Tuesday, 11 October 2022

“ባዕዱ ወንጌል 2”ና ግለ ምልከታዬ!

Please read in PDF

ባዕድ 2 - ሌላ ኢየሱስ (የሐሰተኛ አስተማሪዎች ኢየሱስ - በቅዱስ ቃሉ ሲፈተሽ) ወይም “Baed Documentary Film” የሚለውን ዘጋቢ ፊልም ተመልክቼዋለሁ። የብልጽግና ወንጌል ለእውነተኛዪይቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተናና ከባድ ተግዳሮት ሊኾን እንደሚችል ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም። በዚህ ረገድ እኔም የድርሻዬን ለመወጣት በ2010 ዓ.ም “የእምነት እንቅስቃሴ - የዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተና” በሚል ርዕስ፣ የእንቅስቃሴውን አደገኛነትና በተለይም በተሐድሶአውያን መካከል በነበጋሻው ደሳለኝ አማካይነት ማቆጥቆጡን ተመልክቼ ተቃውሜ ጽፌአለሁ።



የእምነት እንቅስቃሴን ወይም የብልጽግና ወንጌልን የሚያራምዱ አገልጋዮች ቀላል ተከታዮች የላቸውም። የሐሰት መምህራኑ ራሳቸውን በእውነተኛው እርሻ ውስጥ በመሸሸግ ይታወቃሉ፤ ጌታችን እንደ ተናገረው፣ “በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ የሚሄድ” (ማቴ. 13፥28) ወይም ደቀ መዛሙርት እንዳስተማሩን፣ “በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤” (2ጴጥ. 2፥1) ብለው አስተምረውናል፤ ይህን የሚያደርጉትም፣ “ሾልከው በስውር ገብተው” ነው (ገላ. 2፥4፤ 2ጢሞ. 3፥6-7፤ ይሁ. 4)።

የስህተት መምህራንን ስለሚደግፉ ሰዎች ሳስብ በብዙ እንደነቃለሁ፤ በኦርቶዶክስ ቤት “ንጉሥ ቴዎድሮስ” ይመጣል ብለው በከንቱ ተስፋ የሚያደርጉ አያሌ ሰዎች አሉ፤ በጋሻው ደሳለኝ “በልዩ  ቅብአት” ይገለጣል ብለው፣ ዓይናቸውን ተሸፍነው የብልጽግና ወንጌል ትምህርቱን ቁጭ ብለው የሚጋቱ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እንዲሁም ዮናታን አክሊሉ የብልጽግና ወንጌል እንደሚያስተምር ቢያውቁም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሚደግፉት ቍጥራቸው ቀላል ያልኾኑ ሰዎች አሉ፤ እኒህና ሌሎች ደጋፊዎች ዋናቸው መምህራቸው እንዲ ኢየሱስ ወይም ቃለ እግዚአብሔር አይደለም። ይህ ልብ ይሰብራል! ባዕድ 2 ፊልምን አይቶ የዮናታንና የሌሎችንም የስህተት መምህራን ማንነትና የትምህርታቸውን አሳችነት መረዳት አለመቻል ከባድ ድንዛዜ፤ ከልክ ያለፈ ተላላነት ነው።

ሌላው ነገር፣ ዓቃብያነ እምነት የኾኑ ወንድሞችና እህቶች ራሳቸው በድካም ውስጥ ያልፋሉና እነርሱስ ማን ኾነው ለመንቀፍ ደፈሩ? የሚለው ነው። ይህ እጅግ ደካማ አመለካከት ነው። በእርግጥ ኹላችን በድካም ውስጥ ነን፤ እንዝላለን፤ እንስታለን። ነገር ግን  በዓላማ የስህተት አሠራር ውስጥ አንሰማራም፤ ለማሳት ዓልመን አንንቀሳቀስም፤ ከስህተት መምህራን ጋር አናጋፍርም፤ በጉባኤያቸው ተገኝተን በየትኛውም አምልኮአዊ ሥርዓት አንካፈልም። ትላንት የሳትኩትን መሳትና እግዚአብሔር ይቅር ያለኝን ነውሬንና ኀጢአቴን እያነሳ የሚወቅሰኝና የሚከስሰኝ ሰይጣን ብቻ ወይም የእርሱ ወገንተኛ ነው። ዛሬ ላይ ግን የትላንት ሕይወቴን የኑሮ ዘይቤዬ አድርጌ አልሄድም፤ በክርስቶስ ጸጋ የምኖር ኀጢአተኛ እንጂ፣ በኀጢአት የምጸና ተላላ አይደለሁምና።

እንደ ወንድማዊ ምክር፣ አንዳንዶቹ ዓቃብያነ እምነት ቍጡነታቸውን ቢተዉ፤ ለምሳሌ፦ ጠንካራ ሙግት ሲገጥማቸው (በፖለቲካ፣ በለዘብተኛ … አቋማቸው ላይ) ሌሎች ሲወቅሱዋቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ጓደኝነታቸውን ይሰርዛሉ፤ ሰዎችን ቶሎ ወደ መፈረጅ … ወደ ሌሎች አላስፈላጊ ተግባራት ያዘነብላሉ። በተረፈ ግን ዶክመንተሪውም ኾነ ሌሎች ዕቅበተ እምነታዊ ሥራዎች ቢቀጥሉና በእውነተኞችና በሐሳውያን መካከል ግልጥ መስመር ቢሰመር ከሚወድዱት መካከል ነኝ! በዚህ ሥራ የተሠማራችሁትን ኹሉ ጌታ ኢየሱስ ይባርክ፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment