የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ አህዝብ ሞኝነት፤
ለአይሁድም ማሰናከያ ነው፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የመስቀሉን ቃል በእንጨት
ላይ መዋልና መሰቀልን እንደተረገመ ስለሚቆጥሩት ነው፡፡(ዘዳግ.21፥23 ፤ ገላ.3፥13) ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል
ላይ በመሰቀሉ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ … ” እንደኃጢአተኛ
የተቆጠረ ሆነ፡፡(2ቆሮ.5፥21) ለግሪክ ሰዎች ደግሞ በእንጨት ላይ መሰቀል የአማልክትን ክብርና ልዕልና ዝቅ የሚያደርግና እንደድኩም
የሚያስቆጥር ስለሆነ ፈጽሞ አይቀበሉትም፡፡
ቀድሞ የጥንት ፋርሶች በኋላም ሮማውያን አንድን ወንጀለኛ በመስቀል
ላይ በመስቀል የሚቀጡት “ኦርዝሙድ” የተባለ የመሬት አምላካቸው እንዳይረክስባቸው በመጠንቀቅና ለአማልክታቸው ክብርን ለመስጠት በማሰብ
ነበር፡፡(አባ ጐርጐርዮስ(ሊቀ ጳጳስ)፤ የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 3ኛ ዕትም፤ 1991፤ አዲስ አበባ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ
ድርጅት፤ ገጽ.104)
በመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ “ፈላስፋ” የነበረው ፍሬድሪክ ኒቼ
(1844-1900) “አምላክ ሞቷል” በሚለው በክርስትና ትምህርት ላይ መሳለቁ(ተሳልቆቱ) ይታወቃል፡፡ ይህን ፈላስፋ እዚህ የመረረ
ክህደት ላይ ያደረሰው ክስተት ስለክርስቶስ ኢየሱስ ካነበበና ካወቀ በኋላ በክርስቶስ ህይወት ተቃራኒ በድኃው የሮማ ማህበረሰብ ውስጥ
ይኖሩ የነበሩትን የተቀማጠሉ መነኰሳት ፣ ቀሳውስትና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ካየ በኋላ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ “የክርስቶስ
እንደራሴ የተባለው ሊቀ ጳጳስ” ጭልጥ ባለ ልድልድ ኑሮ መዋጡንና መወረሱን በመመልከቱም ነበር፡፡
አይሁድ የተሰናከሉበት ፣ የግሪክ ሰዎች እንደሞኝነት የቆጠሩት ፣ የጥንት
ፋርስና ሮማውያን ለአማልክቶቻቸው ያደሉበት ፣ ፍሬድሪክ ኒቼ “በአምላክ አይሞትም” እና በአገልጋዮች ክፋትና ድሎት ተሰናክለው የወደቁበት የመስቀሉ ቃል ዛሬም አዕላፍ የሚሰናከሉበት ፣ ትዕልፊት የሚያሰናክሉበት መንገድ
ሆኗል፡፡
ኒቼ፤
“በክፉዎች ክፋት ተጠላልፎ” የመስቀሉን ቃል ፤ አካላዊውን ቃል ፤ አስገኚውን ቃል ፤ ሥጋ የሆነውንና ያዳነንን መካዱ አግባብነት
የለውም፡፡ ምክንያቱም የፍልስፍና ጥግ ክህደት ሳይሆን ምርምርን በጠራ አመክንዮ ማስረዳት ነውና፡፡ አይሁድ አውቀውት ሳይሆን “ደሙ
በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው የወደቁበት የማዕዘን ራስ ድንጋይ አደቀቃቸው፡፡(ማቴ.27፥25) የግሪክ ሰዎች “ልፍለፋና
የአዲስ አማልክት ወሬ” ብለው ማፌዛቸው ካለማመን አደረሳቸው፡፡(ሐዋ.17፥18 ፤32) አዎ! ይህ ብቻ አይደለም አንድ ግሪካዊ የዮሐንስን
ወንጌል አጊኝቶ ከምዕራፍ አንድ ጀምሮ ማንበብ ቢጀምርና ምዕ.1፥14 ላይ “ቃል ሥጋ ሆነ” የሚለው ላይ ቢደርስ ሁለት ዕድል ብቻ
ነው ያለው፡፡ ወይ ይህ መጽሐፍ የዕብድና የሞኝነት መጽሐፍ ነው ብሎ መወርወር ፤ አልያ በፍጹም እምነት ማመን ብቻ ነው የሚቻለው፡፡
ግና ይህን እውነት ለማመን የእምነት ልብና ከፍጥረታዊው ሰው ወደ መንፈሳዊው ሰው ማደግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም “ለፍጥረታዊ ሰው
የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልምና።” (1ቆሮ.2፥14)
ኒቼም ቢሆን እስከሞቱ ድረስ “በክርስቲያን አምላክ ደካማነት” እየተሳለቀ
ሞቷል፡፡ ኒቼ ሞቷል፤ ደካማ የተባለው ክርስቶስ ግን ዛሬም በዙፋኑ ፣ በኃይሉና በጥበቡ አለ!!!
አዎ! የመስቀሉ ቃል ለማዳን የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ኃይል መረዳት ለዘገዩ ሰዎች
ፍጹም ሞኝነት ነው፡፡ “ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና”(ሮሜ.1፥16)፡፡ የእግዚአብሔር ኃይል የተገለጠው እግዚአብሔር
በልጁ ሞት ኃጢአትን ሊቀጣ ባሰበ ጊዜ በመስቀል ላይ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መቸንከሩና መድከሙ ሰይጣንን አቅርቧል ፤ ኃይለኛው
ሰይጣን ሊታሰር(ማቴ.12፥29) “ኃይለኛው” ክርስቶስ የደከመ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እኛም ነጻ የወጣነው ፤ የሞቱትም ህያዋን የሆኑት
የእግዚአብሔር ኃይል በሆነው በክርስቶስ ሞት ነው፡፡
ይህ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው የመስቀሉ ቃል
ክርስቶስ ለአይሁድ ማሰናከያ ፣ ለአህዛብ ሞኝነት (1ቆሮ.1፥23) እንደኒቼ ላሉትም ያለመማን ምክንያት ሆኖባቸዋል፡፡
የመስቀሉ ቃል ዛሬም በብዙዎች ዘንድ ተዘንግቷል፡፡ የመስቀሉ ቃል ለአይሁድ
ብቻ አይደለም ማሰናከያ የሆነው፡፡ አይሁድ የተሰናከሉበት አንዱ ምክንያት ዕድገቱንና “ቤተሰቡን” አይተው ነው፡፡(ማቴ.13፥53-56
፤ ዮሐ.7፥15) ከገሊላ ናዝሬት “ከድኃ ቤተሰብ” የተወለደውን(ሉቃ.2፥24 ፤ 9፥58) ኢየሱስን ናቁት፡፡ “የጠራቢ ልጅ” ጥበብ አያውቅም ብለው ተሳለቁበት፡፡ ስምዖን እንደተናገረ ወደቁበት፡፡ (ሉቃ.2፥35)
ደግሞም ተሰናከሉበት፡፡
የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል የሆነውን የመስቀሉን ቃል የሞትና የትንሳኤ
ትምህርት፤ ዘር መድበው ጐሳ ለይተው የሚያስተምሩ፣ የሚያሰለጥኑ ፣
የሚቀጥሩ ፣ የሚሾሙ … የእኛ ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአንገታቸው
የወፍጮ ድንጋይ ታስሮ ወደጥልቁ ባህር (ማቴ.18፥6) ከሚጣሉ ጌታ እንዳለ “ባይወለዱ”(ማቴ.26፥24) በተሻላቸው ነበር!!!
ዛሬ በክርስቶስ ወንጌል ላይ የሚቀማጠሉ ብዙ ናቸው፡፡ የክርስቶስን የርህራሄና
የእረኝነትን ትምህርት አስተምረው ያገኙትን ህዝብ፥ ከአፉና ከኪሱ እየነጠቁ ቤታቸውን የገጠገጡ ፣ መኪና የሚያማርጡ ፣ ሰውነታቸውንና
ነፍሳቸውን “ለዕርድ የሚያሰቡ” ፣ መንኩሰውና “ለስግብግብነት ቆርበናል ብለው” ሀብት በባንክ አከማችተው ልባቸውንና አንገታቸውን
ያደነደኑ፤ ከዘማሪ እስከ ደብር አለቃ፤ ከመነኩሴ እስከ ጳጳስ ለቁጥር
ይታክታሉ፡፡ ግና ቅምጥልነት እንደሚገድል (1ጢሞ.5፥6) ፤ የገንዘብ ብዛትም ህይወት እንደማይሆን (ሉቃ.12፥15) ምነው ሞኝነት ባልመሰላቸው?! አዎ! የመስቀሉን ቃል ባለማፈር መናገርና ጮኾ
መስበክም ለዚህ አለም ሞኝነት፤ አላዋቂነትም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ኃይል በክርስቶስ ሞትና ህማም መገለጡም፤ ለብዙዎች መሰናከያ
መሆኑ ይደንቃል፡፡ የመስቀሉ ቃል በእምነት ልብ እንጂ በዕውቀት ልብ አይጎላም፤ አይረዳም፡፡
ይልቁን ሌላ ሞኝነት አለ፡፡ የዚህን አለም ጥበበኞችና ባዕለጠጎችን
ሀሳብ አጥፍቶ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የመጣውን የእግዚአብሔር
በጎ ፈቃድ ወደጎን ትቶ፤ የመዳኑንና የጸጋውን ወንጌል ሸቃቅጦ “የብዕልጥግናና
ሀብት የማግኘት ወንጌል” የሚሰብኩና የሚለፈልፉ ምንኛ ጎሰቆሉ?! ክርስቶስ የናቀውንና የተፋውን የዚህን አለም የጥበብና ባዕለጠግነትን
አሮጌ ካባ ደርቦ “ይኸው አምሮብናል!” የሚሉ ምንኛ ተራቆቱ?!
ይህ በሌሎች ዘንድ መሰናከያና ሞኝነት የሆነው የመስቀሉ ቃል ለእኛ
ለምናምንና ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ የዘላለም ሕይወታችን ነው፡፡ የመስቀሉ ቃል
እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ ለማያምኑትና ለማይድኑበት ሞኝነት፤ ለምናምንና ለምንድንበት ግን የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ነው፡፡
“ እኛ ግን ጥበብ የተባለ የተሰቀለ ክርስቶስ ነው እያልን እናስተምራለን”
(1ቆሮ.1፥18 ፤ በግርማዊ ቀዳ. ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጲያ መልካም ፈቃድ በአሜሪካ ከታተመው የ1938 ዓ.ም መጽሐፍ
ቅዱስ ከታተመ የተወሰደ፡፡)
ጌታ ይህን እውነት በልባችን ይሳል፡፡
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment