Friday 7 February 2014

በምዕ.1÷8 ታዘዙ በምዕ.8÷1 ፈጸመው!!!




ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሰማያት ሲያርግ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠው ትልቁ ተልዕኮ "በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡" የሚለው ነው፡፡ይህን የምስክርነት አገልግሎት በእርግጥ ያለመንፈስ ቅዱስ ምሪትና ጉልበት ለመፈጸም መቃተት የማይታሰብ ህልም ነው፡፡የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌሉ አገልግሎት ትልቅ የጸሎት ዝግጅት ነበራት፡፡አገልጋይ ደቀ መዛሙርትን ለመላክ ብቻ የምትጸልይም አልነበረችም፤ከላከችም በኋላ የኋላ ደጀን ሆና በጸሎት የምትተጋም ነበረች፡፡
         መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ትልቁ የአገልግሎት ሥፍራ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ብቻ አልነበሩም፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ገና በቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን መንፈስ ቅዱስ እንደወረደ በሰበከው አጭር ስብከት ሦስት ሺህ አማኞችን ለክርስቶስ ማረከ፡፡ስብከቱ የቃል ጋጋታ፣ማባበል፣ፍርሃትያልነበረበት የመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ጥበብ የነበረበት ነውና ገና ሲናገር ሰዎችን ለእውነት የሚገዛ ነበር፡፡አገልግሎታቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚቆዩበት ዘመን ርዝማኔ እንጂ ፍሬንና አማኝን ከማፍራት አንጻር የማይመዝኑ ሰዎች በዚህ ታሪክ ራሳቸውን ቢያዩ መልካም ነው፡፡አገልግሎት ዕድሜ መቁጠር ሳይሆን ባለችን ጥቂትም ትሁን ረዥም ዕድሜ ያፈራነው ፍሬ የሚመዘንበት ነው፡፡ጴጥሮስ በጥቂት ደቂቃ ስብከት ሦስት ሺህ ሰው ከማረከ ዛሬ ሦስት ሺህ ስብከት ሰብከንም ሆነ ተሰብከን ያላፈራንና እልኸኛ የሆንን ጥቂት አይደለንም፡፡
        በአንድ ሌላ ቀን ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ወደመቅደስ ሲወጡ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ አንካሳ በመሆኑና ጤናውን በማጣቱ ሲለምን የነበረውን ሰው "በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም ተነስቶ እንዲመላለስ" በሥልጣን ቃል ቅዱስ ጴጥሮስ ተናግሮ እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጸንቶ ሙሉና ፍጹም ጤናው ተመልሶለታል፡፡ከዚህ ተአምራት  የተነሳም አምስት ሺህ ነፍሳት ተጨምረዋል፡፡ላላመኑ ሰዎች ተአምራት ትልቅ የመመለሻና ወደወንጌል ፊታቸውን ዘወር እንዲያደርጉ የሚጣራ ነው፡፡ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ለወንጌል ተልዕኮ ሲልክ በፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጥቶ ነው፡፡(ማር.16÷17)፡፡ያላመኑ ሰዎች እምነታቸውን ብዙ ጊዜ የሚጥሉት ፍጥረታውያን በሆኑ ነገሮችና ጣኦታት ላይ ነው፡፡የደቀ መዛሙርቱ ፍጥረትን በጌታ ቃል ሥልጣን ማዘዝ ደግሞ ፍጥረታትን የሚያሸንፍና ከፍጥረታት በላይ ሌላ የበላይ እንዳለ እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡በእርግጥም ምልክትና ተአምራት ላላመኑት ነው፡፡ላመኑት ግን የምክሩ ቃልና የመዳኑ ወንጌል ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡(1ቆሮ.14÷22)፡፡ዛሬ ግን ይህ ነገር ተገልብጦ "ያመኑት" ተአምራት ፍለጋ ሲንከራተቱ ያላመኑቱ ግን የቃሉን ደጅ የሚከፍትላቸው ናፍቀው ሲቃትቱ እናያለን፡፡
      በቃሉ ምስክርነት ሦስት ሺህ ነፍሳትን በድንቅ ተአምራቱ ደግሞ አምስት ሺህ ነፍሳት በአጠቃላይ ስምንት ሺህ ነፍሳት አመኑ፡፡ህይወት ያላት ቤተ ክርስቲያን መገለጫዋ በሁለቱም መንገድ ስታገለግል መታየቷ ነው፡፡የዛሬዎቹ አብዛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የክርስቶስን ወንጌል ሲመሰክሩ እንኳን ልብ ገዝተው ሊያሳምኑ ከህይወታቸው ብልሹነት የተነሳ የሞት ሽታ ሲሆኑ በግልጥ ይታያል፡፡ወጭትን ብቻ እያጠሩ ወንጌልን ለመስበክ መሮጥ ፈሪሳዊነት ነው፡፡(ማቴ.23÷25)ቃሉን ለመግለጥ በመንፈስ ቅዱስ እሳት ልንነካ ይገባናል፡፡እንዲሁም የናዝሬቱ ኢየሱስ በሚለው በስሙ ስልጣን በደዌያትና በፍጥረታት ሁሉ ላይ ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ሥልጣንዋን ልትገልጥ ይገባታል፡፡ዛሬ ዛሬ ላይ ከሚታዩት ታላላቅ እንከኖች አንዱ መናፍስትንና ደዌያትን በአጋንንትና በጥንቆላ የሚያወጡ ከምንጊዜውም ይልቅ እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው፡፡  ስለዚህም መንፈስን ሁሉ በቃሉ ሚዛንነት ልንመዝን ይገባናል ማለት ነው፡፡
     በኢየሩሳሌም ስምንት ሺህ ያመኑ ነፍሳት ተቀምጠዋል፡፡ለሰባቱ ዲያቆናት መመረጥ ምክንያት የሆነው የደቀ መዛሙርቱ መብዛት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው የተነሳው ማንጎራጎርና የማዕድ አገልግሎት ነበር፡፡(ሐዋ.6÷1-3) ይህን መልስ ለመመለስ በእስጢፋኖስ የሚመሩ አገልጋዮች ተመርጠው ተሾሙ፡፡ ስለተሾመላቸው ተደላድለው ተቀመጡ፡፡ጌታ በሐዋ.1÷8 ላይ ያዘዛቸውን ትልቁን የተልእኮ ትዕዛዝ ዘነጉት፡፡ወንድሞች ለአምልኮ በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው፡፡ምስክርነት የሌለበት መሰባሰብ ግን ለቤተ ክርስቲያን አደገኛነቱ እንጂ ጥቅሙ አያመዝንም፡፡
      ቤተ ክርስቲያን ትልቁን አገልግሎቷን ረስታለችና የሚያነቃ አስፈልጓታል፡፡ስለዚህም ስምንት ሺህ አማኞች በነበሩባት በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ስደት ተነሳ፡፡የስደቱ ምክንያት የእስጢፋኖስ በድንጋይ መወገር ነበር፡፡መሪው ተመቷልና አማኞቹ ተበተኑ፡፡በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን በመከራ መንቃት የለባትም፤በፍቅር የታዘዘችውን በሠላም ዘመንና በፍቅር ልትፈጽመው ይገባታል፡፡በህመምና በቁጭት ከማገልገል በፍቅር ከህሊና ጋር ማገልገል ይበልጣል፡፡ቤተ ክርስቲያን የነቃችው ትልቁን ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን በማጣት ነው፡፡ዛሬ ላይም አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮቻቸውን እየሰዉ ባይነቁ መልካም በሆነላቸው!!!
    የጌታ ቃል እውነት ነውና ከመፈጸም የሚያግደው ምንም አይነት ኃይልና ሁኔታ የለም፡፡ስለዚህም በሐዋ.1÷8 ላይ የተነገረው ቃል በሐዋ.8÷1 ላይ ተፈጸመ፡፡የተከማቹ ስምነት ሺህ አማኞች "ሁሉምወደይሁዳና ወደሰማርያ አገሮች ተበተኑ  … የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ፡፡"(ሐዋ.8÷14)፡፡ቤተ ክርስቲያን መቼም መርሳት የሌለባት ነገር ቢኖር ቃሉን በእውነትና በፍቅር መስበክን ነው፡፡ያመኑ ነፍሳት ሁሉ ከተሰጣቸው ሥልጣንም ዋናው ቃሉን እየዞሩ መስበክ ነው፡፡ብዙዎቻችን ዞረን ለምናገኛቸው ባልንጀሮቻችን ቃሉን ከመናገርና ከመመስከር እንዲሁም ከመወያየት ይልቅ የማይረባ ፌዝና ወሬ ስናወራ ውለን እንለያያለን፡፡
      የተበተኑት ሁሉ እስከይሁዳና ሰማርያ ተበትነው ቃሉን በመስበክ ዞረዋል፡፡እውነት እንናገር ከተባለ ቤተ ክርስቲያን አስፈሪና ከባድ የደወል ድምጽ እየሰማች ላለመንቃት የወሰነች ይመስላል፡፡ጌታ ስምንት ሺህ ያመኑ ነፍሳት ተሟሙቀው እንዲቀመጡ አልወደደም፡፡ይሁዳ፣ሰማርያና የአህዛብ ምድሮችም የቃሉ ምስክርነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ዛሬ እንኳን ጎረቤት ሀገር ሶማሊያና ጅቡቲ  ሄደን ወንጌሉን ልንመሰክር ቀርቶ በሀገር ቤት የቅድስና ህይወት የሚያፈሩ አማኞችን ማየትና ያለንን የአማኝ ቁጥር ማስከበር ብርቅ ሆኖብናል፡፡የጌታ ሀሳቡ ኢትዮጲያ ብቻ አይደለችም፤አለሙ ሁሉ ያምንና ይድን ዘንድ እንጂ፡፡እንደኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በህመም ከመታዘዝ በፍቅር መታዘዝ ይሻለናል፡፡ቤተ ክርስቲያን ድምጿን እስከሩቅ ሀገር ለማሰማት ከዛሬ የተሻለ ጊዜ የላትምና እንዲህ እንላለን፦
ሙሽራይቱ ሆይ! እስከይሁዳ፣ሰማርያና የምድር ዳር ድረስ ከአፍሪካ እስከአውሮፓና ከአውስተረሊያ እስከኤስያ ለመድረስና ዞረሽ ስለሙሽራሽ ለመናገር ፍጠኚ!!!!
ጸጋው ይቆየን፡፡አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment