Saturday, 28 September 2013

ከሁሉ በፊት

በአለማችን ላይ እጅግ ታላላቅ ከሆኑ ችግሮች መካከል የመሪ እጦት የቀዳሚነቱን ሥፍራ ከሚይዙት አንዱ ነው፡፡  አለቃነት (አለ-ዕቃ ከመሆን ይሰውራችሁና!) ሁሉም የሚመኘውና አብዛኛው ሆኖ ቢያገኘው የሚደሰትበት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ወደብዙ ቢሮዎች ጎራ ያልን እንደሆነ ቅን ፍትህና መፍትሔ ሳይሆን በቅጥ ያጣ የጉበኝነት አዘቅት ውስጥ የተዋጠን አሰራር አይተን ለመትፋት የሰው ምክር አንሻም፡፡
      መሪነትን በተመለከተ ትልቁ አብነት ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ በምሪቱና በመግቦቱ ውስጥ አደላዳይ ሆኖ ለጻድቁና ለኃጥዑ እኩል ፀሐይ ዝናብና ነፋስን … ይሰጣል፡፡እውነተኛ መሪ ነውና ሳያበላልጥ ፍጥረቱን እኩል ይወዳል፡፡ከተፈጥሮ እውቀት እንኳ አንዳች ሳያጓድል ጥበብንና ማስተዋልን አብዝቶ ያጎናጽፈዋል፡፡
      የተረጋጋና ሰላማዊ ሥርወ መንግስትን መመስረት የሚቻለው መሪዎች ለተፈጥሮ ህግና ለህሊናቸው መገዛት እንዲችሉ ሲቀረጹ ነው፡፡የቅን ፈራጅ መንግስት መሰረቱ ቅን መሪዎች ናቸው፡፡ መሪዎች ለጉበኝነትና ለሴሰኝነት ዙፋናቸውን አሳልፈው በሰጡ ቁጥር  አጋንንት የጨበጡትን በትር በመጠቀም ህዝብን ያስጨንቃሉ ድኻ አደጉንም ይበድላሉ፡፡
      መልካምና ቅን መሪዎች ያመኑ ክርስቲያን ባይሆኑ እንኳ ለተፈጥሮ ህግና ለህሊናቸው የታመኑ ከሆኑ በመልካም ስብዕና ታግዘው  ለህዝቡ የሚሆነውን ነገር አሻግረው ቀድመው ያዩለታል፡፡ከሥጋ ድካሙም ያሳርፉታል፡፡ እነማህተመ ጋንዲ ክርስቲያን አልነበሩም ነገር ግን ክርስቲያን ነን ብለው ህዝብና ወገናቸውን በትዕዛዝ ከማረድ እስከማሳረድ ከደረሱ ከሐገራችንና ከአለማችን መሪዎች በተወደደ ስብዕና እጅግ የላቁ ተወዳጆች ነበሩ፡፡


     ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁን ተወዳጁን ጢሞቴዎስ ሲመክረው እንዲህ አለው፦
" እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።  "(1ጢሞ. 2 ÷1-4)
  
      ዛሬ መሪዎችን ለምንጠላና ለምንረግም ሰዎች ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር ወይ እብደት ወይ ከባድ መናፍቅነት መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው "ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። " እያለ ነው ያለው፡፡ በጭካኔያቸውና በአረመኔነታቸው ወደር ላልተገኘላቸው ለሮማ ነገስታት ለነኔሮን ቄሳር (እርሱንና ቅዱስ ጴጥሮስን ላስገደለ)፣ ለነድምጥያኖስ (ዮሐንስን በፈላ ዘይት ቀቅሎ ከፍጥሞ ደሴት ላጋዘው) እና ለሌሎችም ነበር ከሁሉ በፊት እንዲጸልዩ የመከረው፡፡(አስተዋይ መሪ ሐዋርያ!)
        ይህ የጌታ መንፈስ ቅዱስ ብርሐን የበራለት ብርቱ ሐዋርያ በጣም እጅግ በጣም ትክክል ነው፡፡መሪ የተሾመበትን ህዝብ የማገልገል ሥራውን በሚገባ እንዲወጣና ምሪቱ ከአሳቹ ሰይጣን እንዳይሆን ያመኑቱ ቅጥሩንና ዙፋኑን በጸሎት ሊያጥሩለት ከሁሉ በፊት ይገባቸዋል፡፡ምክንያቱም እነርሱ " ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት ፣በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ የተላኩ" ናቸውና፡፡በፍቅርና በአክብሮት ለሚመሩን መሪዎች (ጳጳሳት፣ ካህናት፣ካቢኔዎች፣ሚኒስትሮች፣ ዳኞች፣ ፖሊሶች፣ ሐገር ሽማግሌዎች፣ ወላጆች፣ መምህራኖች፣ መጋቢዎች፣ ሰባኪዎች፣…)በመታዘዝ ልንገዛላቸውና በጸሎትም ልናስባቸው ይገባናል፡፡
       ዛሬ ላይ ቆሞ ቤተ ክርስቲያንንና ትውልዱን ላስተዋለ ግን ከማሳዘን አልፎ የሚያስፈራ ነገር እናያለን፡፡ትውልዱ ስሙን ጠርቶ ሊጸልይለት የተጠየፈውን መሪ ሊሰድበው አፉን ሲከፍት ማየት ምን አይነት ውለታ ቢስ ትውልድ ገጠመን? ያሰኛል፡፡መሪ መልካም ባያደርግ መኖሩ ብቻ እንደሚጠቅም መሪዋን ለጥቂት ቀናት በማጣቷ ሩዋንዳ የደረሰባትን ዘግናኝ  እልቂት በማየት መማሩ መልካም ነው፡፡መልካም እንዲገጥመው ያልተመኘንለትንና ያልጸለይንለትን መሪ መሳደብን ማን ይሆን ያስተማረን?
      በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያን የሞቱ ነገስታትን ስም እያነሳች እየጸለየች በህይወት ያሉትንና እየመሩ ያሉትን መሪዎች ስማቸውን አንስታ ላለመጸለይ ዝምታን መምረጧ ምነው ቃሉን ማስተዋል ለምን ተዘነጋን? ያሰኛል፡፡ከሁሉ በፊት ለመሪ መጸለይን ቅዱሱ የጌታ መንፈስ ከተናገረን ምንም ምክንያት ማቅረብ አይበጀንም፡፡የወንጌሉ በር አብዝቶ እንዲከፈትና መከሩ እንዲበዛ ከሁሉ በፊት የዛሬዎቹን "ቄሳሮችና አውግስጦሶች " በጸሎት እንባርካቸው እናስባቸውም፡፡
     ጌታ የመሪዎቻችንን ልቡና ከክፋት፣ ዙፋናቸውንም ከሴሰኝነትና ከጉበኝነት ይጠብቅልን፡፡አሜን፡፡
 


                             

1 comment:

  1. መንፈሳዊ መሪዎች ነን ስለሚሉ ሰዎችስ ምንነው ዝም አልክ? በእግዚአብሔር ቤት እየኖረ አሜን አሜን እያሰኘ የአግዚአብሔርን መንግስት ሀሳብ የሚያፈርስ መሪ፣ እቅዱን የሚያኮለሽና ከክርስቶስ በላይ የራሱን ሰብዕና የሚገነባ መሪስ ምነው ተረሳ ዞሮ ዞሮ አላማህ መንፈሳዊ ስለሆነ በስሙ እና በክብሩ የየሚቀልዱ አገልጋዮችን መገሰጽ የስፈልጋል፡፡

    ReplyDelete