Thursday, 13 February 2014

ቃሉ “የማይሰራ አይብላ” አይልም!!! (የመጨረሻ ክፍል)


Please read in PDF - kalu yemaysera aybila ayilm

     “ኢየሩሳሌም ትምህርት ቤት እንደገባሁ ሰሞን ከተማሪዎች ጋር የደረቀ ፍግ በአካፋ እየዛቅን በሚገፋ ጋሪ ወደየአትክልቱ እንድናፈስ ታዘዝን፡፡ተማሪዎቹ የለመዱት ሥራ ስለነበር እየተዝናኑ እየተጫወቱ ይሰራሉ፡፡የክፍል አለቃዬ መጣና 'ጎባው አትሰራም እንዴ?' ቢለኝ 'እኔ ፍግ ለመዛቅ አልመጣሁም ለመማር እንጂ!' ብዬ መለስሁለት፡፡የክፍል አለቃዬ ይህንኑ ሄዶ ለዋናው አስተዳደር ነገራቸው፡፡እሳቸውም 'ተውት ግድ የለም እሱ ሥራ መስራት ካልለመደ ሀገር ስለሆነ እስኪለምድ ድረስ አትንኩት' ብለው ሲናገሩ ሰማሁ፡፡እኔም ጥቂት ደቂቃዎች ከቆየሁ በኋላ ቆጨኝና የሚገፋውን ጋሪና አካፋዬን ይዤ እንደጓደኞቼ እየተሻማሁ መስራት ጀመርሁ፡፡ከዚያ በኋላ ሥራ ህይወት መሆኑን ተማርሁና ኑሮዬን ማቅናት ቻልሁ፡፡”(ከንቲባ ገብሩ ደስታ በኢየሩሳሌም ለትምህርት ሄደው የገጠማቸውን ኮሎኔል ዳዊት ገብሩ እንደዘገቡት) ከንቲባ ገብሩ ደስታ የኢትዮጲያ ቅርስ፡፡(1985) አዲስ አበባ፣ቦሌ ማተሚያ ቤት፡፡ገጽ.22)
     በሀገራችን በተለይ የሥራ ባህልን በተመለከተ ያለው እውነት እጅግ በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ነው፡፡ከላይ በምሳሌነት የጠቀስነው የከንቲባ ገብሩ ደስታ ህይወት የጥቂቶች ሳይሆን የብዙዎች መገለጫ ነው፡፡ካለብን አስነዋሪ ስያሜዎች አንዱ “በዓለም ላይ ካሉት ፍጹም ድኃ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ መመደባችን ሳይሆን ረሀብተኞች የሚለውን አለመፋቃችን ከማሳዘን አልፎ ዛሬም የሥራ ባህላችን ቁልቁል መንደርደሩን ሥናይ ማደግ ሆይ ወዴት ነህ? ሥልጣኔ ሆይ ወዴት ተሰወርክ? የሚለው መባዘን ገና የሚያቆም አይመስልም፡፡

    በዓለም ላይ ከጥንት ጀምሮ አሰቃቂ የሥቃይና የባርነት ጊዜያትን ቢያሳልፉም ከህዝቦች ሁሉ አይሁድ የተሻለ የሥራ ባህል እንዳላቸው ይነገራል፡፡በጥንት አይሁድ አንድ ልጅ አምስት አመት ሲሞላው ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ወደተሰራው በአቅራቢው ወደሚገኝ ምኩራብ ወስደው የዕብራይስጡን የፊደል ገበታ ያስጠኑታል፡፡ከዚያም ከቶራህ ክፍል ኦሪት ዘፍጥረትን በቃሉ በማጉተምተም ያጠናዋል፡፡ሲያድግ ደግሞ የማህረሰቡ ሃይማኖት የሚጠይቀውን የሥነ ምግባር ህጎች እንዲማር፤ የተማረውንም በሙሉ እንዲጠብቅ ቃል ይገባል፡፡ልዩ ችሎታ ያላቸውም ተለይተው ወደረቢዎች(መምህራን)ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ይደረጋል፡፡
    ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የተለያዩ የሙያ ሥራዎችን በተለይ እንደድንኳን መስፋት፣ አናጺነትና ንግድን በማስተማር የሥራን ክቡርነት ገና በልጅነታቸው በልባቸው ይስላሉ፡፡የዚህ ማሳያዎች ጌታ ኢየሱስ የወጣለት አናጺ እንደነበር “አይሁድ ሲመሰክሩለት” ቅዱስ ጳውሎስም ድንኳን ሰፊ ነበር፡፡(ማቴ.13÷54)
   እኛም በጥንት ታሪክ ስንሰማና ስናይ የሥራ ባህላቸው ዓለምን ያስደመሙ አባቶችና እናቶች አሉን፡፡መጻህፍት ጽፎ ከመደጎስ እስከ በልዩ አርክቴክት ሙያ ውቅር አብያተ እምነትን መትከል፣ሀገር በቅን ከማስተዳደር እስከለሐገርና ለወገን መሰዋት የደረሱና ወንጌሉን በእውነትና በፍቅር ልብ የሰበኩ፤የናኙ ብርቅዬዎች የጠፍ ከዋክብት ያህል የተራራቁ ቢሆኑም አሉን፡፡ የፍህም ልጅ አመድ ወለደ ሆነብን እንጂ፡፡
    ዛሬ ላይ ከመንፈሳውያን አባቶች ጀምሮ ያለውን የሞተ የሥራ ባህላችንን ብናጠናው የመጀመርያና የማንክደው ምክንያታችን ሥራን በቅድስናው አለማስተማራችን ነው፡፡ታላላቅ ጉባኤያት ሲደረጉ ብዙ ጊዜ ከከተማ ከተማ ሄዶ የመካፈልና የመሳተፍ ልማድ አለኝ፡፡በተለይ “ታላላቅ” የተባሉቱ ሲሰብኩ “ታላቅ” የተባሉበትን ነገር ለማየትም ለመስማትም እሄዳለሁ፡፡ግና አፍሬ አንገት ደፍቻለሁ፡፡ጥቂት ያይደሉ ሰባክያን አንድ ከተማ ላይ ያስተማሩትን የትምህርት ርዕስና ጭብጥ በሌሎች ከተሞች ላይ ምንም አይነት የርዕስና የጭብጥ ጭማሪ ሳያደርጉበት ደጋግመው ሲስተምሩ ሳይ ሁለት ነገር ውስጤን ያቃጥለዋል፡፡
1-     ቃሉን የማያጠኑና በእውነት የማይናገሩ፤ ህይወታቸውም ምሳሌ የማይሆን ሰነፍ አገልጋዮችን ቤተ ክርስቲያን  እስከመቼ ነው ተሸክማ የምትኖረው?
2-   አማኝ ማለት አሜን እንጂ ለምን ብሎ የማይመረምር የሚነዳ መቃኞ በሬ ማለት ነውን? እላለሁ፡፡(1ዮሐ.4÷1)
     እውነት ነው ቃሉ በዘመናት የማያረጅ አዲስ ነው፤የእኛ አገልጋዮች ግን አንዱን የሚደጋግሙት ይህን አምነው አይመስለኝም፡፡በስንፍና ሟሙተውና ቀልጠው እንጂ፡፡ስለዚህም ስለስራ ጨክነው ማስተማር ከየት ይመጣላቸዋል? የቅንጦቱ ሞባይል በንስሐ ልጅ፣ ሱሪና ኮቱ “ወንጌል በተገለገሉት”፣ፍትፍትና ዳቦው በአስራት አውጪው፣ጠላና ካቲካላው ቢራ ከበኩራት አምጪው … እየተገዛና እየመጣ መልበስ፣መብላት፣መጠጣት እንጂ ለምን ትምህርት የምንስ ሥራ?
     ብዙ ጊዜ በመንግስትና በግል ተቋማትም በስብሰባ የመካፈል ሰፊ ዕድልም አለኝና እሳተፋለሁ፡፡እውነት ለመናገር እልፍ ስብሰባዎች አዲስ የትኩረት አቅጣጫ ለማስጨበጥ፣ የተሳሳተ ለማቅናትና የበረታውን ለመሸለም ሳይሆን “በግም-ገማ(ግም መቼም ይገማል፡፡ ለካ ቃሉም አያምር?!!!) እሾህ ለመጋረፍና በውኃ ቀጠነ ለመጨቃጨቅ” ብቻ ነው የሚሰባሰቡት፡፡አስር፣አስራ አምስት ቀን … ስብሰባ ተቀምጦ ጠብ የማይል ነገር ይዞ አለመውጣት እንዴት ያሳዝናል?
     ለዚህ ሁሉ ስህተትና ውድቀት ፣ለትውልድ ግራ መጋባት ፣በስደትና በባርነት መኖር ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያውን ድርሻ በመውሰድ የወሬ ባህልን በመንቀል የሥራ ባህልን ልትተከል ይገባታል፡፡“ደጃችንን ካጸዳን ሀገር ትጸዳለች” እንዲባል ቤተ ክርስቲያንም ራስዋንና ቤቷን ከማስተካከል ልትጀምር ይገባል፡፡እኛም ከተኛንበት የስንፍና እንቅልፍ ልንነቃ ይገባናል፡፡በእርግጥም የሚያወሩ እንጂ ሊሰሩ የማይወዱ እጆች ሊመገቡ አይገባቸውም፡፡    
     እንደጥንት የግሪክ አማልክት አማኞች ክቡርና ወራዳ፣ታላቅና ታናሽ አምላክ፣ … እንደሚሉት  የሥራ ታላቅና ታናሽ ባናወጣ፤ለትንሹ የሥራ መክሊታችን ታምነን ብንገኝ በሚበዛው በረከት እንባረካለን፡፡አልያ ግን በቅዠት እናልማለን እንጂ ልምላሜና ማደግ አይሆንልንም፡፡ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሙሽራሽ ፍጥረትን ፈጥሮ የሚመግብ ትጉህ ሠራተኛ፤ አንቺንም በውድ ፍቅር ያፈቀረ ታማኝ ባልሽ ነውና በሥራ መገዛትና በፊቱ መንጓደድ አሁን ይሁንልሽ፡፡አብረሽው ለመስራትና የወንጌሉን ሥራ ለማድረስም የምትተጊ ሁኚ፡፡እርሱ ሁሌም ካንቺ ጋር ታማኝ ሠራተኛ ነውና፡፡(ማር.16÷20)
ጌታ ሥራን የማይንቅና በሥራ የማረፍን ልብ ይስጠን፡፡አሜን፡፡
   
       

No comments:

Post a Comment