ሰምተው ከተኙበት እየተነሱ ወደ መርከቧ የኋላ
ጫፍ በጥድፊያ ሄዱና ሁሉም አዩዋቸው፡፡ ባህታውያኑ እጅ ለእጅ ተያይዘውና ከበስተዳር ያሉት መርከቡ እንዲቆም እጃቸውን እያውለበለቡ
ይገሰግሱ ነበር፡፡ ሦስቱም እግራቸውን ሳያንቀሳቅሱ በባህሩ ላይ እንደደረቅ መሬት ይፈጥናሉ፡፡
ባህታውያኑ ከመርከቡ ሲደርሱ መርከቡ ገና አልቆመም ነበር፡፡ ከመርከቡም
ጎን ለጎን ሆነው ራሳቸውን ቀና በማድረግ በአንድነት ተናገሩ፡፡
“የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ፣ ያስተማሩንን ረሳነው፡፡ እየደጋገምን በምናጠናበት
ጊዜ አልረሳነውም ነበር፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ብናቆም ግን አንዲት ቃል ተረሳችንና ከዚያም ሁሉም ቃላት ጠፋን፡፡ አሁን ምንም
የምናስታውሰው ነገር የለምና እንደገና ያስተምሩን፡፡”
አቡኑ አማተቡና ወደባህታውያኑ አቅጣጫ ሰውነታቸውን ዘንበል አድርገው
እንዲህ አሏቸው፡፡
“በእምነታችሁ የፀናችሁ ባህታውያን ሆይ! የእናንተ የራሳችሁ ጸሎት ከፈጣሪ
ይደርሳል፡፡ እኔ እናንተን ለማስተማር ፈጽሞ የምበቃ አይደለሁም፡፡ ይልቅስ ለእኛ ለኃጢአተኞቹ ፀልዩልን፡፡”
አቡኑ ይህንን ብለው ከባህታውያኑ ፊት ከወለሉ ላይ ተደፉ፡፡ ባህታውያኑም
ዞሩና ከመጡበት አቅጣጫ በባህሩ ላይ ተጓዙ፡፡ ከዓይን በራቁበት አቅጣጫም እስከማለዳ ድረስ ብርሃን ያበራ ነበር፡፡
ተፈጸመ፡፡
What is your point?I don't get it.PS stop posting this kind of stereotype
ReplyDeleteFiction,don't downgrade your self ps
Raise the bar.
me to what is your point our salvation not based on ignorance, buy with knowlage, wisdom and power of whollyspirit.
ReplyDeleteVery fine. Keep it up!
ReplyDelete