አእመረ አሸብር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቲቪ ላይ
ያደረገውን የክፍል አንዱን ቃለ መጠይቁን አድምጬዋለሁ። እጅግ ሊደንቀኝ በሚችል መልኩ፣ ቃለ መጠይቁን ያደረገው ሰው ደጋግሞ
ላነሳቸው ግልጽ ጥያቄ አእመረ አለመመለሱ ሳይኾን፣ ጠያቂው ጨርሶ ለማመን አለመቻሉ፣ ከአእመረ ይልቅ ጠያቂውን እንዳምነው ግድ
ብሎኛል።
አእመረ በተደጋጋሚ 2010 ዓ.ም ላይ ወደ ተሐድሶ እንደ ሄደ ይናገራል፤ ይህን
እውን ለማድረግም 2010 ዓ.ምን ቢያንስ ከአራት ጊዜ በላይ ሲጠራው እንሰማዋለን፤ ለእኔ ግን ይህ የገዘፈ ውሸት ነው፤ እኔ
አእመረን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ያሬድ የምሥራቅ ሥነ መለኮት የትምህርት የጥናትና የምርምር ተቋም (የኦርቶዶክስ ተሐድሶ መንፈሳዊ
ኮሌጅ) ውስጥ የዲፕሎማ መርሐ ግብር ባስተማረን አራት ትምህርቶች ነው፤ ያስተማረንም ትምህርተ ሥላሴ፣ የአባቶች ትምህርትና
እምነታችን፣ ኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ታሪክና ሥነ መለኮትና ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የሚሉ አራት ኮርሶችን ነው። ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ
እንደ መኾኔ ፍጹም ልዘነጋው አልችልም!
ከዚያ በዘለለ አእመረን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፍ የማውቀው ከ2003
ዓ.ም በፊት ነው፤ ይህ ጊዜ ማለት ደግሞ የዲፕሎማ ትምህርት ከመጀመራችን በፊት ማለት ነው። እና አእመረ ለምን የብል ጠት ቋንቋ
ወይም ውሸ ት እንደ ፈለገ አይገባኝም። አእመረ በትክክል ተመልሻለሁ ካለ፣ ከእኛ ጋር ያሳለፈውን ጊዜ መደበቅ ምንም
አይጠቅመውም፤ እውነተኛ ንስሐና መመለስ የተደረገውን በተደረገበት መንገድ በትክክል ማመንና መጸጸት ነውና። በርግጥ ይህን
መናገር ለእርሱ እጅግ አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም በእነዚያ ጊዜያት እርሱ ታላቅ ሥልጣን ይዞ፣ በኦርቶዶክስ ውስጥ ነበረና። ጥያቄ
አቅራቢው ይህን በተወሰነ ረገድ የተረዳ ይመስለኛል፤ ለዚያም “በዚህ በአጭር ማለትም ስምንት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዴት
ኹሉን ነገር እርግፍ አድርገህ ልትተው ቻልህ?” የሚለው።
በመጣበትም ጊዜ እንኳ አእመረ ወደ መሪነት እንዳይመጣ ፈጽመው ይሟገቱ የነበሩ
ወንድሞች መኖራቸውን ጨርሶ አልዘነጋም፤ ከዚያም ባለፈ እኔ በግሌ ኦርቶዶክስ ላይ በሚያንጸባርቀው ከልክ ያለፈ ጥላቻና የዘር
ተኰር ፖለቲካ በነበረው አቋሙ ፊት ለፊት ከተቃ ወሙት መካከል አንዱ ነኝ። እናም አእመረ፣ በርግጥ ወደ ኦርቶዶክስ ተመልሶ
ከኾነ፣ ስህተቱን በትክክል ቢናገር እኛ የምንፈራው ነገር አይኖረንም።
እንደ ተናገረው ወንጌል ወይም ወደ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እንመለስ
የሚለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ 2010 ዓ.ም አልጀመረም፤ ጥንትም ነበረ፤ ወደ ፊትም ይኖራል፤ አእመረ በዚህ መንገዱ፣ በርግጥ እየተጋጨ
ያለው ከግለሰቦች ጋር ሳይኾን፣ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ካስነሣውና ብዙዎችን ከፍጡር አምልኮ ካላቀቀው ቅዱስ አገልግሎት ጋር ነው።
በእርሱ ልብ የነበረው እውነት፣ እርሱ ሲመለስ ኹሉም ነገር እንደሚያከትምለት አስቦ
ነበር፤ ነገር ግን እርሱ እንዳሰበው አንድም ሰው ተከትሎት አልሄደም! ያ ይበልጥ ሳያበሳ ጨው እንዳልቀረ ገምታለሁ!
እንዳሰበው ተራ ማኅበር ወይም ቡድን ቢኾን ይህን ያህል፣ እርሱና ወዳጆቹ ይዘናል
ላሉት እውነት ሥጋት እንደማይኾንባቸው እናምናለን፤ እውነታው ግን የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህለው የጌታ መንግሥት በየጥቂቱ ማደጓና
መውረሷ እንደማይቀር የታመነ ነው! እናም አእመረ ሆይ፤ ከተናገርህ አይቀር እቅጭ እቅጯን ብትናገር ዳግም ከኅሊና ወቀሳና ጸጸት
ትድናለህ ብዬ እመክርሃለሁ። በውሸ ት የሚጠፋ ስምና አገልግሎት ስለሌለን፤ በብል ጠት ቋንቋም የሚደበዝዝ ወንጌል ስለሌለን ጌታን
እናከብረዋለን።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ
ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።
No comments:
Post a Comment