Saturday, 29 October 2022

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፳፩)

 Please read in PDF

የመድሎተ “ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በግልጥ በመቃወም፣ ሌሎችን መጻሕፍት ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ለማስተካከል የሄደበትን ሩቅ መንገድና እንዲሁም ቅዱሳት መጻሕፍትን አጥምሞ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን እንደ ገና በመተርጐም በመጽሐፉ ውስጥ እንዴት እንዳስገባ በጥቂቱ በማሳየት፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ያለንን ዐሳብ እንቋጫለን፤ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣንን ከተቃወመባቸው ወይም ከሻረባቸው መንገዶች ጥቂቶቹን እናንሳ፦

1.   ያላለውን እንዳለ አድርጎ በማቅረብ፦ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የሚቃወሙ አካላት ከሚፈጽሟቸው ግልጽ ስህተቶች አንዱ፣ የመጽሐፉን ዐውድ በመጣስ ያልተናገረውን እንደ ተናገረ አድርጐ ማቅረብ ነው። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ በዚህ ረገድ ለምሳሌ፦

1.1.     ኀጢአትን ለካህን ስለ መናዘዝና ስለ ቀኖና፦ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ በዚህ ርዕስ ሥር በቅጽ አንድ ከገጽ 241-265 ኀጢአትን ለካህን መናገርና ቀኖና ወይም “መንፈሳዊ ቅጣት” ስለ ኀጢአት በመቀበል፣ የኀጢአት ሥርየት ማግኘት እንደሚቻል ሲያስተምር እንመለከተዋለን።

ይህንም ትምህርት ለማጽናት፣ ከተጠቀማቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል እኒህ ዐውድ የጣሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይገኙበታል፤

1.1.1.   በ1ቆሮ. 5 ላይ ያለው አመንዝራ ሰው ላይ የተወሰደውን እርምጃ፣ የቀኖና ውጤት ነው ይለናል፤ ነገር ግን ዐውዱ አንድ የታወቀ አመንዝራ ምሳሌ አልባ በኾነ መንገድ በቅዱሳን መካከል በመመላለሱ፣ ምንም እንኳ ሰውየው ኃጢአቱን ለቄስ ባይናዘዝም ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅድስና አልባ ምልልሱን በግልጥ ሲቃወምና ልክ አለመኾኑን ሲናገር እንሰማዋለን። በዚህ ክፍል ውስጥ ሰውየው ኀጢአቱን ሲናዘዝ አንመለከተውም፣ እንዲያውም የተገለጠ ኀጢአትን በአደባባይ ስለ መገሰጽ እንጂ በሽሽግ ኀጢአትን ለካህን የሚናገር ክፍል አይደለም።

ነገር ግን ይህን ግልጥ እውነት የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ላልተጠቀሰለት ወይም ላልተጻፈለት ዓላማ ሲጠቅሰው እንመለከታለን።

1.1.2.    እጅግ አጸያፊና አስነዋሪ በኾነ መንገድ ሌላም ስለ ቀኖና የሚጠቅሰው ክፍል ደግሞ፣ እግዚአብሔር የመጀመሪያው ሰው አዳም በመበደሉ፣ በመላለሙ ላይ የሰጠውን ፍርድ ቀኖና ነው ብሎ ይጠቅስልናል፤ ዘፍ. 3፥15-19 ያለውን በመጠቈም። እግዚአብሔር ለመላው ፍጥረት የ5500 ዓመት ቀኖና ሰጥቶ ነበር ይለናል። ነገር ግን ሰው ምን ቦታ ላይ ኑዛዜ እንደ ፈጸመና የ5500 ዓመታት ቀኖና እንደ ተሰጠው አይናገርም።

ይልቁን የ“መድሎተ ጽድቅ” ቀኖናው የተፈጸመው፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰው መኾንና ቤዛነት እንደ ኾነ ይናገራል። እንግዲህ ኀጢአቱን የፈጸመው አዳም ሲኾን፣ ቀኖናውን የፈጸመለት ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይለናል። እውነቱ ግን እርሱ ከሚናገረው የኑዛዜና የቀኖና ትምህርት ፈጽሞ የማይሄድ ትምህርት ነው።

·        በ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ አስተምህሮ፣ ኑዛዜ ፈጻሚና ቀኖና ተቀባይ አንድ ናቸው፤ በአዳም ውድቀት ውስጥ የወደቀው አዳም ቀኖና ፈጻሚው ክርስቶስ ነው የሚለው አይገጥምም፣

·        አዳም 5500 ዓመታት ቀኖና ፈጸመ ብንል እንኳ፣ ነገር ግን ስለ ኀጢአቱ “ወደ ሕይወት ንስሐ መምጣቱን” የሚናገር አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚኾን ንስሐን የሚሰጥና ኹሉን በመጥራትም ባለጸጋ የኾነው” እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብቻ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ (የሐ.ሥ. 11፥18፤ ሮሜ 10፥12)። ስለዚህ በማናቸውም መንገድ አዳም 5500 ዓመታት ቀኖና መቀበሉን የሚያመለክት አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የለም።

·        ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ በመላው የክርስትና አስተምህሮ የታወቀ ክፍል ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ባለመታዘዝ የተነሣሣውን ፊተኛው አዳምን ስለ መተላለፉ ፍርድ እንደ ፈረደበት የሚያመለክት ነው። ፍርዱ እውነትና በትክክል የተተገበረ ነው፤ እንደ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ አባባል፣ ቀለል ያለ አባታዊ ተግሳጽ ሳይኾን፣ እግዚአብሔር እጅግ አዝኖ በጽድቁ በትክክል በመላለሙ ላይ የፈረደበት ፍርድ ነው።

ይህን ከኑዛዜና ከቀኖና ትምህርት ለይተን፣ ከነገረ ድኅነት አንጻር ብናየው፣ በክፍሉ ላይ ያሉትን ፍርዶች ጌታችን በመምጣቱ እንኳ የተሻሩ አይደሉም፤ ይልቁን ጌታችን ኢየሱስ ሲመጣ፣ ፍርዶቹ ወደ በረከት ተለወጡ እንጂ።

ለምሳሌ፦ ወሊድ ምጥ የበዛበት ቢኾንም፣ ጌታ ግን ምጥን በመውለድ ባርኮት ደስታን ሞላበት፤ ሥራን በተመለከተ ጥረትና ግረት ያለበት ቢኾንም፣ ያንን ግን እግዚአብሔር ባረከው፤ ስለዚህ ዛሬም ጥረታችንና ትጋታችንን ከጸጋውና ከመግቦቱ የተነሣ ሥራን ይባርካል (2ተሰ. 3፥10-13)፤ ወደ አፈር መመለስን እግዚአብሔር፣ ወደ ልጁ መንግሥት መፍለሻ መሸጋገሪያ ድልድይ አደረገው እንጂ ስንሞት (በሥጋ) የምናዝን አይደለንም!

ስለዚህ ዘፍ. 3፥15-19 ላይ ያለው እንደ “መድሎተ ጽድቅ” አባባል ኑዛዜ፣ ቀኖናና የኀጢአት ሥርየት መገኘቱን የሚያመለክት አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለም!

ይልቁን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታላቁ ሊቀ ካህናት ስለ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ ይላል፣

እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” (ዕብ. 4፥14-16)።

የእኛ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ኢየሱስ፦

·        ብቸኛ ሊቀ ካህናታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፣

·        እንደ እኛ በማናቸውም ነገር የተፈተነ ነው፤ ቢፈተንም ግን አንዳችም ኀጢአትን አላደረገም፤ የእርሱ መፈተንና የእኛ መፈተን ልዩነቱ በውጤቱ ነው፤ እርሱ በአንዳችም ፈተና አልወደቀም (ማቴ. 4፥1-11)፤ መፈተንን የሚያውቀው ሊቀ ካህናት ስንፈተንና ስንደክም የሚራራልን ነው፣

·        እርሱ ደካማ መኾናችንን ስለሚያውቅ ለምናምንበት አለመራራት አይችልም፣

·        ኀጢአት ባደከመን ጊዜ ኹሉ ወደ ሊቀ ካህናታችን የጸጋ ዙፋን በእምነት እንቅረብ፤ እርሱም ያሳርፈናል፤ አሜን።

ይቀጥላል …

 

No comments:

Post a Comment