Wednesday 25 September 2013

"አድኃነ ህዝቦ በመስቀሉ" "ህዝቡን በመስቀሉ አዳነ"(ቅዱስ ያሬድ)

ምድራችን ካስተናገደቻቸው አስከፊ ገጽታ ካላቸው ጦርነቶች መካከል አንዱ በተለያዩ ዘመናት "በክርስቲያኖች" የተመራውና ብዙ ሚሊዮኖችን ለህልፈት የዳረገው የመስቀል ጦረኞች ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱን ጳጳሳት በመባረክ፣ካህናት ጸሎት በማድረግ ይራዱ እንደነበርም ተዘግቧል፡፡ሰውን ወዳዱ ጌታ ኢየሱስ የፍጡር ደም መፍሰሱ እንዲያባራ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን በመስቀሉ ደሙን አፍስሶ ሲያድነን አመጸኛ ክርስቲያኖች ግን የሰላም ስሙንና አርማውን አንግበው ምድሪቱን በግፍ ደም አጥለቀለቋት፡፡
       ክርስቶስ ኢየሱስ ፣መድኃኒቱ ጌታ "ስለእኛ የተረገመ ሆኖ ከህግ እርግማን ሊዋጀን" ፤ ከኃጢአታችንም ሁሉ ሊያነጻን ፤የእኛን በኃጢአት መረገም አርቆ የእርሱን ጽድቅና ቅድስና እንዲሁ ያለዋጋ ሊሰጠንና "የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል" እርሱ እንደህጉ የተረገመ ሆኖ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡(ገላ.3÷14) እርሱ የተሰቀለው ህይወት እንዲሆንልንና እንዲበዛልን ፣መዳናችንም እውን ሆኖ ከኃጢአት ባርነት ነጻ እንድንወጣ ነው፡፡
       እኛን ኃጢአተኞችን ከኃጢአት ባርነትና ከህግ መርገም ነጻ ለማውጣትና ለማዳን የተከፈለው ተካካይ የሌለው ዋጋ የመስቀሉ ቃል የተባለ የክርስቶስ ሞትና (ገላ.3÷13) የከበረ ደሙ ነው፡፡(1ጴጥ.1÷19) እርሱ በመስቀል ካልተሰቀለ ደሙንም ለስርየት ካላፈሰሰ በቀር እኛ ወደእርሱ፣ በሰማያት ወዳለአባቱም መቅረብ አይሆንልንም፡፡(ዮሐ.12÷32፤ ኤፌ.2÷13)፡፡
    ከምድር እስከሰማይ የተዘረጋው ያ እውነተኛ የያዕቆብ መሰላል ክርስቶስ(ዮሐ.1÷52) በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ እግዚአብሔርና ሰውን የለየው የዘመናት የጠብ ግድግዳ ፈርሶ ሰውና ሰው፣ ሰውና እግዚአብሔር ፍጹም ታርቀው አንድ ሆነዋል፡፡የነበረብንም የዕዳ ጽህፈትና በደል በተትረፈረፈው በመስቀሉ የደም ዋጋ ተደምስሶልናል፡፡(ቆላ.1÷20፤2÷14፤ራዕ.12÷11)


    በዚህ በመስቀሉ ሞት ጌታ ልዩውን ኪዳን አዲሱን መስርቶልናል፡፡(ሉቃ.22÷20) የሞት ስልጣኔ ተወግዶ ክርስቶስ በሞቱ ማርኮናል፡፡ዲያብሎስ አስጨንቆን ከሚገዛን ቤት ክርስቶስ ነፍሱን ሰጥቶ በፍቅርና በምህረት ወደቤቱ አፍልሶናል፡፡በአዲሱ ኪዳን ባቀረበልን የመስቀሉ መስዋዕትም ማንኛውም ሰውና በየትኛውም ዘመን እስከምጽአቱ ያለውን ኃጢአት የሚያስተሰርይ ነቅ የሌለበት መስዋዕት ሆኖ ለአለሙ ተሰጥቷል፡፡በዚህም ክርስቶስ ሌላ አንዳች መስዋዕት እስከማያስፈልግ ድረስ ታርዷል፡፡ከእንግዲህ በኋላ ከክርስቶስ በቀር ሌላ መስዋዕት ፣ሌላም መድኃኒት ስለኃጢአታችን አይቀርብም፡፡(ዕብ.10÷14)፡፡እርሱ በመስቀሉ ሞት ለዘለዓለም ፍጹማን ሆነን እንድንድን አድርጎናልና፡፡
     ኢትዮጲያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ "ህዝቡን በመስቀሉ አዳነ" ያለው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ብሉያትና ሐዲሳት ተስማምተው የሚተረጉሙትም እውነት "አለም በክርስቶስ ሞት ፣ምድር ሁሉ በክርስቶስ መስቀል እንዲሁ ያለዋጋ መዳኑን ነው፡፡" አዎ! ህዝብ ሁሉ የዳነው በክርስቶስ ሞት ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስ የአይሁድና የአህዛብ የሁለቱ ወገኖች መታረቅና ሁሉን ሲለያይና ሲያለያይ የነበረው ጥል የመገደሉና ከመንገድ ተጠርቆም የመወገዱን ነገር ሲገልጥ፦
           "እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና። "(ኤፌ.2÷14-17)
አዎ! ወደአብ የቀረብነውና የመቅረብ ዕድሉን ያገኘነው በእርሱ የመስቀል ሥራ በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት ነው፡፡ይህም በልጁ የሚያምኑትን ሁሉ አብ የሚቀበላቸውና የሚወዳቸው መሆኑን ፣ክርስቶስ በሠራው በሞቱ ሥራም ወደእርሱ የመቅረብ ሙሉ ድፍረትና ብቃት እናዳላቸው የሚያመለክት ነው፡፡
      ሰላማዊው ጌታ በመስቀሉ ሰላሙን አድሎናል፡፡የኃጢአታችንንም ስርየት አስረግጦልናል፡፡ሊቁ ያሬድ በድጓ መስቀሉ እንዲህም ብሏል "መስቀል መመኪያችንና ህይወታችን ነው፣የምንመካበት ይህ መስቀል ረድኤት ነው፤ኃይልም ነው፡፡መስቀል የአለም ኃጢአት የተወገደበት መመኪያ ነው፡፡" አስተውሉ! የአለሙን ኃጢአት ያስወገደው አንዱ የእግዚአብሔር በግ ልጁ ብቻ ነው፡፡(ዮሐ.1÷29)፡፡በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰውም ደም ቤዛነትንና ጽድቅን ያስገኘልን ያ የነቢያት ተስፋ የሐዋርያት የስብከታቸው ርዕስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡(ሮሜ.5÷2፤ሐዋ.3÷14-17፤4÷1-13)፡፡ህይወታችንም፣ረድኤታችንም፣የኃጢአታችንም ስርየት፣ የምንመካበት ብርቱ ትምክህታችን ሰማይንና ምድርን የሰራ አካላዊ ቃል ፣ፈጣሬ ቃል በኋለኛው ዘመን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን የነሳና ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡(ዮሐ.14÷6፤1ቆሮ.1÷31)
    የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ ኢየሱስ በእርግጥ ለሚጠፉት ሞኝነትና አላዋቂነት ነው፡፡መዳን በታላቁ የመስቀል ሥራ በክርስቶስ ሞት ማመን ነው ብሎ መናገር ብዙዎችን እንደከንቱ ልፍለፋና አላዋቂነት ያስቆጠረ ነው፡፡ምክንያቱም ብዙዎች በራሳቸው መልካምነት እንደሚድኑ ያስባሉና፡፡ደሙ ያልጋረደው መልካምነት ምንም ነው፡፡ዳሩ ግን መናንያን አለምን የናቁት ፣ሰማዕታት መራራውን ሞት የታገሱት ፣ወንጌላውያኑ እየተገረፉ በደስታ የሰበኩት ፣ህጻናት በትብ አንደበታቸው የመሰከሩለት፣ሊቃውንት መተርጎም አቁመው በተመስጦ የቀሩት … ያ የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ ልባቸውን በሞቱ ማርኮት ነው፡፡ይህ ነገር ለማያምኑና ለሚጠፉ የሞኝነት ስብከት ነው፡፡አዎ! አለሙ ግን የዳነው በመስቀሉ ቃል ነው፡፡
       በክርስቶስ ክርስቲያን ቤተሰቦቼ ሆይ! ሁላችን በሞቱ የተጠራን ህያዋን ነን፡፡ህያዋን የሆንነው ደግሞ እርሱ ክርስቶስ እስከመስቀል ሞት ታዞ ነው፡፡ወልድ በመስዋዕትነቱና በመታዘዙ አብንና መንፈስ ቅዱስን አርክቷል፡፡በዚህ የመስቀል ሥራውም አለምን ሁሉ አንድ ጊዜ አድኗል፡፡እኛም ፍለጋውን እንከተል ዘንድ ተጠርተናል፡፡ሰውነታችንን የተቀደሰ መስዋዕት አድርገን በማቅረብ ለፈቃዱ በመታዘዝ መስቀላችንን ተሸክመን እንከተለው ዘንድ፡፡
ይቆየን፡፡አሜን፡፡

2 comments: