Friday 7 October 2022

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፳)

Please read in PDF

ከያዝነው ርዕስ ጋር በሚስማማ መልኩ፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ሮሜ 8፥34ን ለመተርጐም በተጠቀመበት መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል፤

“በአዲስ ኪዳን የተጻፉ መጸሕፍት ኹለት ነገሮችን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስን የምትተረጕመው ቤተ ክርስቲያን ናት። መጽሐፉ ይህ ነው ብላም ለይታ፤ ሰፍራ፤ ቈጥራ የሰጠችውም ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያን ናት መጽሐፍ ቅዱስን የሠራችው እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን አልሠራም።”[1]

እንግዲህ አስቀድመን እንደ ተናገርን፣ ይህ የ“መድሎተ ጽድቅ” አቋም ወይም አስተምኅሮ የካቶሊክ እንጂ የኦርቶዶክሳውያን አቋም አይደለም። ጸሐፊው ግን የካቶሊክን አስተምኅሮና እምነት በግልጥ እንደ ኦርቶዶክስ አስተምኅሮ ሲያቀርብ እንመለከተዋለን። ይህን ግልጥ መስመር መለየት ባልቻለበት ኹኔታ፣ ማለትም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥልጣንን ከቤተ ክርስቲያን አሳንሶ ማቅረብ፣ መድሎተ ስሑትነቱን  በግልጥ ያሳያል።


ከ“መድሎተ ጽድቅ” በተቃራኒ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛ ትምህርት የሚገልጡ አስተማሪዎች፣ “መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መገለጥ እንጂ[2] ቤተ ክርስቲያን የሠራችው ነው” በማለት አያምኑም። ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፣ የዚህን መሠረት ፍንትው አድርገው ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፤

“የመለኮታዊ መገለጥ መሠረቱም ሆነ ምንጩ ከሥጋዌም በፊት ሆነ በኋላ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ክርስቶስና የክርስቶስ መንፈስ ብቻ ነው። የክርስቶስ መንፈስ ስንል የእግዚአብሔር መንፈስ ማለታችን ነው፤ የሁለቱም መንፈስ (የባሕርይ ሕይወታቸው) አንድ መንፈስ ቅዱስ ነውና።”[3]

መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሌላ የእግዚአብሔር ቃል የኾነና “ቅዱሳት መጻሕፍት” ተብሎ የበቃ ወይም ሊበቃ የሚችል ፈጽሞ የለም። ለዚህ ነው ፍትሐ ነገሥት እንኳ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለይቶ፣ “የአምላክ መጻሕፍት፤ አምላክ ያጻፋቸው መጻሕፍት”[4] በማለት አክብሮ የሚጠራቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር፣ በትክክል የእግዚአብሔርን ዐሳብና ፈቃድ በግልጥ የሚናገር ሌላ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ለመኾኑና ብቸኛ የጽድቅ መመዘኛ፣ እርሱን የሚመስል ሌላ መጽሐፍ እንደሌለ ለቍጥር የሚታክቱ አያሌ ማስረጃዎች አሉ።

አጭር የስብከት ዘዴን ለማስተማር በጻፉት መጽሐፋቸው ሉሌ መልአኩም ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የኑሮአችን መመሪያና ሥልጣናዊ ይዘታቸው ስላለመለወጡ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፣

“ለመንፈሳዊ ኑሮአችን መመሪያ የኾኑት ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በነቢያትና በሐዋርያት የተጻፉ ስለ ኾኑ ይዘታቸው በምንም ምክንያት አይለወጥም፤ 2ጢሞ. 3፥16”[5]

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምሉዕ ሥልጣን ስላለው፣ የኹሉ ነገራችን ምንጭና መመሪያ መኾኑን ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም እንዲህ ላሉ፤

“ቅዱስ መጽሐፍ[መጽሐፍ ቅዱስ] እስትንፋሰ እግዚአብሔር እንደ መኾኑ እውነተኛውንና ቀጥተኛውን ምስክርነት ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይዎትና በምድር ስለ ሠራው፣ ስላስተማረውም የያዘ ኹኖ ይገኛል። … ሃይማኖታችንን፣ ሥነ ምግባራችንን፣ ባህላችንንና ሥርዓታችን ተከትሎ እውነተኛውን ትምህርት የሚሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። … የዶግማችን፣ አምልኮታዊ አገልግሎታችንንም የሥነ ሥርዓታችንም ኹሉ መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። … እንዲሁም ለሕይወታችን ኹሉ ከፍተኛ መመሪያ የሚሰጠንና … የምንረዳው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት ነው።”[6]

መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ሥልጣናዊ መኾኑን፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማያምኑ ወይም ክርስትናን ያልተቀበሉ የአርኪዎሎጂ ባለሙያዎች ሳይቀሩ፣ ስለ ብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት አስደናቂ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።[7] አንዳቸውም መጽሐፍ ቅዱስን መቃረን የሚችል ግኝት እንዳላገኙም ባለሙያዎቹ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ ይህን እውነታ ካረጋገጡ አርኪዎሎጂስት፣ አንዱን አይሁዳዊ አርኪዎሎጂስት በዋቢነት መጥቀስም ይቻላል።[8]

እንዲሁም ግብጻዊው ጳጳስ አባ ሺኖዳ እንዲህ ብለዋል፣

“የትውፊት ርቱዕነት መመዘኛው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ባለው ስምምነት ነው። … ስለ ትውፊት ስንናገር፣ … (1) ከመጽሐፍ ቅዱስ የማይቃረን (ገላ. 1፥8)፣ (2) ከሌላ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር የማይቃረን፣ (3) አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያለው።”[9]

በሃይማኖተ አበውም እንዲህ ተቀምጦአል፤

“የሚበልጠውም ትእዛዝ በኦሪት፥ በነቢያት፥ በወንጌል በሐዋርያት ቃል እናምን ዘንድ ነው። ንጉሥ ሆይ! … ለነፍስህ መድኀኒት ይኾኑህ ዘንድ እግዚአብሔር ሊገልጽልህ የወደዳቸው መጻሕፍት እሊህ ናቸው።”[10]

ራሱ የመድሎተ “ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ሙሉ ለሙሉ ባይቀበልም፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣናዊነት ሲመሰክር እናየዋለን፤ እንዲህ በማለት፣

“ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ምንም ሊነጻጸርና ሊወዳደር በማይችል መልኩ አክብራና አልቃ የምታምነው መጽሐፍ ቅዱስን ነው”[11]

ምንም እንኳ የመድሎተ “ጽድቅ” ጸሐፊና አያሌ የኦርቶዶክስ ካራ ተከታዮች፣ ይህን በአንደበታቸው ቢናገሩም፣ ነገር ግን በተግባርና ማንም ሊያስተባብል በማይችል መንገድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የቤተ ክርስቲያን ውላጅ ነው” ሲሉ እንጂ፣ ፍጹም እስትንፋሰ መለኮት ነው ሲሉ አንሰማቸውም። አያሌ ኦርቶዶክሳውያን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉ ሌሎችን መጻሕፍት ለመጥቀስ፣ የሚያቀርቧቸው ኹለት መንገዶች አሉ፤ እኒህም፣

  1. አዋልድ መጻሕፍት ሌሎች መጻሕፍት አይደሉም የሚል ደካማ ሙግት፦ ይህንም በምሳሌ ለመናገር ሲጀምሩ እንዲህ ይላሉ፤

“የሰው ዘር አባትና እናት አዳምና ሔዋን ናቸው፤ ልጆቻቸው ግን በዝተዋል፤ ሞልተዋል፤ ይበዛሉም፤ ይሞላሉም፤ አዋልድ መጻሕፍትም አባት እናታቸው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ቢኾንም ልጆቻቸው ግን በዝተዋል፤ ሞልተዋል፤ ይበዛሉም፤ ይሞላሉም”[12]

በዚህ ንግግራቸው ቅዱሳት መጻሕፍትና አዋልድ መጻሕፍት “የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታ” እንጂ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የብቻ ቃለ መለኮት ነው ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ነው የሚለውን ለመቀበል አይደፍሩም። 

2.   ቤተ ክርስቲያን አኹንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሥልጣን አላት የሚል ሙግት፤ ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚቀርበው፣ “መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን በኩል መጣ” የሚል ነው፤ ይህ ማለት ግን፣ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ወይም አስገኚ ናት ማለት አይደለም። እውነት ነው ሐዋርያት ሥልጣናውያን ነበሩ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመጻፍ መንፈስ ቅዱስ ነድቶአቸው ወይም መርቶአቸው ጽፈዋል።

ነገር ግን የሐዋርያት ሥልጣን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከጻፉ በኋላ ሥልጣናቸው አክትሞአል፤ ከሐዋርያት በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመጻፍ ተተኪ ሐዋርያ አልተነሣም። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ናት ካልን፣ ዛሬም ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመጻፍ የሚችሉ ሐዋርያት አሉ ወይም አባቶች አሉ እያልን ነው። ይህ ደግሞ ፍጹም ስህተት ነው።

እኛ ግን እንዲህ እናምናለን፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ስንል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃሎች ሙሉውን ማመን ነው ማለታችን ነው። ምክንያቱም የተናገረው እግዚአብሔር ራሱ፣ የጻፉትም ቅዱሳን ኹሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሪት ብቻ እንደ ጻፉ እናምናለን፤ ስለዚህም የእነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል አለመቀበል ወይም አለማመን ወይም አለመታዘዝ፣ እግዚአብሔር ራሱን አለመታዘዝ ወይም አለማመን ነው ብለን እናምናለን፤ (ዘዳግ. 18፥19፤ ኢያ. 22፥23፤ 1ሳሙ. 10፥8፤ 13፥13-14፤ 15፥3፡ 19፡ 23፤ 1ነገ. 20፥35-36፤ የሐ. ሥ. 3፥23፤ ዕብ. 12፥25)

ይቀጥላል …

 



[1] https://www.youtube.com/watch?v=3AakQxKl6N4&t=474s

[2] አባ ጎርጎርዮስ(ጳጳስ)፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ 1978 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 7 እና 87

[3] አባ አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 54

[4] ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፤ 1990 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ የማሳተሚያ ድርጅት፤ መቅድም ገጽ 11-12

[5] ሉሌ መልአኩ፤ አጭር የስብከት ዘዴ፤ 1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 28

[6] ሊቀ ሥልጣናት ሐ/ምርያም ወርቅነህ፤ የስብከት ዘዴ፤ 1980 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 72-73

[7] William F. Albright, Archaeology and the Religion of Israel (Baltimore: John Hopkins, 1953), 176.

[8] Nelson Glueck, Rivers in the Desert: A History of the Negev (New York: Farrar, Strauss, and Cudahy, 1959), 31.

[9] H.H. Pope Shenouda III, Comparative Theology Vol. I; July 1996; Cairo; pp.110-112

[10] ሃይማኖተ አበው 1986፣ 89፡90

[11] መድሎተ ጽድቅ፤ ገጽ 38

[12] ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ሐመረ ተዋሕዶ(የሐመር መጽሔት ልዩ መጽሔት)፤ ሚያዝያ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን።

No comments:

Post a Comment