Tuesday 25 February 2014

ከሰማይ የወረደው (ዮሐ.3÷13)



ያለንበት ጊዜው የአዋጅ ጾም ወቅት ነው፡፡የጾሙ ቀዳሚው ሳምንት ስያሜ ደግሞ ዘወረደ፡፡ቅዱስ ያሬድ የጌታን የጾም ወራት ሳምንታትን በሥያሜ ከፋፍሎ ከጌታ ትምህርትና ህይወት ጋር ቃኝቶ እንድንገለገልበት አደላድሎ አስቀምጦታል፡፡ጾሙ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ከስያሜው ጋር ፍጹም ተዛምዶ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባትና ዜማዎች ይሰበካሉ፡፡አሁን ላለንበት ሳምንት ከስያሜው ጋር የሚስማማ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በርዕሳችን የጠቀስነው ነው፡፡
     ኒቆዲሞስ የሰማው ነገር እጅግ ግር አሰኝቶታል፡፡የአይሁድ አለቃና የእስራኤል መምህር ቢሆንም አሁን እየሰማ ላለው ትምህርት እንግዳ ነው፡፡መንፈሳዊ ለመሆን መሰረቱ ህልቅናና ሥልጣን ቢሆን ኖሮ ኒቆዲሞስ ያን ያህል ግራ ባልተጋባ ነበር፡፡ዳግም መወለድ ለሥጋ አዕምሮና ለዚህ ዓለም ማስተዋል የሚገባ(የሚረዳ) አይደለም፡፡ክርስቲያን ከማመን ይልቅ በማየት የሚመላለስ ከሆነ ከአለማውያን ይበልጥ ይዝላል፡፡ብፅዕና በማመን እንጂ በማየት አይደለምና፡፡(ዮሐ.20÷29)
   የሥጋ አይናችን የዚህ ዓለም ብርሃን (ፀሀይ፣ጨረቃ፣መብራት …) ካልተዋሃደው ማየት አይችልም፡፡ በተዋሐደው ጊዜ ግን በዚህ አለም ብርሃን የዚህን አለም ነገር ያያል፡፡ መንፈሳዊውን ዓለም በማመን ለማየት ከዚህ ዓለም ያልሆነ ብርሃን ያስፈልገናል፡፡ሰማያዊውን ዓለም የምናየው ከዚህ ዓለም ባልሆነ ብርሃን ነውና፡፡አልያ ግን “ማየት ማመን ነው” የሚለው አባባል “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?” የሚለውን ኒቆዲሞሳዊ ጥያቄ አይመልስም፡፡ የእግዚአብሔር ብርሃንነት ከፍሎ አያሳይም፡፡ብርሃኑ ፍጹም ነውና አጮልቆ ወይም በጨረፍታ አያይም፡፡“በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን” እንዲል፡፡(መዝ.35(36)÷9)

    ከሰማይ የወረደውን ጌታ ያለእርሱ እርሱን ማወቅ አይቻልም፡፡እግዚአብሔርን ያለእግዚአብሔር ማወቅ ከባድና ፈጽሞ የማይቻል ነው፡፡ክርስቶስን ብዙዎች ያለመቀበላቸውና ያለማመናቸው ምስጢር ያለእርሱ እርሱን መረዳት ስለሚሹ ነው፡፡ “እናምነዋለን” የሚሉቱ እንኳ ከእርሱ ይልቅ የሚሰሙት ሌላ የራሳቸው “አማልክት” አሏቸው፡፡ ጌታ ራሱ አይሁድን እንዲህ አለ “እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።” (ዮሐ.5÷43) ሰዎች እርሱን ለመቀበል የተቸገሩት ያኔም አሁንም ነው፡፡ሰዎች በራሱ ስም ክርስቶስን ሳይናገር የሚመጣውን በደስታ የሚቀበሉት ያኔም አሁንም ነው፡፡
      በእርግጥ የእስራኤሉ መምህር ኒቆዲሞስ ይህን መዘንጋት አልነበረበትም፤ ግና ዘንግቶታል፡፡ ሰዎች የወር ደመወዛቸውንና የቀን ምግባቸውን በምንም አይነት ተአምር አይዘነጉትም፤ ከዚህ ይልቅ ግን መዘንጋት የሌለብን ነገር ሰማያዊውንና ዘላለማዊውን ነገር ነው፡፡ ከሰማይም ከወረደው በቀር በሥጋና በደም የተካፈለን(ዕብ.2÷14)፣ በድካማችን የሚራራልን ሊቀ ካህናት(ዕብ.4÷15)፣ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር የሆነንና መንድሞቼ ሲለን ያላፈረብን(ሮሜ.8÷29)፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ የሆነን(ኤፌ.2÷20)፣ ስለእኛ የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገና ለውርደት ሞት የታዘዘ(ፊሊ.2÷8)፣ የሃይማኖታችን ሐዋርያ(ዕብ.3÷1)፣ የፊታችንን ቀድሞ ያየልንና የሚያይልን ነቢይ(ዮሐ.9÷17)፣ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው(ማቴ.1÷21)፣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ የምናየው ጻድቅ ንጉሳችን (ዕብ.2÷9) … ከሰማይ ከወረደው በቀር ሌላ ማንም ለእኛ የለንም፡፡  
        እርሱ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ በክብሩና በግርማው ወደእኛ የመጣ ብቻ አይደለም፤ በክብሩና በግርማውም ከእርሱ በቀር ወደሰማይም የወጣ የለም፡፡እርሱ አሁንም በከበረ ተዋህዶ በሰማይ የሚኖር የሰው ልጅ ነው፡፡ እርሱ ሰው የሆነው ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ነው፡፡እርሱ ወደእኛ በመምጣቱ እኛ ወደአባቱ መንግስት በክብር ያለማፈር ገብተናል፡፡
     የሰማዩ ደጅ ከሰማይ የወረደውን ካላመንን በቀር ፍጹም ዝግ ነው፡፡እርሱ የወረደው አምነን እንድንበት ዘንድ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ዳግመኛ መወለድን አታድንቅ ተብሏል(ዮሐ.3÷7)ምክንያቱም መዳናችንና ዳግም መወለዳችን የድምፁ መሰማት እንጂ ከወዴት እንደመጣ እንደማይታወቀው ነፋስ ነውና፡፡ ነፋስ በሥራው ይሰማል፤ይታያል፡፡ አመጣጡ ግን እንዴት እንደሆነ እንደማይታወቅ ከሰማይ ከወረደው የተወለድን እኛም መወለዳችንን መንፈሱ ከውስጣችን እየመሰከረ በሥራ ስንተረጉመው እናያለን እንጂ እንዴት እንደተወለድን አናውቀውም!!! በተመስጦ ከማድነቅ በቀር!!!
   በእርግጥም ይህ ነገር ይደንቃል! እናደንቅም ዘንድ ይገባናል፡፡ ብርሃን ነው ያለእርሱ ሰማያዊውን ነገር አናይም፡፡ከሰማይ የወረደው የህይወት መሠረትና ራስ ነው፡፡ የፍጥረት መፈጠርና መዳናችን ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ መዳናችንም የፍጥረት መፈጠርም እንኳ ያለእርሱ ፈጽሞ አልሆነም፡፡ ይህንም ፈጽሞ ልናደንቅ ይገባናል፡፡ ትውልድ ሆይ! ይገባዋልና ይህን በሁሉ ሊያድነን የተገለጠውንና ከሰማይ የወረደውን ጌታ እናድንቅ!!!
       

4 comments: