Monday, 10 February 2014

የነነዌ ንስሐ (ዮና.3÷5-9)


Please read in PDF :- yeNenewe nisiha

        የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ።ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥እንዲህም አለ፦ ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፡፡ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ።እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”(ዮና.3÷5-9)፡፡
      እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን የትድግና ሥራውን ለአህዛብም እንዲናገሩ ነቢያትን አዟል፡፡እግዚአብሔር በቤቱ ስላሉት ብቻ አይጨነቅም፡፡በሩቅ ያሉ እስኪሰሙ ድረስም ሳያቋርጥ በፉጨት ድምጽ ይጣራል፡፡በቀደመው ዘመን ኤልያስና ኤልሳዕ (1ነገ.17÷24፤2ነገ.8÷1-17)በኋላም እነአሞጽ ከይሁዳ ውጪ ለእስራኤልና ለአህዛብ የእግዚአብሔርን የትድግና ሥራ የተናገሩ ነቢያት ናቸው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእስራኤል ውጪ ወዳሉ ከተሞችና ሀገሮች እየሄደ ያስተምር ነበር፡፡መድኃኒቱ ጌታ “እምነትሽ ታላቅ ነው፤እምነትህ ታላቅ ነው፡፡”(ማቴ.15÷28፤ሉቃ.7÷9) ያላቸው ሁለቱ ሰዎች የተገኙት ኪዳን ከተቀበሉትና መቅደስ ከነበራቸው ህዝቦች መካከል ሳይሆን ከአህዛብ ወገኖች እንደሆነ ቃሉ ይመሰክራል፡፡
      አገልግሎታችን የራቁትን መቅረብ ካልቻለና ከመቅደስ እስከአውደ ምህረት ብቻ ከሆነ የጌታ ፈቃዱ እንዲህ አይደለምና ዳግም ልናርመውና ልናስተካክለው ይገባናል፡፡ ብዙውን ጊዜ በቤቱ ብቻ ስላለን የምንመካ ጥቂት አይደለንም፡፡ጽሁፎች ፌስቡክ ላይ ሲለቀቁ የሚሰጡ አስተያየቶችን  አያለሁ፡፡ የሚደንቀው ነገር አስተያየቱን የሚሰጡት ጥላቻን የማያልፉ ፣ቅንነት የጎደላቸው ፣የሌላውን ሰው እምነትና አመለካከት የሚያጥላሉ “የስም ክርስቲያኖች” መሆናቸውን ሳይ ለሌላው የተወደደ አክብሮት ያላቸውን ክርስቲያኖች ያልሆኑ ወገኖቼን አከብራቸዋለሁ፡፡
     ጌታ እግዚአብሔር ጭከናና ዝርፊያ፣አመንዝራነትና ጥንቆላ፣በንግድ ማጭበርበር የምትበዘብዘዋን እንዲሁም በእርሱ ላይ በክፋት የማታሴረውን ታላቂቱን የአሶርን ከተማ ነነዌን (ናሆ.1÷11፤2÷12፤3÷1፡19፤3÷16) እንዲሁ ሊተዋት አልወደደም፡፡ነዋሪዎቿ አህዛብ ፤ሥራዋ ደግሞ እንደሰዶምና ገሞራ ክፉ መንገድና አመጽ ቢሆንም (ዮና.3÷8-10) እግዚአብሔር ግን ወደዚህች ከተማ ታላቁን ነቢይ ዮናስን ላከው፡፡

    መድኃኒት ለበሽተኛ እንዲያስፈልግ ቃሉ የሚያሰፈልጋቸው ከሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ለሚያምኑ ነው፡፡በነነዌ ከተማ የነበሩ ኃጢአቶች ዛሬም ምድራችንን የሚያስጨንቁ ናቸው፡፡ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ በንግድ ማጭበርበር “ክርስቲያን ነን” የሚሉ ሳይቀሩ የተያያዙት ሥራ ነው፡፡ስኳር ላይ አሸዋ ፣በርበሬ ላይ ቀይ አፈር፣ቅቤ ላይ ሙዝ … ትርፍ ለማግኘት እየሳሱ የድኃውን ቤት የሚበዘብዙ ብዙ ናቸው ፤እግዚአብሔር ግን እንዲህ ያሉትን ቤታቸውን ያውካል፡፡(ምሳ.15÷27) በንግዱ አለም ሌላው አጸያፊ ነገር አባይ ሚዛን ነው፡፡ኪሎ እየሰረቁ የሚሸጡና የሚገዙቱ ከሚያገኙት ትርፍ ይልቅ በሀገር የሚያመጡት መርገም ተከፍሎ የማያልቅ ነው፡፡(ምሳ.11÷1) ከዚህ የተነሳ እግዚአብሔር ፍጻሜያቸውን መራራ እንደሚያደርገውም ተናግሯል፡፡(አሞ.8÷5-11)
     በዚህ መንገድ የሚመጣውም ገንዘብ በአስራትና በኩራት መልክ ወደእግዚአብሔር ጉባኤ ቢመጣ ያረክስ እንደሆን እንጂ የሚረባ ነገር የለውም፡፡ሌላው በነነዌ የገነነው ኃጢአት ጋለሞታነትና አመንዝራነት ነው፡፡(ናሆ.3÷4) የዝሙት ርኩሰት የሥጋን ፍላጎት በተለየ መንገድ ያረካ ይሆናል፤ነገር ግን በገዛ አካላችን ላይ ኃጢአትን እንሰራለንና ቅዱሱን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ሰውነታችንን እናረክሳለን፡፡(1ቆሮ.6÷18) ዛሬ ከገዳም እስከከተማ ፣ከሆቴል እስከቤት ፣ከትምህርት ቤት እስከማረሚያ ቤት ፣ከዩንቨርሲቲ እስከመስሪያ ቤቶች፣ከመጽሔት እስከፊልሞቻችን … እየተሰሩ ያሉትን ዝሙትና ግልሙትና ላየ የእግዚአብሔርን ቁጣ በኃጢአት ደጅ የምንጠና መሆናችንን ያሳብቃል፡፡
     እኒህና ሌሎች ኃጢአቶች በገነኑባትና “ክፋትዋ ወደፊቱ በወጣባት” በነነዌ ሄዶ እንዲሰብክ የአማቴ ልጅ ወደእርስዋ ተላከ፡፡(ዮና.1÷1) ዮናስ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለህዝቡ ሳስቶና ሐሰተኛ ላለመባል ለክብሩ ተቆጭቶ” አለመታዘዝን መርጦ ወደሌላ መንገድ ወደተርሴስ ሄደ፡፡ከነቢዩ የጠፋው ቅንነት ከአህዛብ መንገደኞች ተገኝቶ በመርከብ ላይታዘዝ የሄደው ዮናስ በባህር ልዩ መንገድ በአሳ አንበሪ ሆድ ተጓጉዞ ወደነነዌ ደረሰ፡፡ዮናስ ወደነነዌ ቢደርስም በውስጡ ግን ደስተኛ አልነበረም፡፡
    ጌታም “የምነግርህን ስበክላት አለው” ነገር ግን ዮናስ የእግዚአብሔርን መልዕክት አቅራቢ የነቢይነቱን አገልግሎት ችላ ብሎ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ የታዘዘ ቢመስልም የነነዌ ህዝቦች እንዲጠፉ ይፈልግ ነበረ፡፡(ዮና.3÷3፤4÷1)ጌታ ግን የኃጢአተኛውን መጥፋት አይወድድም፡፡ (ህዝ.3÷18፤18÷23)ዮናስ በልቡ እንዲድኑ ባልወደደ መጠን ለከተማይቱ ገብቶ ሰበከላት፡፡በነነዌ የእግዚአብሔር ቁጣ እንደተቆረጠ ጮኾ ተናገረ፡፡
       ነነዌ በዮናስ ስብከት በእግዚአብሔር አመነች፤ከታላቁ እስከታናሹም ይጾም ዘንድ ጾምን አወጀች፡፡ስለኃጢአተኝነቷ ምንም ምክንያት አላቀረበችም፡፡አህዛባዊቷ ከተማ ታላቅ እምነት ተገኘባት፡፡በተቆረጠና በተከተተ ዕድሜዋ ራስዋን ለንስሐ አዘጋጀች፡፡ምህረትና ይቅርታን አብዝታ ወዳለችና እንሰሳት እንኳ ሳይቀሩ እንዲጾሙ አወጀች፡፡ንስሐ ገብተን ለመጾም ምክንያተኞች አንሁን፡፡የዛሬው ድንበር አልባ ክፋታችንን ትላንት በነበሩት ትውልዶች አናመካኝ፡፡ አመንዝራነታችንን፣ ዘፋኝነታችንን ፣አባይ ሚዛን የበዛበት ንግዳችንን፣ጋለሞታነታችንን፣በዘረኝነት መከፋፈላችንን፣ በክፉ ምኞት መንደዳችንን … ለሌላ ሳይሆን በንስሐ መንፈስ ለራሳችን እንናዘዘው፤ በደለኝነታችንን አምነን ወደፊቱ እንምጣ፡፡
    ነነዌ ፊቷን በፊቱ አዋረደች፤ንጉስ ከመኳንንቱ ጋር ዝቅ አለ፤የአመንዝራነቱና የዝሙቱ ጌጥ ልብስ በማቅ ተከደነ፡፡ሁሉ ከግፍና ከአመጹ ከክፉ መንገዱም ተመለሰ፡፡በንስሐ ልብ ጾመዋልና በሦስት ቀን የጸሎትና የጾም አዋጅ እግዚአብሔር ሊያመጣ ያለውን ቁጣ መለሰ፡፡ያለንስሐና የኃጢአት ኑዛዜ የሚሆን ጾም ከምግብ አድማና ከረሃብ የዘለለ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ጾማችን ከኃጢአትና መንፈስን ከሚያረክስ በደል መከልከል እንጂ ከመብልና መጠጥ የመከልከል ልማድ ብቻ ሊሆን አይገባውም፡፡
   አዎ! በብዙ ነውርና በደል ተይዘናልና ጾምና ጸሎት ያስፈልገናል፤ጾማችን ግን ለምን እንደምንጾም ርዕስ፣ንስሐና የኃጢአት ኑዛዜ ይቅርታም ሊኖረው ይገባል፡፡የነነዌ ንስሐ መልስ ያገኘው አምነው ከልብ ኃጢአትን ጠልተው በመመለሳቸው ነው፡፡እውነት የጌታን ምህረትና ይቅርታ ከወወድን ቀድመን ምንም የኃጢአት ምክንያተኝነት ሳናቀርብ በመታዘዝ ንስሐ እንግባ፡፡
ጌታ ጾማችንን በምህረቱ ይቀድስልን፡፡አሜን፡፡
    
        
   
 


4 comments:

  1. dibora elias kemal10 February 2014 at 05:29

    አሜን ቃለሕይወት ያሰማልን ተባረክ!!!

    ReplyDelete
  2. Be blessed brother

    ReplyDelete
  3. egziabehere yibarkehe. teru sehuf new.

    ReplyDelete
  4. grum meleekit..biblical....God bless you!!!

    ReplyDelete