Saturday 7 September 2013

"በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት"(ሉቃ.13÷8)



          የዘመን መጨመር በራሱ አንድ ሰፊ የንስሐ በር ነው፡፡እግዚአብሔር ብዙ ዘመን በመስጠት ዕድሜ የሚያትረፈርፍልን ኃጢአተኞች መሆናችንን  አውቀን ፈጥነን ወደልባችን በመመለስ ንስሐ እንድንገባ ነው፡፡ዘመን የተጨመረልን ከሞቱት ዘመድና ወገኖቻችን ይልቅ ጻድቃንና የተሻልን መልካሞች ስለሆንን አይደለም፡፡ይልቁን በደሙ ማስተሰርያነት ያላወራረድነው ኃጢአት ስላለብንና በዚያ ኃጢአት እንዳንሞት "ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ እንዲሞት"(ህዝ.3÷18) የማይፈቅድ እግዚአብሔር ዕድል አብዝቶልን ነው፡፡
          ከክፉ ልማዶቻችን መካከል አንዱ በሰው ላይ አደጋ በደረሰ ጊዜ በኃጢአቱና ከእኛ ይልቅ በከፋ ነውሩ እንደደረሰበት አድርገን እናወራለን፡፡እናምናለን፡፡ያ አደጋ እኛን ያላገኘን በተሻለ በጎነታችንም እንደሆነ እናስባለን፡፡በአንድ ወቅት ሰዎች ወደጌታ ዘንድ መጥተው (ሉቃ.13÷1-6) ያሉት ይህንን ነበር፡፡ ጲላጦስ በመሰውያው አጠገብ ያስገደላቸው የገሊላ ሰዎችና በሰሊሆም ግንቡ ተንዶ የሞቱት ሰዎች በህይወት ካሉት ይልቅ ክፉዎች በመሆናቸው ነው ብለው አወሩለት፡፡ 
        አዎ! ብዙ ጊዜ የምሰማው ነገር አለ፡፡ከባህር ማዶ በአውሮፓና በአሜሪካ ከባባድ አውሎ ነፋሶችና የምድር መናወጦች በተከሰቱ ጊዜ ከብዙ ሰው አንደበት "የኃጢአታቸው ዋጋ ነው!!!" እየተባለ ሲወራ

 እሰማለሁ፡፡ይታያችሁ!!! እኛ እንግዲህ ያ ሁሉ ያላገኘን ከእነዚያ የተሻለ በጎነትና መልካምነት ስላለን ነው ሊባል ነው፡፡እውነታው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ምናልባት እኛ ከእነርሱ በባሰ ክፋት ተይዘን የበለጠ የንስሐ ዕድል ተሰጥቶን እንደሆን ማን ያውቃል?
        ጌታ ይህንን ነው ያለው፦ "ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።"ሉቃ.13÷2-4)
        ከሞቱት ይልቅ ለእኛ ሰፊ የንስሐ ዕድል ተሰጥቶናል፡፡ወንድሜ በሞት ከጎኔ የተለየው ለእኔ የ"ተዘጋጅ" ደወል ነው፡፡የተሻልኩ ሆኜ አልቀረሁም ይልቁን የሚብስ ፍርድ እንዳያገኘኝ ቀን ተጨምሮልኝ ነው፡፡ስለዚህ ብዙ ዕድል ተሰጥቶኛልና ብዙ ከእኔ ይጠበቃል፡፡
    ጌታ ምሳሌ መሰለላቸው(ሉቃ.13÷6-9)፡፡በወይን እርሻ ስፍራ በለስን የተከለ አንድ ሰው ነበር ብሎ፡፡ያ አንድ ሰው የተባለ እግዚአብሔር በለስ የተባለች እስራኤልን ለምድር ፈውስ ትሆን ዘንድ ተክሏት ነበር፡፡በየዘመኑ የተመረጡ ነቢያትን ፣ታላላቅ ነገስታትን ፣ብርቱ ካህናትን አስነስቶ እንደውኃ በፍቅሩ መራት፡፡ተፈውሳ እንድትፈውስ ፣አፍርታ ፍሬዋ ብዙዎችን እንዲማርክ ፣በቅድስና ተውባ በውበቷ ለእርሱ ቆነጃጅት የህይወት ደናግላንን እንድታጭ … ሁሉን ነገርም አደረገላት፡፡
        ይህንን ሁሉ አድርጎ ፍሬ ሊፈልግባት እስከሦስተኛ አመት መጥቶ ምንም ሊያገኝባት ግን አልቻለም፡፡ግዑዙ ቡቃያ የምድሩ ተክል እንኳ ፍሬ ሊያፈራ የሚያስችለው ሰፊ ጊዜ ሦስት አመት ነው፡፡ለእስራኤልም ፍሬ የምታፈራበት በቂና የተትረፈረፈ ጊዜ ተሰጣት፡፡ግና ፈጽሞ ልታፈራ አልቻለችም፡፡ስለዚህም እንዲህ ተባለ፦ "የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው።"(ቁ.7)፡፡የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ ካልተጠቀምን እንደዚህች ተክል ነው፡፡ጌታ ለእያንዳንዳችን የዘመን በረከት አድሎናል፡፡ለሌሎች የህይወት መዓዛና ሽታ እንድንሆን ተጠርተናል፡፡ከረከሰው ዓለም ጋር እንድንረክስ አይደለም በተሰጠን ሰፊ የፍሬ ዘመን አብበን እንድናፈራ እንጂ፡፡
     ዛሬም በተሰጠን ዘመን የኃጢአት ቀጠሮዐችንን ሳንጨርስ በርኩሰታችን ምድርን የምናጎሳቁል አለን፡፡ እግዚአብሔር ተፈጥሮ በርኩሰት እንዲባክን አይወድም፡፡በጦርነትና በአመጽ፣በአደንዣዥ ዕፅና ሲጋራ በሚበከል አየር፣በዝሙትና በጭፈራ ተፈጥሮ እየተበከለ ነገን ማየት ሥጋት እየሆነ ነው፡፡በእጃችን በሰራነው ቦንብና በምናጤሰው ጢስ ተፈጥሮ እጅግ ባክኗል፡፡የባከነው ተፈጥሮ ግን መልኩና ወዙ የሚመለሰው እኛ በንስሐ ስንታደስ ነው፡፡
  ማላጁ ጠባቂ ግን እንዲህ አለ፡-"ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ። "(ቁ.8-9)፡፡ እስራኤል በቂ የንስሐ ዘመን ተሰጥቷት ፣ ቤቷም የተፈታ ወና ሆኖ እንዳይቀር ብዙ መክሯት ልትቀበል ባለመፍቀዷም አለቀሰላት፡፡እውነተኞቹን የእግዚአብሔር ነቢያትና መምህራን ብትገድልም እንኳ የንስሐ ዘመን ዕላቂ ጊዜም ተሰጥቷት ነበር፡፡እንደጫጩት በይቅርታው ክንፍ ሥር እንድትጠለልም ጌታ ብዙ ወዶም ነበር፡፡(ማቴ.23÷29-39)ነገር ግን እርሷ ፈጽሞ አልወደደችም፡፡የተጨመረላትን ትራፊ ዘመን አንኳ ለመጠቀም አልታደለችም፡፡ታሪክ እንደሚነግረን ጌታ ባረገ በአርባኛው አመት ገደማ ኢየሩሳሌም ሙሉ ለሙሉ ወደመች፡፡
      ወገኖቼ! እኛም ዛሬ ያለነው በተዋገደ ዘመን ላይ ነው፡፡በምህረቱና በደሙ በተትረረፈልን በፍጻሜ፣ ዋናችንም አልቆ በትራፊው ዘመናችን ነን፡፡ ከምንኖረውም የኖርነው ዘመናችን ይበልጣል፡፡ዘመን የተጨመረልን ለሌላ የኃጢአት ቀጠሮ እንድናቃጠርበት አይደለም፡፡የተጨመረልን "ለዘንድሮ ብቻ" በምትል የምህረት አዲስ ኪዳን ነው፡፡እንኪያስ ባለቀ "ለዘንድሮ ብቻ" በተባለች በዚህች ዘመናችን ንስሐ እንግባ፡፡እነሆ መቅረዝ የቀን ብርሐን የተባለ እድሜያችንን ካልሰራንበት የሚወስድ በደጅ አለና አሁኑኑ እንመለስ፡፡ጌታ በዚህ ዓመት የተተውን ሁላችንን በንስሐ የምንታደስበትና የምንመለስበት ያድርግልን አሜን፡፡


1 comment: