Saturday, 5 November 2022

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፳፪)

 Please read in PDF

ምጽዋት የናቡከደነጾርን በደል ደመሰሰን?

1.1.3. “… ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል። ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር። ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ።” (ዳን. 4፥25-28)።

እንደ ተለመደው ትምህርቴን ያጸናልኛል ብሎ የተጠቀሰው ክፍል የተሰመረበትን ክፍል ነው።[1] ክፍሉ የሚገኘው ነቢዩ ዳንኤል የናቡከደነጾርን ሕልም ከፈታና ትርጕሙን ከነገረው በኋላ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በሚናገርበት ክፍል ነው። ናቡከደነጾር ከሠራው ኀጢአትና ከልቡ ታላቅ ትዕቢት የተነሣ፣ አእምሮውን ሊያጣና አስተሳሰቡም ወደ እንሰሳነት ሊለወጥ እንደሚችልና ሳርም እንደሚበላ ተናግሮአል። በዚህ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ከሃሊነትን እንደሚረዳና እግዚአብሔርን በማድነቅ ሊመለስ እንደሚችል ያስረዳል።

የሚተርፈው የዛፉ ጉቶ ማለትም፣ ምንም እንኳ ናቡከደነጾር ለሰባት ዓመታት ሣር በመጋጥ አእምሮው ወደ እንሰሳነት ቢለወጥም ንግሥናው ሳይወሰድበት ከሰባት ዓመታት በኋላ መልሶ እንደ እግዚአብሔር ቃል ዙፋኑን ይይዛል። እንግዲህ ዳንኤል እኒህ ክፉው ቀናት ወደ ናቡከደነጾር እንዳይመጡና እንዲዘገዩ፣ ለዚህም ደግሞ ናቡከደነጾር ንስሐ እንዲገባና ሕይወቱን እንዲያስተካክል ጌታ በዳንኤል በኩል ይነግረዋል። ለናቡከደነጾር መንግሥት የሚቆይለትና የሚመለስለት፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ” ነው ይላል። ይህም ይኾን ዘንድ ንጉሡ እውነተኛ ግብረ ገብ መፈጸምና ማሳየት አለበት ይለዋል ዳንኤል፤ ይኸውም፣

ü  ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር።”  መደበኛው ትርጕም ይህን ክፍል፤ “ኀጢአትን መሥራት ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ” ይለዋል።  ናቡከደነጾር ለዚህ ታላቅ ምክር እውነተኛ ምላሽ አልሰጠም። ንጉሥ እንደ መኾኑ፣ ለድኾች ወይም ለተጨቈኑት ቸርነትን ማድረግ ይገባው ነበር፤ ይህን ቢያደርግ ምናልባት ተግሳጹ ወይም ሊመጣ ያለው ቍጣ ይዘገይ ነበር። ነገር ግን ከቍ. 28 በኋላ እንደምንመለከተው የእግዚአብሔር ተግሳጽ ንጉሡ ላይ ሲፈጸም እንመለከታለን።

ü  የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊን ጥያቄ እንጠይቀዋለን፤ በመጽሐፉ ውስጥ እንደ ተናገረው፣ “ቀኖና መቀበል ማለት አንድ ሰው ከሃይማኖት ወይም ከተግባራዊ የክርስትና የሕይወት መንገድ በተለያየ ደረጃና ሁኔታ ወጣ ብሎ ወይም አፈንግጦ ከነበረ ወደ መስመር እንዲመለስና ሃይማኖታዊውን የሕይወት ጉዞ በትክክለኛው ጎዳና እንዲጓዝ መርዳት ነው።”[2] ይላል። በሌላ ስፍራም የቀኖናን አስፈላጊነት ሲናገር፣ “ … ለኀጢአታችን ፈውስና ሕይወት ሆኖ ወደ ተሰጠን የክርስቶስ ሥጋና ደም እንዲቀርብ ለማድረግ ነው”[3] ይላል፤ ለመኾኑ ናቡከደነጾር ቀኖና የሚሰጠው በእግዚአብሔር ከሃሊነት የሚያምን ነው? ከየትኛውስ የክርስትና መንገድስ ወጥቶ ይኾን? ቢመለስስ ወደ የትኛው ሥጋ ወደሙ ሊቀርብ ይኾን?

ü  የናቡከደነጾር ትክክለኛውን ሕይወቱን ብንመለከት አስቀድሞ ለሕልሙ ፍቺ የጠራቸው፤ አስማተኞችንና ቃላተኞችን፣ የባቢሎንን ጠንቃዮች እንደ ኾነ ቅዱስ ቃሉ ይመሰክርበታል፤ (ቍ. 6-7)፤ ታድያ ለዚህ ሰው ዳንኤል ምክርን እንደ መከረው መጽሐፉ ሲነግረን እንጂ፣ ቀኖና ሲሰጠው አንመለከትም። ለድኾች ወይም ለተጨቈኑ ምሕረት፣ ቸርነት፣ ፍትሕ፣ ጩኸታቸውን መስማት … ማድረግ የነገሥታት ግዴታ እንጂ የቀኖና ወይም የንስሐ ጉዳይ አይደለም፤ እግዚአብሔርም ይኸንኑ ይወድዳልና (መዝ. 33፥5፤ ምሳ. 21፥3፡ 13፤ 28፥5፤ ኢሳ. 1፥17፤ ኤር. 22፥3፤ ሚክ. 6፥8)። ነገር ግን የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ አጥምሞ ሲያቀርብ እንመለከተዋለን።

ነገር ግን  የመድሎተ “ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ንባብም፤ ዐውዳዊ ትርጕሜን ስለማይጠነቅቅ እና ለቅዱስ ቃሉ በመታመን በትክክል አንብቦ ስለማይተረጕም ቃሉ ያላለውን ብሎአል ብሎ ሲተረጕም እንመለከተዋለን። ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋል ወደ ልቡ ይመልሰው፤ አሜን።



[1] መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 1፤ ገጽ 234

[2] መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 1፤ ገጽ 246

[3] ገጽ 243

No comments:

Post a Comment